ለሴኩላሪዝም እቆማለሁ

Home Forums የወጣቶች መድረክ ለሴኩላሪዝም እቆማለሁ

 • This topic is empty.
Viewing 0 reply threads
 • Author
  Posts
  • #3614 Reply

   በምህረት ሳምሶን*  

   ሐይማኖት ከረዥም ግዜ ጀምሮ በሰው ልጅ ህይወት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ ኢትዮጵያም ከዚህ ተጽዕኖ አላመለጠችም፡፡ በኢትዮጵያውያን ህይወት ውስጥ ሐይማኖት ትልቅ ስፍራ አለው፡፡ ሐይማኖት በኢትዮጵያውያን ማህበራዊ ህይወት እና ፖለቲካ ውስጥ ውስብስብ እና አነጋጋሪ መሆን ከጀመረ ከራርሟል፡፡ ዳሩ ግን ከዘመናዊነት ማበብ ጋር ተዛምዶ፣ የሐይማኖት ሚና እየደበዘዘ መጥቷል፡፡ ቢሆንም ከቅርብ ግዜያት ወዲህ የሚስተዋሉት ክስተቶች የሚያስረዱት ግን ተቃራኒውን ሁነት ነው፡፡ ሐይማኖት ወደ ሜዳው የተመለሰ ይመስላል፡፡ ቢሆንም መመለሱ ሁልግዜም በመልካም የሚታይ አይደለም፡፡ የትኛውም ታዛቢ እንደሚረዳው በሐይማኖት እና በፖለቲካ መሐል የሚኖር አሉታዊ ፍትጊያ [ጨዋታ] ፣ እንዲሁም በሐይማኖት እና በፖለቲካ መካከል የሚኖረው የመለያየት መርህ [the principle of secularism] በመጣሱ ምክንያት  ነገሮችን ምን ያህል ወደ አደገኛ መስመር እየወሰዳቸው እንደሆነ፣ በተጨማሪም በብሔራዊ አንድነት ላይ አደጋ እንደጋረጠ መረዳት ይቻላል፡፡

   በመንግስት እና በሐይማኖት መካከል የሚኖር ድንበር [the principle of secularism] በዘመናዊ መልክ ጎልቶ የወጣው በዘመነ-አብሮሆት ነው፡፡ እንደ ኦክሶፎርድ መዝገበ ቃላት ፍቺ ሴኩላሪዝም [ዓለማዊ መንግስት] በመንግስት እና በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚኖረውን ልዩነት የሚያከብር፣ ወይም አንዳቸው በአንዳቸው ጉዳይ ጣልቃ የማይገቡበት አሰራር ማለት ነው፡፡ ይህ መርህ ዜጎች የፈለጉትን ሐይማኖት የመከተል እና ያለመከተል መብትን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በመርሁ የሚረጋገጠው መንግስት በሐይማኖት ጉዳይ ገለልተኛ ሆኖ እንዲቆም፣ እንዲሁም መንግስት በሃይማኖታዊ ጉዳዩች ውስጥ ጣልቃ መግባት እንደሌለበት ነው፡፡ በሁለቱ መካከል የሚኖረው ቀጭን መስመር ካልተጠበቀ አጠቃላይ ሰላም እና ደህንነትን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ በርግጥ ሴኩላሪዝም ማለት ሐይማኖቶችን የሚፈልጉትን ነገሮች ከማድረግ የሚገፋ ማለት አይደለም፡፡ ሴኩላሪዝም ማለት የሐይማኖት እና የመንግስት መለያየት ነው፡፡ ይህም ሲባል ሐይማኖት ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከማህበራዊ እና ከባህላዊ የህይወት አውዶች ራሱን ሲነጥል ነው፡፡  ይህ መርህ በአማኞች መካከል ነጻነት፣ መቻቻል እና እኩል ዕድልን ይፈጥራል፡፡ በዚህ መሰረት መርሁ ሐይማኖት በግልጽ የግል ጉዳይ ይሆናል፡፡

   ቢሆንም ግን ሐይማኖት እና መንግስት የሚገናኙበት መስመር አለ፡፡ የመጀመሪያው ፖለቲካዊ ህብረት ነው፡፡ ይህም ሲባል ህግ በሐይማኖት ተቋማት ሲወጣ ወይም ተቋማቱ ራሳቸው የህግ ምንጭ ሆነው ሲያገለግሉ ሲሆን፤ ሁለተኛው ተቋማዊ ህብረት ነው፣ በዚህ እሳቤ የሐይማኖት ተቋማት እንደመንግስታዊ ተነጻጻሪ ተቋማት ሲመሰርቱ የሚስተዋል ግንኙነት ነው፡፡ ሶስተኛው ግንኙነታቸው ፍልስፍናዊ ህብረት ወይም ግብን መሰረት ያደረገ ግንኙነት ነው፡፡ ይህም ማለት የሐይማኖትም ሆነ የመንግስት መዳረሻ ግብ ሌላውን ማገልግል ነው፡፡ ስለዚህም ግባቸውም ወይም መዳረሻቸው አንድ ነው ማለት እንችላለን፡፡ በሌላ ገጽ ሁለቱ የሚለዩበትን መንገድ በዚህ መልኩ ማሳየት እንችላለን፡፡ በሐይማኖት እና በመንግስት መካከል ያለው ልዩነት በእነዚህ ሁለት መንገዶች ይገለጻል፡፡ አንደኛው የጋራ ግንኙነት [ጣልቃ አለመግባት] ሲሆን፣ አንዱ የአንዱን መስመር ማክበርን ይመለከታል፣ በርግጥ አስፈላጊ በሚሆንበት ግዜ አንዱ የአንዱን ድንበር ሳይዘል በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ሊደጋገፉ፣ ሊተባበሩ አይገባም ማለት አይደለም፡፡ ሌላኛው ጉዳይ በሁለቱ መካከል በሚኖር ግንኙነት ውስጥ ሐይማኖት በመንግስት አይን ሁሌም በጥርጣሬ ውስጥ ያለ ተቋም ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ መንግስት የሐይማኖት ጠላት እየሆነ ይሄዳል፡፡ መንግስት የሐይማኖት ተቋማት የግለሰብ ነጻነት ላይ ጋሬጣ ይሆናል ብሎ ባሰበበት ወቅት ሐይማኖቱን ሊጨቁን እና ሊያግድ ይችላል፡፡ ለዚህ አብነት የሚሆነን እ.ኤ.አ በ1789 በፈረንሳይ አብዮት ማግስት የተቀሰቀሰው የጸረ-ቄሳዊነት ንቅንቄ ነው፡፡

   ሴኩላሪዝም በኢትዮጵያ  

   ኢትዮጵያ የተለያዩ ሐይማኖቶች እና እምነቶች መገኛ ነች፡፡ በኢትዮጵያ የሴኩላሪዝም ፅንሰ-ሀሳብ ጅማሬ/ትውውቅ በአንፃራዊነት የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው። በዘውዳዊው ስርዓት የሃይማኖት እኩልነት ጥያቄ ተነስቷል፡፡ በወቅቱ ግን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና የመንግስታዊ ሃይማኖት እውቅና ነበረው፣ ከሌሎች ሐይማኖቶች በተሻለ መንግስታዊ ድጋፍም ነበረው፡፡ በወቅቱ ሐይማኖት የስልጣን መቆናጠጫ እንዲሁም ዜጎችን ማስገበሪያ መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በግዜው ስልጣን ላይ የነበሩ ኃይሎች ስልጣናቸው ከሰው በላይ ከሆነ አካል እንዳገኙት እንዲታመን አድርገዋል፡፡ ሐይማኖት ለዚህ እንደመሳሪያ ሆኖ አገልግሏል፣ ሐይማኖት እና መንግስትም አንድ ነበሩ፡፡

   እ.ኤ.አ በ1974 የዘውዳዊው ስርዓት ስልጣኑን በሶሻሊስቱ የደርግ ስርዓት ሲነጠቅ፣ ነገሮች መልካቸውን ቀየሩ፡፡ ደርግ ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በኃላ ህጋዊ የሐይማኖት ነጻነት፣ እኩልነት እና ሴኩላሪዝም በይፋ አወጀ፡፡ በእርግጥ በተግባር የሶሻሊስት ፖሊሲዎች ኢ-መለኮታዊ (ኤቲስታዊ) ባህሪ ነበራቸው፡፡ በተጨማሪም የሐይማኖት ነጻነትና እኩልነትን ይጋፋሉ፡፡ በዚህ ምክንያት መንግስታዊ ሐይማኖት-ጠልነት እና በሐይማኖት ላይ የሚደርስ መድሎን ወለደ፡፡ የአብዮቱም ግብ የነበረው ሐይማኖት-አልባዋን ኢትዮጵያ መገንባት ሆነ፣ በዚህ ወቅት ለሐይማኖት ክፍት ቦታ አልነበረም፡፡ ከደርግ መውደቅ በኃላ እ.ኤ.አ በ1995ቱ ህገ-መንግስት አንድ ግለሰብ የፈለገውን ሐይማኖት የመከተል እና የሐይማኖቶች እኩልነት እውቅና ተሰጠው፡፡ በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 11 በግልጽ ሴኩላሪዝም ተደነገገ፡፡ እንዲሁም ምንም አይነት መንግስታዊ ሐይማኖት እንደሌለ ታወጀ፡፡ በዚህ ድንጋጌ መንግስት እና ሐይማኖት ተለያዩ፣ ጣልቃ-ገብነትንም ከለከለ፡፡ ይህ የሚያመለክተው ሁለቱም በጋራ መቆም እንደማይችሉ ነው፡፡

   ለአንድነት ስጋት

   በአሁኑ ወቅት ሐይማኖት በኢትዮጵያ የፖለቲካ የልዩነት መስመር መሆኑ ግልጽ እየሆነ ይመስላል፡፡ ይህም ዜጎችን ለልዩነት እና ለግጭት እየዳረገ ነው፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዜጋ አማኝ እንደመሆኑ፣ ህይወቱ ላይ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ የፖለቲካ ርዕዮቶች ይልቅ ቅድሚያ ለእምነቱ እና ለሚከተለው ሐይማኖት መስጠቱ እንግዳ አይደለም፡፡ በርግጥ በ1970ዎቹ አጋማሽ ሴኩላሪዝም በህጋዊ መንገድ በኢትዮጵያ የተዋወቀ ቢሆንም ፣ የሐይማኖት ተቋማት ላይ እና መሪዎች ላይ መንግስታዊ ጫናው አልረገበም፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎች የሐይማኖት ሰዎችን ከኃላፊነታቸው እና ከአምልኮ ቦታቸው ላይ ከማንሳት እስከ ማንገላታት የደረሰ ነበር፡፡

   በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚስተዋለው ሐይማኖታዊ ችግር መነሻው የሴኩላሪዝምን መርሆ ባለማክበር እና በአግባቡ ባለመተግበር የሚከሰት ነው፡፡ የሴኩላሪዝም መርሆ በአግባቡ የማይከበር ከሆነ፣ የዚህ መርሆ ዋነኛ አላማ፣ የሐይማኖቶችን እኩልነት መጠበቅ የሚለው እሳቤ ይጣሳል፡፡ የትኛውም አይነት ኢ-እኩልነት ደግሞ የብሔራዊ አንድነት ስጋት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

   የሴኩላሪዝም መርሆች ተጥሰዋል፣ በአግባቡ አልተተገበሩም  የሚያሰኙ ምሳሌዎችን ከዚህ በታች እናያለን፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በፖለቲካ ፓርቲ ስም የተደራጁ ነገር ግን፣ ሐይማኖታዊ ፍላጎት አላቸው ተብለዉ የሚጠረጠሩ ድርጅቶች መኖራቸው አንዱ ነው፡፡ ለአብነት ‘እናት ፓርቲ’ እና ‘ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ’ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አንዳንዶች የብልጽግና ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ከብልጽግና ወንጌል እንደተቀዳ ይከራከራሉ፡፡ ይህ የብልጽግና ወንጌል እሳቤ የጴንጤኮስታል ክርስቲያኖች ሲሆን፣ የእምነቱ ተከታዮች የሚፈልጉትን ነገር በማሰብ እና በጽኑ በመመኘት በእጃቸው ማድረግ እንደሚችሉ ያስተምራል፡፡ ዳሩ ግን የትኛውም ፓርቲ ከሐይማኖታዊ ጉዳዮች ጋር ያለውን ትስስር ሲያምን አይደመጥም፣ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ህግ የሐይማኖት ድርጅቶች የፖለቲካ ፓርቲ ሆነው መመዝገብ እንደማይችሉ ስለሚከለክል ይመስላል፡፡

   ሌሎች የሐይማኖት ተቋማት ሐይማኖታዊ ኢ-እኩልነት እና አድሎኣዊነት በእነርሱ መካከል እንዲሁም በእስልምና እና በኦርቶዶክስ መካከል እንደሚስተዋል ይከሳሉ፡፡ ከእነዚህ ክሶች በተጨማሪ በዋናነት የሚነሳው ለሐይማኖት ድርጅቶች የሚደረገው የመሬት ክፍፍል ጉዳይ ነው፡፡ ምናልባት በስፋት የሚታወቀው እና በማሳያነት የሚነሳው በአክሱም ከተማ መስጂድ ስለመስራት የሚነሳው ውዝግብ ተጠቃሽ ነው፡፡ በሌሎች ከተሞች እንዲሁ የፕሮቴስታንት አማኞች በቀደመው ስርዓት ስለተወረሰባቸው ንብረት ምላሽ እንዲሰጣቸው ዛሬም የሚያነሱት ጥያቄ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የሚሰጡት ምላሽ የመልካም አስተዳደር ችግር መሆኑን በመግለጽ መመሪያ አውጥተዋል፡፡ ጥያቄያቸውም ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡ የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያንም በሌላ በኩል በአንዳንድ መንግስታዊ ውሳኔዎች የተወሰዱ ንብረቶቿ ላይ ካሳ የማግኘት ጥያቄዎችን በተወካዮቿ በኩል አንስታለች፡፡

   ሌላው ከመሬት ይዞታ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ጥያቄ በመንግስት-መር ልማት ስም የሐይማኖት ተቋማት ባሉበት አከባቢ ለልማት ስራዎች በሚደረጉ መስፋፋቶች የሚነሱ ክርክሮች ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ በስፋት የሚታወሰው የወልቃይት የስኳር ፕሮጀክት ሲሆን በዋልድባ ገዳም ይዞታ የክርክር እና የግጭት ምክንያት ሆኗል፡፡ መንግስት ለልማት ያለው ተነሳሽነት የሚደነቅ ቢሆንም፣ ዳሩ ግን የፕሮጀክቱ ስራ በአከባቢው ላይ ባለው የዋልድባ ገዳም ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል የእምነቱ ተከታዮች ያምናሉ፡፡ ለልማት ተብሎ በአከባቢው መንገድ፣ የመኖሪያ መንደር፣ የገበያ ሱቆች እና የመሳሰሉት መከፈት ገዳሙ ሊያሳካው ከሚያስበው ዓላማ ጋር ይጋጫል፡፡ እንዲሁም የገዳሙን ሐይማኖታዊ ግብ ያደናቅፋል የሚል እምነት አላቸው፡፡

   በተጨማሪም የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እና መስጂዶች በተለያዩ አከባቢዎች እየወደሙ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው መንግስት መጠበቅ፣ ማክበር እና ማስከበር ያለበትን የሐይማኖት ደህንነት ዋጋ እንዳልሰጠው እንዲሁም የሴኩላሪዝምን መርሆ እንዳላከበረ ነው፡፡ ይህን መሰል ጥቃቶች እና ውጥረቶች በህዝብ ደህንነት እና በሀገሪቱ መረጋጋት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ከማሳደር አልፎ ፖለቲካዊ አንድምታ አላቸው፡፡ ጽንፈኝነት እያደገ ሲሄድ ሀይማኖት ቀስቃሽ ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ በአመጽ ግጭቶችም ውስጥ እንደ መሣሪያ ሊያገለግል ይችላል፡፡

   እነዚህና ሌሎች ችግሮች የእለት ተዕለት ጉዳያችን መሆን ከጀመሩ ከራረሙ፡፡ ከላይ ያሉት ማሳያዎች እንደሚጠቁሙት፣ የሴኩላሪዝም መርሆ ተጥሶ፣ መንግስት በሐይማኖት ጉዳይ፣ ሐይማኖት በመንግስት አጀንዳዎች ጣልቃ መግባቱ እየተስተዋለ ነው፡፡ አንዳንዶች ለዚህ እንደመነሻ የሚያደርጉት የሴኩላሪዝም መርሆን ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ፍጹም አልስማማም፡፡ እኔ እንደማምነው ለዚህ ችግር መነሻ የሚሆነው የሴኩላሪዝም መርሆ በአግባቡ አለመተግበሩ ነው፡፡ መርሆዎን መተግበር ከጀመረ አንስቶ በቅጡ ተረድቶ መሬት ላይ ያወረደው የለም፡፡ በቅጡ መሬት ላይ ያልወረደን ቀመር ስህተት ነው ማለት ስሜት አይሰጥም፡፡

   የብርሃን ነጸብራቅ

   በአገራችን ሴኩላሪዝም ደካማ ጅምሮች ሊኖሩት ይችላል፣ ቅቡልነቱም ሆነ ተግባራዊነቱ ከተገቢው በታች እና ያነሰ ሊሆን ይችላል። የሆነው ሆኖ እንደኢትዮጵያ ላሉ ሐገራት ያለው ጠቀሜታ በቀላሉ ሊገለጽ አይችልም። በእርግጥ ሴኩላሪዝም ጉዳቶቹ እንዳሉት አይዘነጋም፤ ከጉድለቶች መካከል የሰዎችን አስተሳሰብ በማዛባት በቁሳዊው ዓለም ላይ እንዲያተኩር እና መንፈሳዊውን ህይወት ችላ በማለት የሞራል ውድቀትን ይፈጥራል የሚል ትችት አለ፡፡ ነገር ግን ለአንድ ዲሞክራሲያዊ ሀገር ትልቅ ስኬት ነው ብዬ አምናለሁ። ከሁሉም በላይ፣ የግል እምነትን የመምረጥ እና የመተግበር ነፃነት ይሰጣል እናም ምንም አይነት የመንግስት ህግ በሃይማኖት ስርዓት ላይ ሊጫን አይገባም። ሆኖም ግን የዕምነት ተቋማት ተግባራቸው የዜጎችን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግስት ጣልቃ መግባት የለበትም ማለትም አይደለም።

   መንግስት የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ህዝባዊ እንቅስቃሴን እና መግባባትን በሚያደፈርሱ ቡድኖች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። በሁሉም ሃይማኖቶች መካከል ያለውን እኩልነት ማስጠበቅ እና አለመረጋጋት የሚያስከትሉ ማነቆዎችን ማስወገድ ይጠበቅበታል። በተጨማሪም እኩል እድሎችን በመስጠት ከማንኛውም ሀይማኖታዊ ተፅዕኖ ራሱን ማራቅ፣ የየትኛውንም ሀይማኖት ዶግማዊ ጉዳዮችን ከመንካት መቆጠብ እንዲሁም መቻቻል እና ሀይማኖታዊ ብዝሃነት  በዜጎች መካከል እንዲኖር ማድረግ አለበት፡፡ በሌላ በኩል የሃይማኖት ተቋማትም በመንግስት ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ መግባት የለባቸውም። በእኔ እምነት ይህ ኃላፊነት በመንግስት ላይ ብቻ ሳይሆን እንደ ዜጋ  የእኛም ነው። ዜጎች ህግን አክብረው በልዩነታችን ላይ ከማተኮር ይልቅ አንድ በሚያደርጋቸው ጉዳይ ላይ ማተኮር አለባቸው።

   ሴኩላሪዝም በአግባቡ ካልተተገበረ የግለሰቦች የእምነት ነፃነት፣ የአስተሳሰብ፣ የአመለካከት እና ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት ሙሉ በሙሉ ይጣሳል። እነዚህ ነፃነቶች ሲጨቆኑ የሰው ልጅ መንፈሳዊ ልዕልና እና የአዕምሮ ዕድገት ውስን ይሆናል:: በተጨማሪም የሰው ልጅን ክብር ከመሠረታዊ ተፈጥሮ ጋር ያለውን መስተጋብር ይቃረናል፡፡ ስለዚህ የሴኩላሪዝምን መርህ ግንባር ቀደም ቦታ ሊሰጠው የሚገባ እና በአግባቡ መተግበር ያለበት ጉዳይ መሆኑን ልንስታወስ ያስፈልጋል፡፡

   *ምህረት ሳምሶን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተማሪ ናት።

   የአታሚው ማስታወሻ: ይህ ጽሑፍ ካርድ የወጣቶችን ሥልጡን እና ምሁራዊ የውይይት ልማድ ለማሳደግ “በወጣቶች የምክክር መድረኩ” ከሚያስተናግዳቸው ጽሑፎች አንዱ ነው።  በዚህ ዓምድ ለመስተናገድ ወይም ለዚህ ጽሑፍ መልስ ለመስጠት ከፈለጉ በ info@cardeth.org ላይ ኢሜይል ያድርጉልን።

Viewing 0 reply threads
Reply To: ለሴኩላሪዝም እቆማለሁ
Your information: