ለውጥ (?) እና ባዶ ሆድ

Home Forums የወጣቶች መድረክ ለውጥ (?) እና ባዶ ሆድ

 • This topic is empty.
Viewing 0 reply threads
 • Author
  Posts
  • #4232 Reply

   ፍቅር ጌታቸው* 

   በፖለቲካ ሽግግር ዙሪያ የጋራ ስምምነት ያለው ሐሳብ በ’ርግጥ ባናገኝም፤ ኦዶኔል እና ሼምተር እንደሚከራከሩት “ለውጥ በአንድ ጎኑ ወሰን ያለው ጠቅላይ አገዛዝን የማፍረስ እንቅስቃሴ ሲጀመር ነው፡፡ በሌላ መልኩ ጠቅላይ አገዛዙን ወደ አዲስ አይነት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መለወጥን ይጨምራል፡፡ ወይም አብዮታዊ አማራጭ ማስቀመጥ ነው” ይላሉ።

   እጅግ የተለመደው አለም-አቀፋዊ ጉዳይ አምባገነናዊ አገዛዙን በመናድ ወደ ዲሞክራሲ በሚደረግ ሽግግር ውስጥ የፖለቲካ ሊሂቃን የበጀት ውሳኔ ተጽዕኖ ማሳረፉን ነው፡፡ አድሎዓዊ የሆነው የሀብት ክፍፍል፣ ሐብት የማፍራት ዕድል እና የህዝብን ሐብት ማስተዳደር እነዚህ ሁሉ በህብረተሰቡ መካከል የሚኖረውን ግንኙነት፣ የሐብት ፈጠራ እና ተጨማሪ ሐብት የማግኘትን እና የማፍራትን ሚና ይወስናሉ፡፡ ኢትዮጵያም ከእዚህ ውጪ አይደለችም፡፡ እውነታው ሐገሪቱን ወደ ከፍተኛ ለውጥ ያሻገራት የ2010 ዓ.ም ተቃውሞ የተወለደው የሐብት ክፍፍልን መሰረት አድርጎ ቢሆንም በውስጡ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ጥያቄዎችን ያዘለ ነበር፡፡

   አምባገነናዊ አገዛዞች የግለሰቦችን እና የማህበረሰቡን መሰረታዊ ፍላጎቶች አያሟሉም፡፡ እንዲሁም ጤናማ ማህበረሰባዊ ወይም የመንግስት እና የህዝብ ግንኙነት እንዲዳብር አያደርጉም፡፡ ሁልግዜም ለለውጥ መነሻ የሚሆነው እንቅስቃሴ እንዲሟሉለት የሚፈልጋቸው ጥያቄዎች የቀደመው የማህበረ-መንግስታዊ ስሪትን በድርድር መቀየርን መሰረት ያደረገ ይሆናል፡፡ ይህ የሚገነባው መንግስት ለዜጎች በሚሰጠው አገልግሎት፣ በቀደመው ስርዓት ለተገለሉ ዜጎች በሚሰጠው ውክልና እንዲሁም የእኩል ተጠቃሚነት ዕድልን በማሳደግ እና እኩል የህግ ከለላ በማግኘት መርህ ላይ ይመሰረታል፡፡

   ስለዚህም ለውጡ ፈጣን፣ የሚታይ እና ግልጽ የኢኮኖሚ እና አሳታፊ የሆነ የማህበራዊ ፖሊሲ እንዲሁም ለመዋቅራዊ ኢ-ፍትሃዊነት ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ የለውጡ መሪዎችም እንዲሁ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን የኃይል መዋቅር ለማስተካከል አልመዋል፣ በተጨማሪም ትኩረታቸው ስልጣኑን ማን ይዞታል የሚለው ብቻ ሳይሆን፣ ሐብቱ በማን እጅ ነው ያለው፣ የሐብት ፈጣሪውስ ማነው የሚለውን ለመቀየር ሞክረዋል፡፡

   የኢህአዴግ ልማታዊ መንግሥት

   የኢህአዴግ ኃይል የመንግስትን ስልጣን ተቆጣጥሮ የስልጣን ክፍፍል ከማድረጉ አስቀድሞ የኢትዮጵያ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ታሪክ በባህሪው በማዕከላዊ መንግስት ቁጥጥር ስር የዋለ ነበር፡፡ የመንግስት ወጪ በተለያየ ተዋረድ የተከፋፈለ ቢሆንም፣ ሐብት የመሰብሰብ ስልጣን በማዕከላዊ መንግስት ቁጥጥር ስር መሆኑ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡

   ህወሓት/ ኢህአዴግ በጫካ ትግል በነበረበት ወቅት ጥብቅ የማርክሲስት-ሌኒኒስት ርዕዮት አራማጅ ነበር፡፡ ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኃላ በተፈጠረው አለም-አቀፋዊ ለውጥ ምክንያት ራሱን በፍጥነት እንዲቀይር አስገድዶታል፡፡ ድርጅቱንም ከቀደመ ሃሳቡ ጋር የሚገጥም ርዕዮተ ዓለም እንዳይኖረው አደረገው፡፡ ኢህአዴግ በ1983 ዓ.ም ወደ ስልጣን ሲመጣ ለተራድኦ ድርጅቶች እና በለጋሽ ተቋማት ሐሳብ በቀላሉ ይጠመዘዝ ነበር፡፡ ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ፣ የግል ባለሐብቶች ላይ የተጋረጡ እንቅፋቶችን ለማንሳት፣ የገበያ ሚናን ለማሳደግ በሚል በድንገት ፊቱን ወደ ነጻ ገበያ ርዕዮተ ዓለም አዞረ፡፡

   በ1993 ዓ.ም አቋሙን አስተካክሎ የልማታዊ መንግስት ጽንሰ-ሃሳብን የሐገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያነቃቃ ሞዴል አድርጎ አቀረበ፡፡ በወቅቱ የተራድኦ ድርጅቶች ተጽዕኖ መዳከም መንግስት በሃሳቡ እንዲገፋ ረድቶታል፡፡ ኢትዮጵያ በግዜው የምዕራቡ ዓለም የምስራቅ አፍሪካ ታማኝ ወዳጅ እንዲሁም ከዓለም ሁለተኛዋ ግዙፍ የውጭ ዕርዳታ ተቀባይ ሀገር ነበረች፡፡

   የኢህአዴግ ልማታዊ መንግስት ጽንሰ-ሃሳብ ከፍተኛ ዕድገት ያስመዘገበ፣ በሰው ሐብት ላይ የዜጎች የሸማችነት አቅምን ያሳደገ፣ እና ህዝባዊ መዋዕለ-ንዋይን በማሳደግ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር አድርጓል፡፡ በእዚህ የእድገት መንገድ ውስጥ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2022 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሐገራት ተርታ እንደምትገባ ይጠበቅ ነበር፡፡

   የሚያስቆጨው ነገር ይህንን ዕድገት የመንግስትን አምባገነንነት፣ ነጻ ድምጾችን ለማፈን፣ የስርዓቱ ተቃዋሚዎችን ለማንገላታት የሚቀርብ መከራከሪያ ነበር፡፡ በርግጥ የስርዓቱ ቁልፍ ሰዎችም በህዝብ ፊት ስለሚፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች እና የዲሞክራሲ ጥሰቶች አንድም ግዜ ክደው አያውቁም፡፡ መከራከሪያቸው ምክንያቱም “በባዶ ሆድ ዲሞክራሲ ሊኖረን አይችልም” የሚል ነው፡፡

   መንግስት የአውራ ፓርቲ የበላይነቱን እና ጠቅላይነቱን አረጋግጦ ለመቀጠል፣ የልማታዊ መንግስት ርዕዮተ ዓለምን እያቀነቀነ፣ ፖለቲካዊ ተቀናቃኞቹን አዳክሞ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሙሰኛ እና ለስርዓቱ ታማኝ አገልጋይ የሆኑ ግለሰቦችን አቅፎ ይዞ ነበር፡፡

   የኢህአዴግ ፖለቲካዊ ሐብቶች

   ናታን “በአፍሪካ የፖለቲካ ስልጣን በአብዛኛው የራስን እና በዙሪያው የሚገኙ ሰዎችን በሐብት ማበልጸጊያ መንገድ ነው” በሚለው ሐሳብ እስማማለሁ፡፡ ከ2010 ዓ.ም ቀደም ባለው በነበሩት አመታት ኢትዮጵያ፣ የሀገሪቱ ሐብት በኢህአዴግ እና በዙሪያው ባሉ አካላቶች ቁጥጥር ስር የወደቀ ነበር፡፡ የፖለቲካ የሐብት ምንጭ የነበሩት መንግስታዊ የልማት ተቋማት፣ የክልል በጀትን በእጅ ማስገባት፣ እንዲሁም ለስርዓቱ እና ለባለስልጣናቱ ቅርበት ያላቸውን ግለሰቦች የመጥቀም አካሄድ ይስተዋል ነበር፡፡

   ለስርዓቱ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ የነበሩት የመንግስት የልማት ተቋማት ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ ከቀደመው ስርዓት ወደ አዲሱ መንግስት የተሻገሩት (የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮዩምኒኬሽን ኮርፖሬሽን) እና በፓርቲው ቁጥጥር ስር የነበሩት “ኢንዶውመንት” ድርጅቶች ናቸው፡፡ ለአብነት የህወሓት የነበረው ኤፈርት እና ፓርቲው ምንም በህግ ቢለያዩም፣ ለፓርቲው ቀጥታ ድጋፍ ባያደርግም፣ ለስርዓቱ ታማኝ የሆኑ ሰዎችን ግን በስራ እድል፣ በምልመላ፣ በኮንትራት ስራ እና በመሳሰሉት ተጠቃሚ የሚያደርግ ልምድ ነበረው፡፡

   ሁሉም የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች በክልላቸው ትላልቅ ቢዝነሶችን የሚቆጣጠሩበት “ኢንዶውመንት”፤ ለምሳሌ የኦሮሚያው ‘ቱምሳ’ና የአማራው ‘ጥረት’፤ ቢኖራቸውም ከብዛት፣ ከጥራት እና ከተሰማሩባቸው ዘርፎች እና ክልሎች ስፋት አንጻር ኤፈርትን የሚያክለው አልነበረም፡፡ ይህ ማለት አንጻራዊ በሆነ መልኩ ኤፈርትን ተጠግተው በትግራይ ተጠቃሚ የሆኑትን ያህል ግለሰቦች የሌሎቹ ፓርቲዎች ድርጅቶች መጥቀም አልቻሉም፡፡ ለዚህም ይመስላል ለውጡን የፈጠረው አመጽ ሌሎች እህት ፓርቲዎች በሚያስተዳድሯቸው አከባቢዎች ሲነሱ፣ በትግራይ ይህን መሰል አመጽ ያልተስተዋለው፡፡

   እንደ እውነቱ ከሆነ ኤፈርት ግዙፍ የፓርቲ ድርጅት 60 በመቶ የትግራይን ክልል ውስጣዊ ገቢ ያስገኛል፣ እንዲሁም ለክልሉ እና ለፓርቲው ነጻ የፋይናንስ ምንጭ መሆን ችሏል፡፡ አንዳንዴም ለትግራይ ክልል ከፌደራል የሚመደበው በጀት በሚያንስበት ወቅት ክልሉን በመደጎም ይታወቃል፡፡

   ለውጡ ምን ይዞ ነበር ?  

   በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ የገባችበት የፖለቲካ ትርምስ  በመሓል ሐገር እና በዳር ሐገር መካከል ለዓመታት የኖረው ፍጥጫ ውጤት ነው፡፡ የ2010 ዓ.ምቱ ለውጥ በብዙዎች ዘንድ የተጠበቀው የዲሞክራሲ፣ የአስተዳደር እና የሰብዓዊ መብት ችግሮችን ብቻ ይፈታል ተብሎ አይደለም፣ በመሰረታዊነት ስር የሰደደውን ኢ-ፍትሃዊ የሐብት ክፍፍል መስመር ያስይዛል ተብሎ ነበር፡፡ ድህረ-2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሐገሪቱን የፖለቲካ ፋይናንስ ገለባብጦ፣ የባንክ እና የቴሌኮም ዘርፉን ለግል ባለሐብቶች በከፊል ለማዛወር ሞክሯል፡፡ በተጨማሪም የውጭ ምንዛሪውን ለቁልፍ ብሔራዊ ልማቶች እያዋለ፣ የብር የመግዛት አቅምን ከዶላር አንጻር እያዳከመ፣ ትግራይን የፖለቲካ የሐብት ምንጭ መሆኗ እንዲከስም አድርጓል፡፡

   ይህ ግን ኢህአዴግ ከመንግስት ጋር የተጣመረ ስለነበር እና በመንግስት ውስጥ የተከሰቱት ለውጦች በሁሉም ሴክተሮች የሚተረጎም አንድምታ ነበረው፣ እንዲሁም ጉዞው ቀላል አልነበረም። እ.ኤ.አ. በ 2020 የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ያጠቃው ወረርሽኝ፣ በሰሜን የተቀሰቀሰው ጦርነት፣ በመጀመሪያው አመት ብቻ መንግስት ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ አስወጥቶ ለኪሳራ ዳርጎታል፣ በሚሊዮኖች ህይወት ላይ እየደረሰ ያለው ድርቅ እና ሊታለፍ የማይችል የአለም ኢኮኖሚ ውድቀት ከዩክሬን ጦርነት ጋር ተዳምሮ ቀደም ሲል የነበሩትን ሁኔታዎች እያባባሰ ይገኛል።

   ምንም እንኳን በመጀመሪያው ወቅቶች መንግስት የተቀናጁ የሚመስሉ የፖሊሲ እርምጃዎችን የወሰደ ቢመስልም (እንደ የባንክ ኖቶች መቀየር እና የገንዘብ ፍሰት መገደብ) እንዲሁም ብዙ የገንዘብ ፍሰት ወደ መደበኛው ስርዓት ሲገባ የሚያመጣውን ሕገ-ወጥ የፋይናንስ ፍሰት የሚገድብ ቢሆንም በቂ እንዳልሆኑ ግልጽ ሆኗል። እናም በዚህ ሁሉ ውዥንብር ውስጥ መንግስት የወሰዳቸው እርምጃዎች ለመዋቅራዊ ችግሮች ዘላቂ የመዋቅር ማሻሻያ መስጠትን ሳይሆን ለ”ኤርጎኖሚክስ” ቅድሚያ በመስጠት በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ወጪ በማድረግ በመዲናዋ የሚገኙ የፌዴራል መስሪያ ቤቶችን ማደስና እንደ “ሸገርን ማስዋብ” ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ላይ እንዲሁም የታይታ ማሻሻያዎችን ማድረግ ላይ ነው፡፡

   መጪው ጊዜ ምን ይዟል ? 

   የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ክትባት አለምን ሐብታም እና ደሃ በሚል ለሁለት የተከፈለውን ጎራ ግልጽ አድርጎታል፡፡ የአለም ኢኮኖሚ ለመነቃቃት እየሞከረ ባለበት በእዚህ ሰዓት፣ ባለሐብቶች የኢኮኖሚውን መረጋጋት እና ሰላም ማረጋገጥ ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህም ግዙፍ ዓለም-አቀፍ ተቋማት ክትባት ያላገኘ ሰራተኛ ቀጥረው ምርታማነታቸው እንዲዋዥቅ አይፈልጉም፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ቁጥር ከ80 በመቶ በላይ ዜጎቿ አልተከተቡም፡፡

   መንግስት በግዴለሽነት የሚያወጣው ወጪ፣ ለቱሪስት መስህቦች ከሚያወጣው የተጋነነ ኢንቨስትመንት ጋር ተደምሮ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢንዱስትሪዎች መዘጋታቸው፣ ስራ-አጥነት እየጨመረ መምጣቱ፣ ከአጠቃላይ የጦርነት አውድ እና የኃይል ማመንጫ ማዕከላት ጋር ታክሎ የምግብና ነዳጅ ታሪፍን ጨምሮ አስፈላጊው የገቢ ምርቶች ዋጋ እየጨመረ ይገኛል። ጉዳዩ ችላ ከተባለ ሀገሪቱን ወደ ሌላ የፖለቲካ ቀውስ ይመራታል። ምንም እንኳን የባንክ፣ የቴሌኮም እና የኢትዮጵያ አየር መንገድን በከፊል ወደ ግል ማዞር በሀገሪቱ ፋይናንስ ላይ ፈጣን ክፍተቶችን መሙላት ቢችልም የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሰፋ ያለ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን የሚያመጣ ዘላቂ መፍትሄ አይሰጥም።

   በእርግጥ፣ በኢትዮጵያ አሁን ባለው አዝማሚያ በጣም ድሃ ለሆኑ ዜጎች ህልውና እጅግ ከባድ ግዜ ነው። ስለሆነም መንግስት የማህበራዊ ድጋፍ ፕሮግራሞችን የበለጠ ድጎማ የሚያደርግበት፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ቡድኖች በሰፊው የሚደጉም፣ እንዲሁም ባልተመጣጠነ ዕድገቱ ተጎጂ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረጉ እቅዶች መንደፍ ይኖርበታል፡፡

   የአይኤምኤፍ አዲሱ ሪፖርት በ2023 የኢትዮጵያ እድገት 5.7 በመቶ እንደሚሆን ቢተነብይም፣ መንግስትም በበኩሉ ከልክ ያለፈ የፕራይቬታይዜሽን ፕሮጀክቶች ላይ እንደገና እያሰበ ቢመስልም፣ ለበለጠ የኢኮኖሚ ሊበራላይዜሽን መጓጓቱ ግን በግልጽ ይታያል። ስለሆነም የኢትዮጵያ ተራማጅ ኃይሎች መንግስት ኢኮኖሚውን ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ እንደገና ለማዋቀር የሚወስዳቸው እርምጃዎች የብዙሃኑን የኢትዮጵያውያን ድሆች ተስፋ የሚያቀጭጩ እንዳይሆን እንዲሁም እምነት የተጣለበትን የዲሞክራሲ ግንባታ አደጋ ውስጥ እንዳይከቱ ለማድረግ መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወስድ ሊያስገድዱት ይገባል፡፡

   * ፍቅር ጌታቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዩዝ አሊያንስ ፎር ሊደርሺፕ እና ደቨሎፕመንት ዋና ዳይረክተር ነች። 

   ** የአታሚው ማስታወሻ: ይህ ጽሑፍ ካርድ የወጣቶችን ሥልጡን እና ምሁራዊ የውይይት ልማድ ለማሳደግ “በወጣቶች የምክክር መድረኩ” ከሚያስተናግዳቸው ጽሑፎች አንዱ ነው።  በዚህ ዓምድ ለመስተናገድ ወይም ለዚህ ጽሑፍ መልስ ለመስጠት ከፈለጉ በinfo@cardeth.org ላይ ኢሜይል ያድርጉልን።

Viewing 0 reply threads
Reply To: ለውጥ (?) እና ባዶ ሆድ
Your information: