ሴኩላሪዝምን ማጠናከር፡- የማን ቀዳሚ ስራ ነው?

Home Forums የወጣቶች መድረክ ሴኩላሪዝምን ማጠናከር፡- የማን ቀዳሚ ስራ ነው?

 • This topic is empty.
Viewing 0 reply threads
 • Author
  Posts
  • #3629 Reply

   ኡሪጂ ቢሶ*

   የሴኩላሪዝም እሳቤን ከፊት ማምጣት የሐይማኖት ነጻነትን ለማክበር እና የሰው ልጆችን ሰብዓዊ መብት ለመጠበቅ ምርጫ-አልባ መርሆ ነው፡፡ መንግስት እና ሐይማኖት ያልተለያዩበት ሐገር፣ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ብዝሃ-ሐይማኖት ያለባቸው ሐገራት ላይ፣ አንድ ሐይማኖትን መንግስታዊ አድርጎ እኩልነትን ማስፈን አይቻልም፡፡ ምህረት “ለሴኩላሪዝም እቆማለሁ” በሚለው ጽሁፏ ውስጥ በአጠቃላይ ስለሴኩላሪዝም ሁሉም ሐሳብ ተነስቷል፡፡ ሴኩላሪዝም ለምን እንደሚያስፈልግ እና እንዴት እንደሚሰራ ጥሩ ነጥቦች ተጠቅሰዋል፣ በአጭሩ በሃሳቡ ውስጥ የተዘነጉ መከራከሪያዎች የሉም፡፡ ሙሉ በሙሉ የሴኩላሪዝም አስፈላጊነት በጽሁፉ ውስጥ ሰፍሯል፡፡ ጸሃፊዋ በጽሁፉ ውስጥ ትኩረት ያደረገችው የሐይማኖት ተቋማት በመንግስት ጉዳይ የሚያደርጉትን ተሳትፎ መገደብ ላይ ነው፡፡ ይህ አይነት ምልክታ የዳበረው ምናልባትም ለረዥም ዓመታት በመንግስት ጉዳይ የሐይማኖት ጣልቃ-ገብነት እና ከቅርብ ግዜ ወዲህ እያበበ የመጣው የሐይማኖት አጀንዳ ያላቸው ፓርቲዎች ብቅ ብቅ ማለት የፈጠረው ፍርሃት ሊሆን ይችላል፡፡

   ሴኩላሪዝም፡- አማራጭ መንገድ   

   እስከ አሁን የቀረቡት መከራከሪያዎች እና ማብራሪያዎች የሴኩላሪዝምን መርሆ በመደገፍ ነው፡፡ አንዱ በአንዱ ጉዳይ ጣልቃ መግባት የለበትም የሚለው መርሁ በበቂ ተገልጿል ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን፣ በተመሳሳይ መልኩ ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው መንግስት በሐይማኖት ጉዳይ ጣልቃ የማይገባበት እና ሐይማኖት በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ የሚገባበትን ወሰን ማጥበብ ነው፡፡ መንግስታዊ ሐይማኖት መኖርም ሆነ፣ ሁሉንም ሐይማኖታዊ ድርጊቶች መከልከል የሴኩላሪዝም መርህን ይጥሳል፡፡ መርሁንም ለአደጋ ያጋልጣል፡፡ የሐይማኖት ነጻነት የሰው ልጅ መሰረታዊ መብት ነው፣ በእዚህ መብት ላይ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ዜጎች ማመን ያለባቸውን እና የሌላባቸውን ጉዳይ ከወሰነ፣ ይህንን መብት ሙሉ በሙሉ ይጥሳል፡፡ ሐይማኖት እና መንግስት ህብረት ከኖራቸው የእኩልነት መብት እና የሐይማኖት ነጻነት፣ የመንግስትን ሐይማኖት በሚከተሉና የመንግስትም ሆነ ሌላ ምንም ነገር በማያምኑ ዜጎች መካከል አድሎ ይፈጥራል፡፡

   ዛሬ ላይ በስፋት የሚታወቀዉ የሴኩላሪዝም መርህ ተግባር ላይ መዋል የጀመረው፣ የሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በመንግስት ላይ ያላትን ተጽዕኖ ለመቀነስ በማለም ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ለረዥም ጊዜ የሴኩላሪዝም መሰረታዊ ዓላማ ሐይማኖት በመንግስት ጉዳይ ያለውን ሚና ለመቀነስ ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡ ይህ የሴኩላሪዝም መርህ ለዓለም ብሎም ለሐገራችን እንዲሁም የሐይማኖት ብዝሃነት ላለበት ህብረተሰብ ወሳኝ እሳቤ ነው፡፡ የሴኩላሪዝም መርሆ በአግባቡ የሚተገበር ከሆነ፣ ብዙ መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበር መነሻ የሆነውን የእኩልነት መብት ለማስጠበቅ ይረዳል፡፡ የሐይማኖት እና የመንግስት ድንበር በቅጡ ሲበጅ፣ ‘ሁሉም ሐይማኖት በህግ ፊት እኩል ነው’ የሚለው መርህ ይጠበቃል፡፡

   የመንግስት በሐይማኖት ውስጥ ጣልቃ-ገብነት በኢትዮጵያ

   ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የሴኩላሪዝም መርሆ በአግባቡ የሚሰራው ክልከላው በሁለቱም አካላት በኩል ከሆነ ነው፡፡ ይህም ሲባል የመንግስት ተቋማት በሐይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት ሐይማኖት ተቋማትም በመንግስት ጉዳይ ከመሳተፍ ራሳቸውን ሲያቅቡ ማለት ነው፡፡ በርግጥ ዛሬም አንዳንድ ምልክቶቹ ቢቀሩም፣ ከዚህ በኃላ በግልጽ ሐይማኖት የመንግስት አካል የሚሆንበት ዕድል  ከዘውዳዊዉ ስርዓት መውደቅ በኃላ አክትሟል፡፡ ከዘዉዳዊው ስርዓት መውደቅ በኃላ የመጣው መንግስት የተወሰነ ጉድለት ቢኖርበትም፣ አንጻራዊ በሆነ መልኩ ነጻ እና በራሱ መንገድ ሁሉንም ሐይማኖት በእኩልነት ለመመልከት ሞክሯል፡፡ ይህ ጉዳይ ለጽሁፉ ምላሽ እንድሰጥ ምክንያት ሆኖኛል፡፡ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም የሚከተለው የደርግ መንግስት የመንግስት ሐይማኖት እንዳይኖር እና ሐገሩ እምነት-አልባ እንዲሆን ሞክሯል፡፡ በመርህ ደረጃ መንግስት ሐይማኖት-ጠል ነበር፡፡ በተግባር ግን ሁሉም ሐይማኖት እኩል ነው፣ መንግስታዊ ድጋፍ የሚደረግለትም ሐይማኖት አልነበረም፡፡ ከደርግ መውደቅ በኃላ የመጣው የኢፌዲሪ መንግስት የሴኩላሪዝም መርህን በህገ-መንግስቱ እውቅና ሰጥቷል፣ መንግስታዊ ሐይማኖት እንደሌለ ደንግጓል፣ በሐይማኖት መካከል የሚኖር ጥላቻ እንዳይኖር እንዲሁም ለሁሉም ሐይማኖቶች እኩል የውድድር ሜዳ አመቻችቷል፡፡ ዳሩ ግን የተለያዩ ሐይማኖታዊ ቡድኖች በእጅ አዙር ከመንግስት ጋር እንደሚሰሩ ይነሳል፡፡ ግልጽ የሆነ የልዩነት መስመር ቢኖራቸውም፣ መንግስት በማይታይ እጁ የሐይማኖት ተቋማቱን ለማዳከም ይሰራል ሲሉ ይደመጣል፡፡

   በዚህ ወቅት ሁለቱም አካላት የሴኩላሪዝም መርሆ ድንበራቸውን ቢጥሱ እንኳ ስጋት የሚፈጥር ግዜ አይደለም፣ ምክንያቱም ይህ ግዜ በአንጻራዊነት ለሐይማኖት እኩልነት ጥሩ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅት ሴኩላሪዝምን ለማስከበር ትልቁ ኃላፊነት የሚወድቀው በመንግስት ላይ ነው፡፡ ይህ ኃላፊነት በቅድሚያ የሴኩላሪዝም መርህን በማክበርና ከሐይማኖታዊ ጉዳዮች እጁን በማዉጣት ይገለፃል፡፡ እዚህ ጋር ማንሳት የምንችለው ማሳያ መንግስት በሐይማኖታዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ሲገባ የሐይማኖት እኩልነት እና በህገ-መንግስቱ የተረጋገጡ የህግ መርሆዎች መጣሳቸውን ነው፡፡ እነዚህን ማሳያዎች ማንሳት የፈለግኩት በፖለቲካው መድረክ ለሚስተዋለው ፀረ-መንግስት ተቃውሞና ለሐይማኖታዊ አስተሳሰቦች ህዝባዊ ሚና መጉላት መነሻ ምክንያት ናቸው ስለማምን ነው፡፡ የመንግስት ጣልቃ ገብነትንና የሌላ ሐይማኖት ተቋማት ተፅዕኖ መጉላን የሚፈሩ የሐይማኖት ተቋማት መንግስትን በመቃወም ሳይሆን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የራሳቸውንና ተከታዮቻቸውን ጥቅም በሚያሰጠብቅ አኳዃን መንግስት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ሞክረዋል፡፡

   ዋነኛው የመንግስት ጣልቃ ገብነት የሚስተዋለው የሐይማኖት መሪዎች ምርጫ ላይ፣ በተለይም በኦርቶዶክስ እና በእስልምና የሐይማኖት ተቋማት ላይ ጎልቶ ይታያል፡፡ በሁለቱም የሐይማኖት ተቋማት ውስጥ የመሪ አባቶች ሚና የጎላ እና በተከታዩች ዘንድ ትኩረት የሚደረግበት ፖለቲካዊ ትርጓሜ ይይዛል፡፡ ብዙዎቹ በሐይማኖት ውስጥ የሚስተዋሉት ውስጣዊ ትግሎች መነሻቸው የመንግስት የማይታይ እጅ አንዳንድ ጉዳዮችን ለማደስ ሲሞክር የሚከሰቱ ናቸው፡ የመንግስት ጣልቃ-ገብነት በእስልምና ሐይማኖት ውስጥ በተከሰተበት ወቅት ጉዳዩ አማኞችን ለትግል አነሳስቷል፡፡ በሚሊኒየሙ መጀመሪያ አካባቢ መንግስት አንዳንድ ጉዳዮችን በእጁ ለማድረግ ሞክሮ ነበር፡፡ ርቆ ሄዶ አዲስ ትምህርት ለማስረግ ጥሯል እንዲሁም ኢማሞችን በ’አሕባሽ’ አስተምህሮ ለማጥመቅ ሞክሯል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ መንግስት ስዉር እጁን በኦሮቶዶክስ ቤተክርስቲያን በማስገባት የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች የመንግስትን ፍላጎት በአማኞች እና በቤተክርስቲያን ላይ እንዲያሳድሩ ገፍቷል፡፡

   ሌላው ማሳያ መንግስት በትምህርት ተቋማት ውስጥ አምልኮ ማካሄድን የሚከለክል መመሪያ ካወጣ በኃላ በተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት ቅሬታ ተነስቶበታል፡፡ በተለይም በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ጉዳዩ በበጎ አልተወሰደም፣ ክልከላዎቹም በእምነታቸው አስተምህሮ ላይ የተቃጣ ጥቃት አድርገው ቆጥረውታል፡፡ በተጨማሪም ክልከላው የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ተማሪዎችንም መብት የሚገድብ ነበር፡፡ ማለትም በጾም ወራት በግቢ ውስጥ የሚዘጋጅ የተለየ የጾም ማዕድ እንዳይኖር ይከለክላል፡፡ ይህ እና መሰል ጉዳዮች የሴኩላሪዝም መርሆን የሚጥስ የቅርብ ግዜ ታሪካችን ነው፡፡ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን እንደሚያሳየን የጎሳ ቡድኖች የአደጋ ስጋትና የእኩልነት ስጋት ሲሰማቸው ጉዳዩን በግላቸው ወስደው በብሄራቸው በመቧደን ተፈጠረ ያሉትን ኢ-ፍትሃዊነት በመታገል ዛሬ የምናውቃቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች አስገኝተዋል፡፡ ሃይማኖትን ወደ ፖለቲካ መጫወቻ ሜዳ ያመጣ የሚመስለው አዲሱ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ በከፍተኛ ደረጃ ያበበው የመንግስትን ተገቢ ያልሆነ የተራዘሙ እጆችን በመፍራት እና የእምነት ነፃነትን ለማስጠበቅ የመንግስት ሃላፊነት ሊሆን የሚገባውን የዜጎችን ከማንኛውም  የነፃነት፣ የሃይማኖት እና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ስጋት እንዳይሰማቸው አለማድረጉ ይመስላል፡፡

   እንደ ማጠቃለያ ይህ ጽሁፍ የምህረት ሃሳብን የመቃወም ሳይሆን ሃሳቡን ከሌላ አቅጣጫ ለማየት የመሞከር ነው፡፡ የሴኩላሪዝም መርሆን ማጠናከር ለክርክር የሚቀርብ ሃሳብ አይደለም፡፡ የሴኩላሪዝም መርሆ በአግባቡ እንዲተገበር መርሁ በሁለቱም አቅጣጫ (በሐይማኖት እና በመንግስት፣ በመንግስት እና በሐይማኖት) መከበር ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም ይህን መርህ የማጠናከር እና የመጠበቅ ግዴታ የሚወድቀው በመንግስት ትከሻ ላይ ይሆናል፡፡ ጥሩነቱ የሐይማኖት ተቋማት በመንግስት ጉዳዮች ጣልቃ ላለመግባት ሊስማሙ ይችላሉ። ነገሮች ቢከፉና የሃይማኖት ቡድኖች በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ቢሞክሩ፣ መንግሥት እንዲህ ያለውን ሃይማኖታዊ ጣልቃ-ገብነት አልቀበልም ለማለት አቅም አለው፡፡

   እንደኔ እምነት የሴኩላሪዝምን መርሆ ማስቀደም እና ማስከበር የመንግስት ተቀዳሚ ኅላፊነት ነው፡፡ የሴኩላሪዝም መርሆንም ለማስጠበቅ መንግስት አዲስ ህግ እንዲያወጣ አይጠበቅም፡፡ ከዛ ይልቅ በእጁ በሚገኘው ህገ-መንግስት ላይ የሰፈሩትን የህግ መርሆዎች ማክበሩ በቂ ነው፡፡ አዲስ የሚመጡም ሆኑ፣ ቀድሞም የነበሩ ሐይማኖት በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ የሚገባበት ዕድል በግልጽ መዘጋት አለበት፡፡ እናም መንግስት በሐይማኖታዊ ጉዳይ እና አሰራር ላይ ግልጽ ችግር ካልተፈጠረ በስተቀር ጣልቃ ገብነቱን ማቆም ይኖርበታል፡፡

   * ኡርጂ ቢሶ በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ሲሆኑ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋትን ለሁለተኛ ዲግሪያቸው እያጠኑ ነው።

   የአታሚው ማስታወሻ: ይህ ጽሑፍ ካርድ የወጣቶችን ሥልጡን እና ምሁራዊ የውይይት ልማድ ለማሳደግ “በወጣቶች የምክክር መድረኩ” ከሚያስተናግዳቸው ጽሑፎች አንዱ ነው።  በዚህ ዓምድ ለመስተናገድ ወይም ለዚህ ጽሑፍ መልስ ለመስጠት ከፈለጉ በ info@cardeth.org ላይ ኢሜይል ያድርጉልን።

Viewing 0 reply threads
Reply To: ሴኩላሪዝምን ማጠናከር፡- የማን ቀዳሚ ስራ ነው?
Your information: