በተንጋደደ የታሪክ አረዳድ ዛሬን የማፍረስ ጉዞ…

Home Forums የወጣቶች መድረክ በተንጋደደ የታሪክ አረዳድ ዛሬን የማፍረስ ጉዞ…

 • This topic is empty.
Viewing 0 reply threads
 • Author
  Posts
  • #3490 Reply

   ክሩቤል ፅጌ (ይህ ጽሑፍ በፀባዖት መላኩ እና አስራት አብርሃም ጽሑፎች ላይ የተመሰረተ መጣጥፍ ሲሆን፣ በወጣቶች የውይይት መድረክ ውስጥ ከሚስተናገዱ ጽሑፎች ውስጥ ይካተታል።)

   “ታሪክ መማሪያ እንጅ መማረሪያ ሊሆን አይገባም” – ደረጀ ገብሬ (የታሪክ ምሁር)

   ታሪክ በጊዜ ሂደት ውስጥ ይከወናል፡፡ ይህን የመነሻ ሀሳብ ተመርኩዘን፤ ታሪክን በቅርበት ለመመርመር ብንሞክር ሠውን ከታሪክ ሰሪነት ወደ የታሪክ ስሪትነት ወርዶ እናገኘዋለን፡፡ ይህን ሀሳብ እዚህ ላይ ማንሳቴ አንድምታው፤ ከሠው ልጅ በፊት ታሪክ ነበር፤ ታሪክ ደግሞ ጊዜ ነው የሚለውን ለሙግት ክፍት የሆነ ድምዳሜዬን አፅዕኖት ለመስጠት ነው፡፡ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ነፃነትን ለማስረዳት የሚጠቀሙበት ግሩም አገላለፅ አላቸው፤ “ቅፅበትን መኖር” (living a moment):: ታሪክም እንዲሁ ነው ቅፅበትን መኖር፡፡ እያንዳንዷ ቅፅበትም ታሪክ ትሆናለች፡፡ ዳሩ ግን እያንዳንዷን ቅፅበት ማስታወስ አለመቻል አንድን ኹነት/ ክውን/ድርጊት ታሪክ ከመሆን ያጎድለዋል፡፡ ታዋቂው ጀርመናዊ አንሰላሳይ፣ፈላስፋ እና ምሁር ኒቼ “እያንዳንዱ ታሪክ ሌሎች ታሪኮችን ይደብቃል” የሚለውም ለዚሁ ይመስላል፡፡ እንደውም ማስታወስ ብቻም በቂ እንዳልሆነ የሚነግሩን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ሰለሞን ተሰማ ናቸው፡፡ “የታሪክ ዘይቤ” በሚል ርዕስ ባስነበቡት ጽሑፍ ላይ “ያለፈ ነገር ሁሉ ታሪክ አይደለም” ይሉናል። አክለውም ያለፉ ነገሮች በታሪክ ዓምድ ተቀርጸው ለመኖር ሦስት መስፈርቶች የግድ ያስፈልጋሉ ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ በሁለተኛው መስፈርት ላይ ብዙም ባልስማማበትም ሦስቱ መስፈርቶች ግን ከዚህ እንደሚከተሉት ናቸው፡፡

   አንደኛው ድርጊቱ በተወሰነ ቦታና ጊዜ ለመፈጸሙ እርግጠኛ መሆን መቻል፣ ሁለተኛው ደግሞ ከሰው ሕይወት ጋር የተያያዘ መሆኑ ሲሆን ሦስተኛው ምን ያህል አስፈላጊ ነው ለሚለው ጥያቄ በቂ መልስ ሰጪ ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ እኝህ መስፈርቶች ባልተሞሉበት ግን አንድ ድርጊት ታሪክ ሊባል አይቻልም የሚል ጥቅል ሀሳብ ያለው ነው፡፡ የሚረሱ ክውኖች እንዳሉ ሁሉ በአንፃሩ ደግሞ አይረሴ የሆኑ ቅፅበቶች ዘመንን ተሻግረው ከትውልድ ትውልድ እየተቀባበሉ ህያው ሆነው ይዘልቃሉ፡፡ ስለዚህ የታሪክ መጉላት እና መፍዘዝ ያለና የነበረ ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ በሌላ መንገድ ደግሞ ከቅፅበቶች አይረሴነትም ባሻገር የጎለበተ የሥነ-ፅሁፍ፣ የሥነ-ቃል፣ የባሕል መኖር እንዲሁም ታሪክ ሰሪው ማሕበረሰብ ከእርሱ ውጭ ያለው ማህበረሰብ ጋር ያለው የተግባቦት ልክ አንድን ታሪክ ሊያጎሉት ከሚችሉ አላባዊያን (elements) መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡

   አሁን ላይ በሀገራችን የሚስተዋለው ታሪክን አንሻፎ ወይም አበቅ-የለሽ አድርጎ የመረዳት አባዜ፤ ታሪክን መሠረት ካደረገ ፖለቲካዊ ትንተና ጋር ተዳምሮ ወደ ማይታረቁ ታሪክን ማያ ንፃሬዎች (perspectives) አዘቅት ውስጥ ከቶናል፡፡ ይህም ብዘሃ-ንፃሬ ታሪካዊ ብያኔ ለመስጠት ግድ የሚለንን ታሪካዊ እውነት ፍለጋ ላይ እንዳንጠመድ አስንፎናል (ምንም እንኳን አሁንም ብያኔ ከመስጠት ባንቦዝንም)፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይከልባችሁ ሲለን ደግሞ ይህ የተካረረ እና ዋልታ-ረገጥ የታሪክ አረዳድ እንደህዝብ አቅፎ በሚይዘን የሀገረ-መንግስት ግንባታ ላይ መበርታቱ ለከፍተኛ ሀገራዊ አንድነት መኮሰስ እና እንደ ሀገር የመቀጠል ዕጣ-ፈንታ ላይ ጥላውን አጥልቷል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆን ዘንድ አንድ መምህሬ በክፍል ውስጥ ሲያስተምር የሰጠንን ምሳሌ ላንሳ፡፡ “ወደ ሰሜን የአገራችን ክፍል ስትሄዱ የእዛ አካባቢ ማህበረሰብ ለቤተ-መንግስት የቀረበውን ሁሉ የእኔ ወገን ነው ሲል ትታዘባላችሁ፡፡ በአንፃሩ ወደ ደቡብ ስትመለሱ ደግሞ ቤተ-መንግስት ዙሪያ የቀረበውን ወገኑን ከእኔ አይደለህም ከማለትም አልፎ ጀግናውንም የሚክድ ማህበረሰብን ታያላችሁ” ይላል፡፡ ይህ የሚያስገነዝበን በዘመናዊ ሀገረ-መንግስት ግንባታ ላይ የተደነቀረው የተዛባ የታሪክ አረዳድ እና አተራረክ ጦስ የፈጠረብን ውዥንብር ነው ባይ ነኝ፡፡ እንደ ወቅታዊ እና አንገብጋቢ ጉዳይ ይህን በይቅደም አነሳሁት እንጅ የታሪክ አረዳዳችን ከመካከለኛውም ዘመን የሚመዘዝ በሐይማኖት እና በፖለቲካ የተዋጠ የተጣመመ የታሪክ አረዳድንም ማንሳት ይቻላል፡፡

   በጊዜው ያልነበረን፣ ከማንበብ እና ከመጠየቅ ጋር የተፋታን ትውልድ የኋላ ታሪኩን በማወደስ አልያም በማኳሰስ ሥነ-ልቦናዊ ውቅሩን መለዋወጥ ሙዝ የመላጥ ያክል ቀላል የሆነበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ችግሩም እዚህ ላይ ነው እንዲህ በቀላሉ የሚለዋወጥ ሥነ-ልቦናዊ ውቅር አንዱን አስኮርፎ አንዱን ጮቤ የሚያስረግጥ፣ አንዱን ከሰውነት ከፍ ሲያደርግ አንዱን ደግሞ ዝቅ አድርጎ የሚያሳየን ስለሚመስለን ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ የታሪክ መዛነፎች ከምን የመነጩ እንደሆኑ መመርመር አግባብነት አለው፡፡

   ዝንፈተ ምክንያት ፩:- በሀገራችን ታሪክ የምንገነዘብበትን መንገድ በሁለት ጎራዎች ከፍለን ለመመርመር ብንሞክረስ?

   አንደኛው ታሪክ የአጋጣሚ ክስተቶች/ድርጊቶች ውጤት ነው የሚለው አብዛኛውን የታሪክ አጥኝዎች የሚያግባባ እና በኦፊሻል ተቀባይነት ያለው የታሪካዊ ክስተቶች አረዳድ መንገድ ነው፡፡ ይህን መሰረት አድርገው የሀገራችንን ታሪክ የሚፅፉ የታሪክ ፀሀፊዎችን የቤተ-መንግሥት ታሪክ መዝጋቢዎች (Establishment Historians) ብለው ይጠሯቸዋል። ለዚህ መጠሪያቸው ምክንያት ደግሞ ታሪክን ለመፃፍ እንደ ምንጭነት የሚጠቀሙበት የነገስታት መዋዕለ-ዜናዎች፣ ገድላት እንዲሁም የጉዞ ማስታወሻዎች መሆናቸው ከቤተ መንግስት ውጭ ያለውን ታሪክ እንዳያዩ ጋርዶቸዋል በሚል ነው፡፡ ይህ የታሪክ አረዳድ በሀገራችን ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች ማለትም ለምን አማርኛ ቋንቋ የቤተ-መንግስት ቋንቋ ሆነ፣ የሰሜኖች (በተለይም አማራ እና ትግሬ) የአለባበስና አመጋገብ ባሕል የአኗኗር ዘይቤ ለምን ጎልቶ መውጣት ቻለ ለሚሉት እና መሰል ጊዜ-ወለድ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት የሚሞከርበት የታሪክ አረዳድ መንገድ ነው፡፡

   ሁለተኛው የታሪክ አረዳድ መንገድ ደግሞ የለም ታሪክ እንዲሁ የአጋጣሚዎች ውጤት ሳይሆን የተቀነባበረና የታሰበበት ክንውኖች ውጤት ነው የሚለን ሲሆን ሴራዊ የታሪክ ትንተናን የተንተራሰም ጭምር ነው፡፡ የዚህ ዋና ጭብጥም ደግሞ ኢትዮጵያ የምንላት ሀገር እሳቢያዊ ምስል ብዙኀንነታችንን ደብቆ የአንድን ብሄር ቋንቋ እና ባህል ያነገሰ ነው እንዲህም እንዲሆን በየጊዜው የነበሩ የአገር መሪዎች የህዝቡን ስነ-ልቦናዊ ውቅር አሳምነውም ይሁን ገርፈው (by stick or carrot) ጠፍጥፈው ሰርተውታል የሚል ነው፡፡ በዚህ የሚስማሙ የታሪክ ፀሀፊዎች ደግሞ የዘውግ ታሪክ ጸሐፊዎች ወይም Ethno Nationalist ይባላሉ፡፡ እነዚህ ታሪክ ጸሐፍት ምክንያትም የታሪክ ሽሚያ እንደተጀመረም ይነገራል፡፡

   አዳዲስ የታሪክ አረዳድ መንገዶች ከ 1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ በተለይም የዋለልኝ የብሄር ጥያቄ ንባብ በኋላ የተፈጠሩ ሳይሆን ስም የወጣላቸው ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ በእኔ እይታ ልክ፤ የኢትዮጵያ የታሪክ አረዳድም ይሁን አተራረክ በሦስት ሂደቶች ውስጥ ያለፈ ነው፡፡ እነርሱም እውነት/ውሸት፣ ምርጫ፣ ፃፉ/ክፍት ቦታውን ሙሉ/ ናቸው።
   ከተማሪዎች ንቅናቄ በፊት የነበረው የታሪክ አተራረክ እውነት ወይንም ውሸት በሚል አጭር መልስ የሚዘጋ ነገር የነበረ ይመስለኛል፤ በሌላ አገላለፅ አጨቃጫቂ የታሪክ እይታዎች አልነበሩም፡፡ መስማማት ወይም አለመስማማት፤ ያልተስማማውም አለመስማማቱን ይይዛል እንጅ የሚስማማውን ታሪክ ልፈልግ ወይም ልፍጠር አይልም፡፡ የተማሪዎችን ንቅናቄ ተከትሎ ደግሞ ወደ ምርጫ ይዘት ተቀየረ፤ እዚህም ላይ ነው መልከ ብዙ የታሪክ ማያ መነፀሮች የተፈበረኩ አልያም እንዳሉ እውቅና የተሰጣቸው፡፡ እንደ ምሳሌ የሀገረ-መንግስት ግንባታን ታሪክን ብንወስድ፤ መረራ (ፕ/ር) እንደሚነግሩን ሦስት አይነት ዋና ዋና ታሪክን ደጀን ያደረጉ ፖለቲካዊ እይታዎች እንዳሉ ይጠቁሙናል፡፡ እነሱም አገር-ማቅናት (nation state-building thesis)፣ የብሔርና የመደብ ትንተና ላይ የተመሠረተ (class and ethnic analysis) የብሄር ጭቆና ( national oppression thesis) እና ውስጣዊ ቅኝ አገዛዝ (Colonization thesis) ናቸው፡፡ ከዚህም ጊዜ በሗላ ታሪክን እንደ ትግል ስልት መጠቀምና የሚፃፍበት አላማና አውድ ተቀይሮ በፖለቲካ የተቀለመ ታሪክ (Politicized history) ላይ መደናቆር የጀመርነው፡፡ ሦስተኛ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምናልባትም ከ ሦስት አስርት አመታት ወዲህ የተጀመረው የፈጠራ ታሪክ ወይንም ታሪካዊ ክፍተቶችን መሙላት ነው፡፡ ስለዚህም የታሪክ እውነት ላይ የመድረስ እድላችን 50 በመቶ ወደ 25 እና 30 በመቶ እዲሁም ከዛ በታች አሽቆልቁሏል፡፡

   ዝንፈተ ምክንያት ፪. ስለ ተሳተው ታሪክስ…?

   በመጀመሪያ የታሪክ ፀሐፊዎቻችንን ለሰሩት ስራ ምስጋናም ክብርም አጉዳዮች በመሆናችን እያፈርኩ፤ አሁን ላይ ስለ ታሪክ እንድናወራም እድል የፈጠሩልን እነሱ መሆናቸውን ግን አብዛኞቻችን ዘንግተናልና እሱን ላስታውሳችሁ እወዳለሁ፡፡ በአለምም ይሁን በእኛ ሐገር የሀይል ታሪክ ይጎላል፡፡ የጥቂት ሰዎች ታሪክ፤ ለዛውም በትረ-ስልጣን የጨበጡ እና በእነርሱ ዙሪያ ያሉ ሰዎች ታሪክ ብቻ፡፡ እኚህን መሰል ታሪኮች በእኛ አገር እገሌ እገሌን ገደለ ወይ አስገደለ፣ገበረ ወይ አስገበረ ከሚሉ የጊዜው ፖለቲከኞችም የታሪክ ፀሀፍት ከሚያራግቡት ደረቅ የፖለቲካ ታሪክ ውጭ የማህበረሰቡን የእርስ በእርስ መስተጋብር፣ የባህል እና የቋንቋ መወራረስ፣ ሐዘንና ደስታን የመጋራት፤ ክሬም የሆነው የታሪክ ክፍል ስተውታል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ የጊዜው ዘውጌ የፖለቲካ ልሂቃን፤ ማደናገሪያ የታሪክ ክስተትን ፍለጋ፤ ግለሰባዊ የሀይል አሰላለፍን ብቻ ነጥሎ ማጥናት እና ታሪክ ፀሀፊዎችንም በእነርሱ አምሳል በመቅረጽ፤ ማህበረሰባዊ ታሪኮቻችንን ትኩረት በማሳጣትንም ነው፡፡ ለዚህም ነው ደረቅ ዶቦ የሆነውን የፖለቲካ ታሪክ ያለ ክሬም (ማህበረሰባዊ ታሪክ) ውጠን ቃር ቃር የሚለን፡፡

   ዝንፈተ ምክንያት ፫ :- ጊዜን አግላይ የታሪክ ትንተና በጊዜ ሂደት ውስጥ የትላንትን ስራ ትክክል የሚደርጉ፣ አጃኢብ የሚሰኙ በአንፃሩ ደግሞ ከስህተት የሚያስቆጥሩ ሀገራዊም ዓለም-አቀፍዊ መለዋወጦች አሉ፡፡ እንደ ምሳሌ የላሊበላ ቤተ-ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን አሰራር አሁንም ድረስ ግርምትና መደነቅ የሚጭርብን ጥንት ከመሰራቱም በተጨማሪ አሁንም አለም ላይ ላሊበላን የሚስተካከል በስነ-ህንፃ ጥበብ የላቀ ሌላ አለመኖሩ ነው፡፡ በአንፃሩ የቀደሙ የሀሳብ ልዩነቶችን መፍቻ የነበሩት የእርስ በእርስ ግጭቶችና ደም መፋሰሶች፤ አሁን አለም ላይ እንደ አማራጭ የማይቀርቡ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በምትኩም ከጦር ሰበቃ ይልቅ የሀሳብ ፍጭት፣ ድርድርና ምክክር ያስቀድማሉ፤ ይህንንም የሚያሳልጡ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ጠንካራ ተቋማት ያሉበት የዘመን ዳራ ላይ እንገኛለን፡፡ በጠቅላላው ጦርነትን ትላንት እንደ ልማዳዊ ግጭት መፍቻ መንገድ ዛሬ ላይ ደግሞ እንደ ነውር ያስቆጠረው ጊዜ ነው፡፡ እናም የትላንትን ታሪክ የዛሬ ጫማ ውስጥ ቆሞ የመመልከት ችግር (Present minded) መሆን እና ትላንትን መውቀስና የታሪክ ብያኔ መስጠት ሌላው የታሪክ ዝንፈት ምክንያት ነው፡፡

   የአ.አ.ዩ የታሪክ ተማሪ ሰለሞን ስዩም ከአዲስ ማለዳዋ ልዲያ ተስፋዬ ጋር ባደረገው ቆይታ፤ የኢትዮጵያን የታሪክ አጠቃቀምና አረዳድ በተመለከተ ሲናገሩ፤ “ታሪክን ለነገ ብንጠቀም አንድ ነገር ነው፤ ነገር ግን ትላንት ለመኖር ነው እየተጠቀምንበት ያለነው” ይላሉ። ታሪክን ለነገ ስንጠቀም መማሪያ ይሆናል የተገላቢጦሽ ደግሞ ያለፍነውን ትላንት ለመኖር ስንከጅልበት ታሪክ መማረሪያ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ላይ የቤት ስራው የረሳ ሰነፍ (እንዲሰንፍ የተሰራበት) ትውልድ ሲታከልበት ደግሞ የትላንትን ታሪክ መንፈስ ወርሶ ዛሬውን ሲያማርር “ዳውን ዳውን ምኒሊክ” በትላንቱ ሲኩራራ ደግሞ “ምኒሊክ ዛሬም ንጉስ ነው” በሚሉ ቅራኔዎች የታጀለ ደስታንም ሀዘንንም ለመጋራት ያልታደልንበት ጊዜ ላይ ያደርሰናል፡፡

   እንደ መፍትሔ
   ታሪካዊ እውነትን በጥብቅ መሻት :- ታሪክን እንዳመቸን መቀበል እና መግፋት ይቆም ዘንድ፣ መጀመሪያ ላይ እንዳነሳነው ታሪክ በጊዜው እና በቦታው መፈጠሩን ማረጋገጥ እውነቱንም ለህዝብ መግለጥ እንደ ሀገር ብሄራዊ የታሪክ አጥኝዎች ቡድን አቋቁሞ ሊሰራበት ይገባል እላለሁ፡፡ በእኔ እምነት ታሪክ እንደ ቁጥር በሰሜን ስናየው ዘጠኝ በደቡብ ደግሞ ስድስት እያልን የምንነታረክበት የእኔ እውነት ያንተ ሐሰት እያልን የምንቧጨቅበት አይደለም፡፡ የታሪክ አጥኝዎች እዚህ ላይ የምንቆምበትን ትክክለኛ አቅጣጫ ማመላከት ሙያዊም ሞራላዊም ግዴታ አለባቸው፡፡

   ዳሩ ግን ነገሩ ታሪካዊ እውነትን በመግለፅ የሚቋጭ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት የትኛውም ማህበረሰብ እውነታውን ለመቀበል የሚያስችለው ስነ-ልቦናዊ ዝግጅት ሊኖረው ይገባል፡፡ አውቀዋለሁ ከምንለው ተቃራኒ የታሪክ እውነት ጋር ልንፋጠጥ እንችላለን እናም ታሪክ እውቀት እንጅ እምነት እዳልሆነ መገንዘብ ተገቢነት አለው፡፡ታሪክን ከፖለቲካ ጥሬ እቃነት ማላቀቅ፡- በፖለቲካ የተቀለሙ ታሪኮችን መለየት እና በታሪክ እውነታ መተካት ከማህበረሰብም ትውስታ መፋቅ (Depoliticization of history)፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው ነገር የተረጋገጡ የታሪክ እውነታዎችን ለማሕበረሰቡ ማስተማር እና ማሳወቅ፤ ታሪክን አንሻፈው ተጠቅመው የፖለቲካ ፈረስን በህዝብ ላይ ሽምጥ መጋለብን ለሚመኙ የታሪክ ወንበዴዎች ምትክ-የለሽ ልጓም ነው፡፡ ማንሰላሰል የተሳናቸውንና ሀሳብ ሲያልቅባቸው ከታሪክ ሂደው ለሚለጠፉ ፖለቲከኛ ተብዬዎቹንም ለማረቅ ሁነኛ መፍትሔ ይመስለኛል፡፡

   እንደ ማጠቃለያ:- ታሪክን ከመሠረታዊ አላማው በማሸሽ፤ ለአምና እና ታችአምና ልቅሶ፤ ዛሬ ላይ ሙሾ እናውርድበት ካልን ከባድ ዋጋ ያስከፍለናልና ከታሪክ መማሩ ላይ ብንበረታ እጅጉን መልካም ነው፡፡ ታሪካዊ እውነታወችን መመርመር፣ ማመን፣ መቀበል፣ እናም ማዎቅ ተቀራራቢ የታሪክ ይዘት ግንዛቤ ውስጥ ያቆየናል፡፡ ይህም የሳሳ ብሔራዊ ክብራችንን ከውድቀት አፋፍ መለስ፤ ከአላስፈላጊ ክፍፍልና የእርስበእር መናከስም ጋብ ያደርገናል፡፡ እናም የምናስውበው “ዛሬ” ያለን ሰዎች ምኑንም ልንቀይር ለማንችለው “ትላንት” እያላዘለን ጊዜና ጉልበታችንን በዋዛ አናባክን።

Viewing 0 reply threads
Reply To: በተንጋደደ የታሪክ አረዳድ ዛሬን የማፍረስ ጉዞ…
Your information: