ብሔርተኝነት እና ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ፡ ኢትዮጵያን የሁሉም ኢትዮጵያውያን አገር ማድረግ

Home Forums Waltajjii Dargaggoota ብሔርተኝነት እና ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ፡ ኢትዮጵያን የሁሉም ኢትዮጵያውያን አገር ማድረግ

 • This topic is empty.
Viewing 0 reply threads
 • Author
  Posts
  • #3463 Reply

   በኢዶሳ ደገፌ ጉታ

   የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ግዛት በዳግማዊ አጼ ምኒልክ (እ.ኤ.አ 1889-1913) በኃይል የመመስረቷ እውነታ በብዙ ዘርፍ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሆነችን ኢትዮጵያን ዛሬ ላይ ለመገንባት የምንቸገርበት አጣብቂኝን አስከትሏል። ብፅዕት አለሙ “ኢትዮጵያ የማን ናት” በሚል ርዕስ በፃፈችው ፅሁፍ ላይ ባነሳቻቸው አንዳንድ አስተያየቶች እስማማለሁ፤ በተለይም “አግባብ ባለው ሁኔታ ያልተመራው የብሔር ፌደራሊዝም የብሔር ጽፈኝነትን በማባባስ ለፖለቲካዊ ግጭት እና ሌሎች ስር የሰደዱ ችግሮች መንስኤ ሆኗል” የሚለውን ሀሳብ እጋራለሁ። እንዲሁም አሁን ላለው ቀውስ መፍትሔው ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር መሆኗን ከመቀበል ጋር በቅርበት የተቆራኘ ነው  እንዲሁም “እኛ ይህን እስካልተቀበልን ድረስ ወደፊት መጓዝ አይቻልም” በሚለው መከራከሪያዋ እስማማለሁ፡፡

   የመነሻዬ ነጥብ የብፅዕት ጹሑፍ ግድፈቶች እና የዘለለቻቸው ጉዳዮች ላይ ተመስርቶ እንደሚከተለው ይቀርባል። አንደኛ፣ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ግዛት በዳግማዊ አጼ ምኒልክ  መመሥረት እኛ ያለንበት እንቆቅልሽ ማዕከል ቢሆንም፣ እሷ ትኩረት አልሰጠችውም። የዳግማዊ ምኒልክ ወደ ደቡብ መስፋፋት ተቃውሞ ገጥሞታል። ለዚህም አስረጅ የሚሆነውበኋላ በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ-መንግስት ማብቂያ ላይ (እ.ኤ.አ 1930-1974) እነዚህ በአጼ ምኒልክ በሃይል የተያዙ የተጨቆኑ ቡድኖች ብሔራዊ የራስን ዕድል በራስ የመወሰንጥያቄን አንስቷል። የሀገር ባለቤትነትም ቀድሞ በተከሰቱት ኢ-ፍትሐዊነቶች ተጽዕኖ ይደረግበታል። ከዚህ በፊት የተፈጸሙ ግፎች በጥንቃቄ መታረም አለባቸው። ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት እያንዳንዱን ህብረተሰብ እና ያሏቸውን የይገባኛል ጥያቄዎች ማጥናት ያስፈልጋል።

   በተጨማሪም ጥናቱ ገለልተኛ መሆኑን ለማረጋገጥ የባለሙያዎችን እና የአሠራር ዘዴዎችን በጥንቃቄ መምረጥ ያስፈልጋል። ይህ የኢትዮጵያውያንን የሀገር ባለቤትነት ስሜት እየገደበ ያለውን ያለፈውን ኢ-ፍትሐዊነት ለማስተካከል ነው። ሆኖም፣ ብፅዕት ይህንን በፖለቲካ የተጫነውን ታሪካዊ ሂደት ብዙም አልተመለከተችውም​​። ነገር ግን፡ ለብሔሮች ከመጠን በላይ መከፋፈል እና በብሔረሰቦች መካከል ለሚነሱ ግጭቶች የብሔር ፌዴራሊዝምን ተጠያቂ አድርገዋለች። ያም ቢሆን እንኳን በስርዓቱ መልካምነት እና በኢሕአዴግ እጅ የተፈጸሙ የስርአቱ አፈጻጸም ውድቀቶችን መለየት ይገባል።

   በጽሁፏ ውስጥ ብፅዕት እንደ ጠቆመችው የአገሪቱን ብዝሃነት በተሻለ ሁኔታ እንዴት ማስተዳደር እንደሚቻል አማራጮችን ካቀረቡ ብዙ ሰዎች የሁለት ኢትዮጵያውያንን አመለካከት ብቻ ያካተተች ሲሆን እነሱም ዋለልኝ መኮንን እና ኢብሳ ጉተማ ናቸው። ለምሳሌ፣ “እንደ ኤርትራ ሁሉ የኦሮሚያም ጥያቄ ከቅኝ ግዛት ነጻ የመሆን ነው” ብለው የሚከራከሩት የፕሮፌሰር አሰፋ ጃለታን ክርክር ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን። በዚህ አኳኃን በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ለመገንባትም ሆነ የብሔረሰብ ጥያቄን በአግባቡ ለመቅረፍ መፍትሔ ሊገኝ አይችልም።

   በዚህ ረገድ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በበኩሉ “አብላጫውን ማህበረሰብ በማግለል እና በአንድ ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ እና ማዕከላዊነትን ለማስወገድ ተስፋ ማድረግ እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው” ሲሉ ተከራክረዋል። ለኢትዮጵያ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የጋራ አጀንዳ ለማዘጋጀት የሚያስችለው በልዩነት ውስጥ ያለውን የአንድነት መርህ መቀበልን አጽንዖት በመስጠት በሐቀኝነት እና በተጠናከረ ሁኔታ መከተልን አብዝተው ይመከራሉ። የመረራ እይታ ለዘብተኛ ነው ማለት ይቻላል።

   ኢትዮጵያዊ ለመሆን የሚሟሉ ሁኔታዎች ካሉ፣ አንዳንድ ግለሰቦች እና ቡድኖች በአሁኑ ጊዜ ሊደርሱበት የሚሞክሩ አይነት መሆኑ መታወቅ አለበት። የኢብሳ ጉተማ ጥያቄ “ኢትዮጵያዊ ማን ነው” የሚለው ጥያቄ በኢትዮጵያዊነት እና በብሔረሰብ መካከል እንደተጫነ እርስ በእርስ የሚወሰን ምርጫ ብቻ ሆኖ መታየት የለበትም። ይልቁንም፣ አንዱ ከሁለቱም ጋር ሊጣመር ይችላል፣ እና እያንዳንዳቸው የሌላው የጋራ ህብረት ሊሆኑ ይችላሉ። ያ ማለቂያ የሌለው የራስ-ግንዛቤዎችን እና ማንነቶችን (እንዲሁም በጊዜ እና በቦታ በመረጡት መለወጥ የሚያስችል ሲሆን)፣ በመሆኑም ጽንፈኝነትን እና ግጭትን ይቀንሳል።

   እውነት ነው በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ማንነት በፖለቲካ ውስጥ በመግባት፣ ተፎካካሪ ብሔርተኝነት ጫፍ ላይ ደርሶ በሥልጣን ፖለቲካ፣ በወታደራዊነት እና በመገለል ራሱን እስከመግለጽ ደርሷል። ሆኖም በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ላይ ያለውን ቀውስ ለመፍታት በምናደርገው ሙከራ አክራሪነት የሚለውን ቃል መጠቀም የለብንም። ለብሔረሰቦች የሚያዋርዱ ስሞች መጠቀም እና ልሂቃንን “ከሌላ ቡድኖች የተውጣጡ” የሚል ቅጥያን መጠቀም ሰላማዊ መፍትሔን ለማምጣት የማይጠቅም እና ነገሮችን የበለጠ አስቸጋሪ እንዲሆን ያደርገዋል። የሚገድሉ ሳይሆን የሚፈውሱ ቃላትን መፈለግ አለብን።

   ብፅዕት መሬት በኢትዮጵያ ውስጥ የግጭቶች ማዕከል እንደመሆኑ መጠን የመሬትን ጥያቄ አንስታለች። ይህ ምናልባትም ማህበረሰቦች በአንዳንድ ግዛቶች ላይ በቋሚነት መስፈር እንደሚያስፈልጋቸው ሊያመለክት ይችላል። ሆኖም፣ በዚህ ነጥብ ላይ የበለጠ አልገፋችም፣ የመሬት ባለቤትነት እና የክልል ግዛት አሰጣጥ ተለዋዋጭነት ላይ የክርክሮችን እና ውይይቶችን አስፈላጊነት በማጉላት አላሳየችም።

   እርግጥ ነው፣ ብፅዕት እንዳስቀመጠችው ሁሉም ብሔረሰቦች በመንግስት ጉዳዮች ውስጥ በእኩል የሚሳተፉበትን እውነተኛ ሀገሬ መንግስት ለመፍጠር በሚደረግ ሙከራ የአገር-በቀል ዴሞክራሲያዊ መርሆችን መጠቀም አለብን። ብዙሃኑ የሚስማሙበትን አገር-በቀል ተቋማትን በጥንቃቄ መምረጥ ስለሚያስፈልግ ይህ ቀላል ተግባር አይደለም። እኔ እንደ አድዋ ድል ያሉ ታሪካዊ ድሎችን ውስጣዊ አለመግባባቶችን ለመቅረፍ ሊያገለግሉ ይችላሉ በሚለው መከራከሪያ ነጥብ አልስማማም። ይልቁንም ህዝቡን ከውጭ የሚመጡ ስጋቶችን ለመመከት ለማነሳሳት የሚስችሉ ናቸው።

   የኢትዮጵያ የማን እንደሆነች (የኢትዮጵያ ባለቤትነት) እና በውስጡ የሚያካትተው በሕገ-መንግስቱ በዝርዝር ተካትቶ ይገኛል። በተለያየ ወቅት በተደረጉት ተቃውሞዎች እና ከዚያ ወዲህ በነበረው የፖለቲካ ሂደቶች ወቅት ለተነሱት ጥያቄዎች መፍትሄ ለመስጠት በፖለቲካ ንግግር ላይ የተመሰረተ ሕገ-መንግሥት የማሻሻል ተፈላጊነት ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው። ሕገ-መንግስቱ ‘የበለጠ ፍፁም’ እንዲሆን እና ከአሁኑ እና ከመጪው ትውልድ ፍላጎቶች እና ምኞቶች ጋር የሚስማማ እንዲሆን መደረግ አለበት። ይህ መሆን ያለበት በሕገ-መንግስታዊ ክለሳ ውስጥ የተካተቱ እና የተገለሉ ድንጋጌዎችን ተከትሎ እና በሕዝብ ፍላጎት ላይ በመመስረት መሆን አለበት።

   ሁሉም የሕዝብ ሕይወት ልኬቶች ተፈትነው በመወያያነት ይቀርቡ የነበረው በብሄር ፖለቲካ እይታ ውስጥ ነበር ለማለት ይቻላል። በ“እኛ” እና “እነሱ” በሚል እይታ ላይ ያተኮረ አግላይ ብሔርተኝነት እና የአስተሳሰብ ሁኔታ ሊፈታ የሚችለው በአገር አቀፍ ግንዛቤ ወይም በውይይት ብቻ ነው። የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እና የሲቪል ማህበራት፣ ሽምቅ ተዋጊዎችን፣ ምሁራን እና ሚዲያዎችን ያካተተ ሰፊ እና ተጨባጭ ክርክር ዘላቂ ሕገ-መንግስት ለማጽደቅ፣ ለመላው ህብረተሰብ ተቀባይነት ያለው እና ከዴሞክራሲያዊ መመዘኛዎች ጋር የሚስማማ ለማድረግ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነው። ለስኬታማ የክለሳ ሂደት ሕጋዊነት እና የወደፊቱን ሕገ-መንግሥት የባለቤትነት ስሜት በተመለከተ ብሔራዊ መረዳት እንዲኖር መስራት ሊበረታታ ይገባል። በጣም ጥብቅ በሆነ የጊዜ ገደቦች ውስጥ በእጅ የተመረጡ ‘የሕዝብ ተወካዮች’ ጋር የሚድረግ ምክክር መወገድ አለበት። ሕገ-መንግስታዊ መረጋጋት በአጠቃላይ ለአገሪቱ መረጋጋት አስፈላጊ አካል ነው። እናም ማንም ቢሆን የአሁኑን የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት አዲስ ሕገ-መንግሥት እንደ “ፈጣን ማስተካከያ” አድርጎ መቀበል የለበትም። ይህ ሂደትም በከፍተኛ ደረጃ የግልጽነት እና አካታችነት ደረጃን እንዲይዝ መደረግ አለበት። ስለሆነም በዚህ እና በቀጣይ ሕገ-መንግስቱን ለማሻሻል በሚደረገው ሙከራ ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ሲቪል ማህበረሰቡ እና ሰፊው ህዝብ፣ የተደረጉ ለውጦችን ማወቃቸውን ማረጋገጥ ይመከራል።

   በኢትዮጵያ ውስጥ የሚጋጩ ፓርቲዎች ከመሸጉበት ወጥተው፣ ትልቁን ምስል ማየት፣ አቋማቸውን እና አመለካከታቸውን እንደገና መመርመር፣ አሉታዊ ዘመቻቸውን ማቆም፣ የህዝብ ግጭትን ለፖለቲካ ትርፍ ከማድረግ መቆጠብ እና መደራደር፣ በድርድር ውስጥ አማራጭ መኖሩን መቀበል እና ሽንፈት አለመሆኑን መረዳት አለባቸው። በኢትዮጵያ ሁኔታ ውስጥ፣ ሁሉም ወገኖች የተዋጊነትን መንፈስ “ሁሉንም አሸነፋለሁ ወይም እሸነፋለሁ” የሚለውን ዘለቄታዊ ያልሆነን አመለካከት መተው አለባቸው። በቅን ልቦና ያልተከናወነ ድርድር መተማመንን መሸርሸሩን እና እድገትን ማገዱን ስለሚቀጥል፣ ሁሉም ወገኖች ለመደራደር- ሰጥቶ መቀበልን መርህ ማድረግ አለባቸው። ስለዚህ፣ ለድርድር ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ተፎካካሪ ወገኖች የሚጠቀሙበትን የአነጋገር ሁኔታ እና ቋንቋ እንደገና ማጤን አለባቸው።

   የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ከመጀመሩ በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ ውይይት እንዲደረግ እመክራለሁ። የጋራ መግባባት ግንባታን ቅድሚያ መስጠት አለብን። በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ይሠራል። የስኮትላንድ ነፃነት ሕዝበ ውሳኔ እና የደቡብ ሱዳን የመገንጠል ጉዳዮች የአካታች ውይይት አለመኖርን ያንፀባርቃሉ። ለዚህም ነው በጋራ መግባባት ላይ መድረስ አለብን ብዬ የምመክረው። የሕገ መንግስቱ አንቀጾች ማሻሻያ ግለሰቦች እና ሰፊው ህዝብ በአስፈላጊነቱ ከተስማሙ በኋላ በባለሙያዎች አማካይነት መከናወን አለበት። ብዙ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጾች ዝርዝር በሕግ ይወሰናል ይላሉ። ይህ በማሻሻያው ሂደት ውስጥ የባለሙያዎችን ተሳትፎ አስፈላጊነትን ያንፀባርቃል። በቅርቡ በትግራይ ክልል የምርጫ ቦርድ መመስረት ከእንዲህ ዓይነቱ ውዝግብ ለመውጣት የባለሙያዎች ክርክር አስፈላጊነቱን ያመላክታል።

   ታሪካዊ ያልተመጣጠነ ግንኙነቶችን ለማስተካከል እና ሚዛናዊ ለማድረግ የሚያስችል ያልተማከለ እና ዴሞክራሲያዊነት በእውነቱ መከናወን አለበት። ከቀደምት መሪዎቹ የወረሰው የገዥው ፓርቲ ከላይ ወደታች ያለው አቀራረብ እንደገና መታየት አለበት። በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውስጥ አካባቢያዊ ገዥነትን የሚያካትት እውነተኛ ያልተማከለ አስተዳደር ተግባራዊ መሆን አለበት። በመላ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ውስጥ እኩል ያልሆነ ልማት እና በተለያዩ ቡድኖች የተያዙ የጋራ ትውስታዎች ሁሉ የመፍትሔ ሃሳቦችም እንዲሁ በመፍትሔ ፍለጋ ሂደቶች ውስጥ መታሰብ አለባቸው።

   በኢትዮጵያ ያለው የመሃል-ጠረፍ ግንኙነት መሻሻል አለበት። የተገለሉ በጠረፍ የሚኖሩ ሰዎችን (በተለይም አርብቶ አደሮችን እና ከፊል አርብቶ አደሮችን) አሳንሶ የማየት ባህል መቆም አለበት፤ ይህንንም ለማረም ጥረት መደረግ አለበት። ለማጠቃለል፣ የሁላችንም የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር መንግሥት፣ አማጽያን፣ ሲቪል ማኅበራት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ተደማጭ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሚመለከታቸው ሁሉ፣ አማራጮቻቸውን፣ ፖሊሲዎቻቸውን እና ድርጊቶቻቸውን በሐቀኝነት እና በድርድር መንፈስ እንደገና የማጤን ጊዜው አሁን ነው።

Viewing 0 reply threads
Reply To: ብሔርተኝነት እና ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ፡ ኢትዮጵያን የሁሉም ኢትዮጵያውያን አገር ማድረግ
Your information: