ኅዳጣን ቡድኖች እና በማኅበረ-ፖለቲካ ሥርዓቱ የአካታችነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

Home Forums የወጣቶች መድረክ ኅዳጣን ቡድኖች እና በማኅበረ-ፖለቲካ ሥርዓቱ የአካታችነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

 • This topic is empty.
Viewing 0 reply threads
 • Author
  Posts
  • #3640 Reply

   በፀጋዬ ደጀኔ ዳባ*

   ኅዳጣን(አናሳዎች) የሚለው ቃል በማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ አከራካሪ ከሆኑትና በልዩ ልዩ አውዶችና ይዘት ውስጥ የተለያዩ ዓይነት ትርጉሞች ካሏቸው ቃሎች መካከል አንዱ ነው። ቃሉ በአብዛኛው በአንጻራዊነት አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸውን ቡድኖች ከመግለጽ ጋር የሚያያዝ ነው። ይሁንና፣ የቃሉ ፖለቲካዊ ዕሳቤ አንድ የማኅበረ-ፖለቲካ ምህዳር እንዴት በአንድ በተወሰነ ቡድን ተጠቃሎ ተያዘ የሚለውን ያጠቃላል። በተጨማሪም፣ በጽንሰ-ሀሳብ ደረጃ ኅዳጣን የሚለው ሐሳብ በአንድ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሥሪት ውስጥ “በሚገባው መጠን አለመወከል”፣ “መገለል” እና “መጨቆን ወይም ጭቆና” የሚሉትን ስር የሰደዱ እሳቤዎች ያካትታል፡፡

   በኢትዮጵያ ያሉ ኅዳጣን ቡድኖች በሦስት ሰፊ ምድቦች ማለትም፡- በክልላቸው ያሉ ኅዳጣንከክልላቸው ውጪ ያሉ ኅዳጣን” እና ግሉላን (የተገለሉ) ኅዳጣን ተብለው ሊከፋፈሉ ይችላሉ። በክልላቸው ያሉ ኅዳጣን የሚባሉት በርስት መሬታቸው የሚኖሩ ነገር ግን በሕዝብ ብዛታቸው ምክንያት በክልሉ ፖለቲካ ውስጥ አነስተኛ ሚና የሚጫወቱ አናሳ ብሔረሰቦች ናቸው። ከክልላቸው ውጪ ያሉ ኅዳጣን የሚባሉት በትውልድ ክልላቸው አብላጫ የሆኑ፤ ነገር ግን ለእነሱ ብሔረሰብ ከተከለለው ክልል ውጪ በመፍለሳቸውና ከብሔረሰባቸው በመነጠላቸው አነሳ የሆኑ ናቸው፡፡ ግሉላን አናሳዎች የሚባሉት ደግሞ በማኅበረሰብ ውስጥ የተገለሉ ተደርገው በሚቆጠሩ የሥራ ዘርፎች እና ሙያዎች ውስጥ የተሠማሩት እንደ ሸክላ ሠሪዎች፣ ቆዳ ፋቂዎች፣ አንጥረኞች፣ ሸማኔዎች፣ የእንጨት ሠራተኞች፣ አዳኞች እና አርብቶ አደሮች ያሉት ናቸው።

   በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኅዳጣን ቡድኖች ሦስት ገፅታዎች

   በቀዳሚነት፣ በክልላቸው ያሉ ኅዳጣንን በሚመለከት ቀዳሚ ኃላፊነት ያለው አካል በሕዝቦች መካከል እኩልነትና አንድነትን የማጎልበት ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣን ያለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቢሆንም፤ ምክር ቤቱ ባለው ለብዙኃን የሚያደላ ተፈጥሯዊ አወቃቀር እንዲሁም ያልተመጣጠነ የብሔረሰቦች ውክልና ምክንያት፣ ይህ ኃላፊነቱ ሙሉ በሙሉ የሚሳካ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህም የኢትዮጵን ልምድ እንደ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ስዊዘርላንድ እና በመሳሰሉት አገራት ካለው ዓለም አቀፍ ልምድ የተለየ ያደርገዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰማኒያ በላይ ብሔረሰቦች ያሉ ቢሆንም፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥ ባለው ያልተመጣጠነ ውክልናና ለኅዳጣኖች ጥበቃ የሚሰጥ ሕግ ባለመኖሩ ምክንያት፣ በውሳኔ አሰጣጥ ሒደት ወቅት በቀላሉ እንዲበለጡ እና እዚህ ግባ የሚባል ድምጽ እንዳይኖራቸው ሆኗል፡፡ ኅዳጣኑ በሕግ ማውጣት፣ በፖሊሲ ቀረጻ እና አፈጻጸም ሒደቶች ላይ ጠንካራ ተጽዕኖ የላቸውም፡፡ በአጠቃላይ ሁሉም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔዎች በቀላል የአብላጫ ድምጽ ሥርዓት የሚወሰኑ ናቸው፡፡

   ስለሆነም፣ ሌሎች ልዩ ሕጎች ወይም አሠራሮች እስካልወጡ ድረስ የኅዳጣኑ ጥቅም ይጠበቃል ብሎ ለማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት የሚሆኑት በየክልል ምክር ቤቶቹ ከገዢው ፓርቲ አባላት መካከል ተመርጠው የሚመጡ ሲሆኑ፤ ምክር ቤቱ ከእንደዚህ ዓይነቱ የፓርቲ ፖለቲካ የተላቀቀ እስካልሆነ ድረስ በኅዳጣኑ ቡድኖች ዘንድ ተዓማኒነት ለማግኘት የሚያስችል ሙሉ ነጻነትና ገለልተኝነት ይጎድለዋል፡፡ ይህም የኅዳጣኑን መብቶች ለማስከበር እና ለማስፋፋት በሚያስችል ትክክለኛ ጎዳና ላይ እንዳልሆነ ያሳያል፡፡ ሕገ-መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን ያለው አካል ነጻና ገለልተኛ እስካልሆነ ድረስ፤ ሕገ-መንግሥታዊ ትርጓሜ የኅዳጣን ቡድኖችን መብቶች የማስከበር እና የማስፋፋት ዓላማዎችን ሊያሳካ አይችልም፡፡

   በሁለተኛነት፣ ከክልላቸው ውጪ ያሉ ኅዳጣን ቡድኖችን [በየክልሎቹ ውስጥ ያሉ ኅዳጣኖችን] በሚመለከት ክልሎቹ ራሳቸው ብዝኃነት ያላቸው ሆነው ሳለ፤ በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ ብሔር ብሔረሰቦች በግዛታቸው ያላቸው በራስ የመወሰን ስልጣን ስለ ግዛት ግትር አረዳድ እንዲኖር አድርጓል፡፡ የተዋቀረው ክልል ወይም የአካባቢ መንግሥት አንድን የተወሰነ የብሔረሰብ ቡድን የበለጠ ኃይል የሰጠ ነው። የክልሉን ግዛት እና ሕዝባዊ ተቋማቱን በብቸኝነት መቆጣጠር የመዋቅሩ ዋነኛ መገለጫ ነው፡፡ ራስን የማስተዳደር ነጻነት ያለው የብሔረሰብ ቡድን በዋናነት ራሱ ሊቆጣጠር ከሚፈልገው ግዛት ጋር አስተሳስሮ የመግለጽ ዝንባሌ አለው፡፡ በዚህም ክልሉ በአብዛኛው የአንድ የተወሰነ ብሔረሰብ ርስት ተደርጎ ይታሰባል፡፡  በዚህ ረገድ ካየነው፤ በአንድ የተወሰነ ክልል ውስጥ የበላይ ለሆነው የብሔረሰብ ቡድን በግዛቱ ውስጥ ራስን የማስተዳደሩ ሁኔታ የበለጠ የመጎለበት ስሜትን ሲያጠነክር፤ ከክልላቸው ውጪ በየክልሎቹ ለሚኖሩ ኅዳጣኖች ግን የተለየ ትርጉም አለው

   ግዛትን የራስ ብቻ አድርጎ የማሰብ ዝንባሌ እና የአንድ ብሔረሰብ ቡድን በክልል ይሁን በዝቅተኛው የመንግሥት መዋቅር ደረጃ በፖለቲካ አብላጫ ድምጽ ወዳለው ማኅረሰብነት የመቀየር አዝማሚያ፣ ክልሎቹ ራሳቸው ብዝኃነት ያላቸው እንደመሆናቸው፤ ከክልላቸው ውጪ በየክልሎቹ ለሚኖሩ ኅዳጣኖች የፖለቲካ መገለልን ይፈጥራል። በእርግጥም በኢትዮጵያ ውስጥ ቀድሞም በነበረው የአገሪቱ የታሪክ እና ፖለቲካ ቅራኔ መኃል የተሰነቀረ የአንድ ክልል ባለቤት በሆኑ የብሔረሰብ ቡድኖች እና በየክልሎቹ በሚኖሩ ኅዳጣኖች መካከል ፍጭቶችና ግጭቶችን ማየት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡

   በአንዳንድ ሁኔታዎች፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከክልላቸው ውጪ በየክልሎቹ የሚኖሩ ኅዳጣን ሥራን፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን፣ የጨረታ ውድድሮች እና ውስን የመሬት ተደራሽነትን የመሳሰሉ ሕግን መሠረት ያደረጉ አድልዎች ይደርስባቸዋል፡፡ ለምሳሌ፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የክልሉ ሕገ-መንግሥት መሬት የክልሉ ነባር ሕዝቦች መሆኑን ጠቅሶ፤ በኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ወደ ክልሉ የሄዱ ፍልሰተኞችን መሬት የማግኘት መብት ይገድባል። ከክልላቸው ውጪ በየክልሎቹ የሚኖሩ ኅዳጣን በክልሉ መንግሥትም ሆነ በታችኛው የመንግሥት መዋቅር ውስጥ በአስፈጻሚው እና በሕግ አውጪው የመንግሥት አካል ላይ ውክልና የሌላቸው፣ ምርጫ ለመወዳደርና ሕዝባዊ ተቋማትን መያዝ ሲፈልጉም እንዲህ ዓይነቶቹ ተቋማት የክልሉ ባለቤት ሕዝቦች እንደሆኑ ተደርገው የሚታሰቡ በመሆናቸው፣ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች የሚገጥማቸው ብሎም ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ አድልዎ የሚያጋጥማቸው ናቸው፡፡

   ከዚህም አልፎ፤ በሁሉም ክልሎች ሊባል በሚችል ደረጃ ከክልላቸው ውጪ በየክልሎቹ ያሉ ኅዳጣን ሕይወት የአንዱ ከሌላኛው ብሔረሰብ ቡድን ጋር በልዩ ልዩ የሕይወት መስኮች እርስ በእርሱ የተቆራኘ ነው፡፡ ሆኖም፤ የእነዚህን ኅዳጣን ቡድኖች በጠቅላላ ፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ የመካተት ጥያቄ መመለስ አሁን ድረስ አከራካሪ እንደሆነ የቀጠለ በመሆኑ፤ ብሔርን መሠረት ያደረገው የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ከክልላቸው ውጪ ያሉ ኅዳጣንን ያካተተ እንዲሆን ዳግም ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ክልሎች ከክልላቸው ውጪ ያሉ ኅዳጣንን በፖለቲካው ስርዓት ውስጥ እንዲካተቱ የማያስችሉ ሕገ-መንግሥታዊ እና ተቋማዊ ውስንነቶች አሉባቸው፡፡ በዚህም ምክንያት፤ ከክልላቸው ውጪ ያሉ ኅዳጣን እና የፖለቲካ አካታችነት ጉዳይ ብሔርን መሠረት ያደረገው የአገሪቱ ፌዴሬሽንን መዋቅራዊ እና የአሠራር አደረጃጀት በጥልቀት ለመፈተሽ ይጋብዛል፡፡

   በሶስተኛነት የሚነሱት፣ በሙያቸው ምክንያት በአብዛኛው ከማኀበረሰባዊ እንቅስቃሴዎች እንዲገለሉ የተደረጉ “ግሉል ኅዳጣን” ናቸው፡፡ ሱዛን ኢፕል (2018፣ ገጽ፡- 173) የተሰኘችው ጸኃፊ እንዳለችው ከሆነ ለምሳሌ፡- ከማኅበረሰብ መገለልን ከሚያስከትሉ የምግብና መጠጥ የነውር ድርጊቶች እንዲሁም ዝቅተኛ እና ከፍተኛ ደረጃ ወይም መደብ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚደረግ ጋብቻ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ባቋቋማቸው ብሔርን መሠረት ባደረጉ ክልሎች ውስጥ ያሉትን የብሔረሰብ እና የሙያ ኅዳጣን መብቶች በቀጥታ ተደራሽ ለማድረግ ግልጽ አቋም ይጎድለዋል፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ብሔርን እንደ ብቸኛ የአደረጃጀት መርህ ቢያስቀምጥም፣ አንድን ቡድን ብሔር ነው አይደለም ብሎ ለመለየት በፌዴራሉም ሆነ በክልሎች ሕገ-መንግሥት በተቀመጡት መስፈርቶች መሠረት የብሔርነትን መስፈርት የሚያሟሉ ቢሆኑም እንኳን ሕገ-መንግሥቱ ለእነዚህ ኅዳጣን ከለላ ሳይሰጣቸው አልፏል፡፡

   በዚህ የተነሳ፣ በአሁኗ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካቶች መድልዎ፣ ተለይቶ መኖር፣ ጭቆናና መገለል እንዲደርስባቸው ብሎም በማኅበረሰቡ ውስጥ እዚህ ግባ የማይባል ደረጃ ኖሯው እንዲኖሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ ለምሳሌ፡- በአማራ ክልል፣ ደቡባዊ ክፍል እነዋሪ ወረዳ በሚባል አካባቢ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች፣ ቤተ-እስራኤላዊያን እና የወይጦ ማኅበረሰቦች እንዲሁም በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጉራጌ ዞን ውስጥ የሚኖሩት የሀዲቾ፣ ማና እና ማንጃ እንዲሁም ፉጃ (የእንጨት ሠራተኞች) የሚባሉት ኅዳጣን ይገኙበታል፡፡

   መውጪያ መንገድ

   የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት በክልላቸው ያሉ ኅዳጣን ቡድኖችን ጥቂት መብቶች የሚያረጋግጡ የተለያዩ ድንጋጌዎች የያዘ ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው ብሔሮችና ብሔረሰቦች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥ ቢያንስ አንድ ተወካይ አላቸው፡፡ ምንም እንኳን ሁሉንም ያካተተ ባይሆንም ከ100,000 በታች ሕዝብ ያሏቸው አናሳ ብሔረሰቦች፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥ ለእነሱ ብቻ ተለይተው የተቀመጡ 20 የምክር ቤት መቀመጫዎች አላቸው። እነዚህ አናሳ ብሔረሰቦችም ሆኑ ሌሎች እስካሁን ዕውቅና ያልተሰጣቸው ሕዝቦች ትርጉም ያለው ሚና ይጫወቱ ዘንድ አሁን በምክር ቤቶቹ  ካሏቸው መቀመጫዎች በተጨማሪ ተጨማሪ መቀመጫዎችን ለይቶ ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው። ሕገ-መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣንን በሚመለከት በሌሎች አገራት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኘው የፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ማሻሻያ በማድረግ የፌዴሬሸን ምክር ቤት ሥልጣኑ ዳግም ታይቶ ነጻና ገለልተኛ ለሆኑት መደበኛ ፍርድ ቤቶች እንዲያስተላልፍ መደረግ ይኖርበታል።

   ከክልላቸው ውጪ ያሉ ኅዳጣን ቡድኖች የሚገጥማቸውን የአካታችነት ችግሮች በሚመለከት የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ሁለት የመፍትሔ ሐሳቦች ያሉ ሲሆን፤ እነርሱም፡- ሕዝቦቹ ነዋሪ በሆኑበት ግዛት ውስጥ ከብዙኃኑ ጋር የሥልጣን ተጋሪ እንዲሆኑ ማድረግ ወይም ከግዛት ጋር ቁርኝት የሌለው የአስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት ናቸው። በአንዳንድ ፌዴሬሽኖች የፌደራል መንግሥቱ የፌዴሬሽኑ አባላት በየግዛታቸው ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ኅዳጣንን መብቶች እያከበሩ መሆን አለመሆናቸውን እንዲቆጣጠር የሚያስችል ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣን እንዲኖረው ይደረጋል፡፡ በሕገ መንግሥት በግልጽ የተቀመጡ መብቶች እና ጠንካራ የአፈጻጸም ሥርዓቶች መኖር የአብላጫዎችን አምባገነን የመሆን ስጋቶች ለመቀነስ እንዲሁም በየክልሎቹ ውስጥ ያሉ ኅዳጣኖችን መብቶችን እንዲከበሩ ለማድረግ ይችላሉ። በተጨማሪም፤ በቂ ተወካይ ሳይኖራቸው ቀርቶ በየክልሎቹ ውስጥ ያሉ ኅዳጣን ብሔረሰቦች ላይ የሚደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቅረፍ የብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት የማይጋፉ ተጨማሪ የድጋፍ እርምጃዎች ሊኖሩ ይገባል።

   ስልጣንን የመጋራት አደረጃጀት ቁልፍ ባህሪ የሚባለው በየክልሎቹ ውስጥ ያሉ ኅዳጣኖችን ጨምሮ አብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል የሚወክሉትን ዋናዎቹን የፖለቲካ ተዋንያን በፖለቲካ ሂደቱም ሆነ በፌዴራል፣ በክልል ወይም በአካባቢ ደረጃ ባሉ ውሳኔ ሰጭ አካላት ውስጥ እንደ አስፈላጊነቱ ማካተት ነው። ከግዛት ጋር ቁርኝት የሌለው የአስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት ወሳኝ ከሆኑት ነገሮች መካከል በተበታተነ መልኩ ለሚኖሩት ብሔር ብሔረሰቦች የባህል እና የቋንቋ ራስ-ገዝ አስተዳደር እንዲዘረጉ ማስቻል ነው፡፡ ከዚህም አልፎ፣ በየክልሎቹ ውስጥ ላሉ ኅዳጣኖች በክልሉ ባለቤት ብሔረሰብ ሊደርስባቸው ከሚችል ጭቆና እና አድልዎ ጠባቂ ሆኖ እንዲያገለግል ለፌዴራል መንግሥቱ ተጨማሪ ሥልጣን መስጠትም ይቻላል፡፡ በመጨረሻም፣ በየክልሎቹ ውስጥ ላሉ ኅዳጣን ብሔረሰቦችን መብቶችም ይሁን የግለሰብ ዜጎች መብቶችን ለማረጋገጥ የሚያለግሉት ሁነኛ መንገዶች በፌዴራልና በክልሎች ሕገ-መንግሥት ውስጥ የመሠረታዊ መብቶች ጥቅል ዝርዝር እንዲኖረው ማካተት እና በጠንካራ ፍርድ ቤቶች ጨምሮ በሌሎችም ተቋማዊ አሠራሮች በሚገባ በማስፈጸም ነው፡፡ ይህ ኃላፊነት በዋናነት የፌደራል መንግስቱ ቢሆንም ክልሎች በፌዴራል ሕገ መንግሥቱ ከተቀመጡት መብቶች በተሻለ መብቶችን የበለጠ አስፋፍተው ሊያበለጽጉ ይችላሉ፡፡

   በመጨረሻም፤ በሙያቸው ምክንያት እንዲገለሉ የተደረጉ ኅዳጣን ቡድኖችን በተመለከተ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ ማኅበረሰቡ፣ እንዲሁም ሌሎችም ዓለም አቀፍ ባለድርሻዎች ሁሉን-አቀፍ ሥልጠናዎችና የሰብአዊ መብቶች ትምህርቶችን የመሳሰሉ ስልታዊ እርምጃዎችን ሊወስዱ ይገባል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ለእነዚህን ኅዳጣኖች ምላሽ በመስጠት ሒደት ውስጥ የተጠናከረ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎችም የማበረታቻ ማዕቀፎችን ማፈላለግ አስፈላጊ ነው፡፡

   በጥቅሉ፤ በዚህ ጹሁፍ የተላለፈው ቁልፉ ነጥብ በዚህ አከራካሪ ጉዳይ ላይ መፍትሔ የመሻቱ ነገር የአገሪቱን የማኅበረ-ፖለቲካ ሥርዓት ሁሉንም ገጽታዎች ዴሞክራሲያዊ ማድረግ እና ኅዳጣኑ የሚያነሱትን በማኅበረ-ፖለቲካው የመካተት ጥያቄያቸውን ተጨባጭ ችግሮች ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ሁነኛ በሆኑ ተግባራዊ እርምጃዎች ሊደገፍ ይገባል የሚለው ነው፡፡

   *ፀጋዬ ደጀኔ ዳባ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሲሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት የዶክትሬት (ፒ.ኤች.ዲ) ዲግሪያቸውን በሀሮማያ ዩንቨርሲቲ በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

   የአታሚው ማስታወሻ: ይህ ጽሑፍ ካርድ የወጣቶችን ሥልጡን እና ምሁራዊ የውይይት ልማድ ለማሳደግ “በወጣቶች የምክክር መድረኩ” ከሚያስተናግዳቸው ጽሑፎች አንዱ ነው።  በዚህ ዓምድ ለመስተናገድ ወይም ለዚህ ጽሑፍ መልስ ለመስጠት ከፈለጉ በ info@cardeth.org ላይ ኢሜይል ያድርጉልን።

Viewing 0 reply threads
Reply To: ኅዳጣን ቡድኖች እና በማኅበረ-ፖለቲካ ሥርዓቱ የአካታችነት ጥያቄ በኢትዮጵያ
Your information: