አካታች ማኅበረሰብ የመፍጠር ጉዞ

Home Forums የወጣቶች መድረክ አካታች ማኅበረሰብ የመፍጠር ጉዞ

 • This topic is empty.
Viewing 0 reply threads
 • Author
  Posts
  • #3646 Reply

   በአብዱልፈታ መሀመድ ፋራህ*

   ኢትዮጵያ የኅዳጣን ብሔረሰቦች ሀገር መሆኗ በሰፊው ይነገራል፤ በፌዴራል ደረጃ አብላጫውን የሚይዝ የተለየ ብሔር የለም በሚለው መልኩ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በክልል ደረጃ የተወሰኑ አብላጫ እና አናሳ ብሔረሰቦች አሉ።

   የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት የተዋቀረው በአንድ ክልል የተሰባሰቡ ኅዳጣን ብሔረሰቦችን ለማብቃት ነው። በመሆኑም፤ ዋና ዋና ብሔር ብሔረሰቦች የየራሳቸውን ሕገ-መንግሥትና ስልጣን ይዘው የራሳቸውን ክልል አቋቁመዋል። እንደ ኦሮምያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ አፋር፣ ሶማሌ እና ሀረሪ ያሉት አንዳንድ ክልላዊ መንግሥታት በቅርቡ የተቋቋመውን ሲዳማን ጨምሮ የተዋቀሩት ለርዕሰ ብሔሮቹ ነው። በሌላ በኩል እንደ ደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝና ጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት  ያሉት ደግሞ ፖለቲካን፣ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን፣ የአሰፋፈር ቅርጽን፣ ባህልንና ቋንቋን መሠረት በማድረግ የበላይ ያልሆኑ ቡድኖች ያሏቸው ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት ተቋቁመዋል። ሆኖም በኢትዮጵያ የብሔር-ተኮር ፌደራሊዝም ከተጀመረ በኋላ በክልላቸው ያሉ እና ከክልላቸው ውጪ ያሉ ሁለት ዓይነት ኅዳጣን ብሔረሰቦች ተፈጥረዋል፡፡ በእነዚህ ክልላዊ መንግስታት ውስጥ፣ በክልላቸው ያሉ እና ከክልላቸው ውጪ ያሉ ኅዳጣን ብሔረሰቦች የተለያዩ መገለጫዎች አሏቸው።

   ይህ በንዲህ እንዳለ፣ ጸጋዬ “ኅዳጣን ቡድኖች እና የማኅበረ-ፖለቲካ ሥርዓቱ የአካታችነት ጥያቄ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በጻፈው መጣጥፍ በኢትዮጵያ ውስጥ በክልላቸው የሚኖሩ፣ ከክልላቸው ውጪ የሚኖሩ እና ግሉላን ኅዳጣን ቡድኖች የሚያጋጥሟቸውን አንዳንድ ማኅበረ-ፖለቲካዊ መገለሎች ጠቁሟል። የጸጋዬ ጽሁፍ የኅዳጣን ቡድኖችን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መገለል በደንብ ያብራራ መሆኑን እውቅና የምሰጠው ቢሆንም፤ በጽሁፉ ውስጥ ያልተነሱ ነገሮች ግን አሉ። ስለዚህም፤ ለጸጋዬ ጽሁፍ የሰጠኹት ይህ ምላሽ በኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ ኅዳጣን ቡድኖች ጉዳይ ሰፋ አድርጎ ለማሳየት እና ከሌላ አንጻር ለማየት እንጂ፤ ለመሞገት ያለመ አይደለም፡፡

   የኅዳጣንን ማኅበራዊ ተሳትፎ ማሳደግ በኢትዮጵያ 

   አሁን ምላሽ እየሰጠሁበት ባለው ጽሁፍ ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ኅዳጣን ብሔረሰቦች የተሰጠውን ትንተና እያከበርኩ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በክልላቸው ውስጥ እና ከክልላቸው ውጪ የሚኖሩ ኅዳጣን ብሔረሰቦች ጋር አካታች የሆነ ማኅበረሰብ አስፈላጊነት ላይ ማስፋት እና ትኩረት መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ ማኅበረሰባዊ አካታችነትን ለማስፋፋት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከማኅበራዊ አካታችነት ስልቶች ጋር በማያያዝ በተለያዩ ዘርፎች ማለትም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና ፖለቲካዊ ግንባሮች በበርካታ ደረጃዎች ላይ መከናወን አለበት።

   በክልላቸው ውስጥ ያሉ ኅዳጣንን ሁኔታ በተመለከተ፣ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ውስጥ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች በክልል ወይም ንዑስ ክልላዊ ደረጃ በብሔረሰብ ዞንና በልዩ ወረዳ ደረጃ ጭምር ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ተፈቅዶላቸዋል። የራሳቸው ክልል ያላቸው ብሔር ብሔረሰቦች በክልሉ መንግስት የመሳተፍ መብታቸውን በክልል ተቋማት እና በአብዛኛው በክልሉ ውስጥ አብላጫ በሆኑ ብሔረሰቦች የበላይነት በተያዙት የክልሉ ምክር ቤት እና አስተዳደር በኩል ይጠቀማሉ፡፡ በዚህ ምክንያት በክልላቸው ውስጥ ያሉ ኅዳጣን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ወቅት እንዲሁም በክልል ደረጃ በሚደረጉ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውስጥ መካተት ላይ ብዙውን ጊዜ እክል ይገጥማቸዋል፡፡

   በአገር አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት በፌዴራል ደረጃ የሚገኙ ኅዳጣን ብሔረሰቦችን በሁለቱ የፓርላማ ምክር ቤቶች ውስጥ የመወከል እድሎችን በስፋት በማዘጋጀት አናሳ የሆኑ ብሔረሰቦችን በማካተት ለማስፋፋት ሞክሯል። በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ውክልና በፌዴራል መንግሥት የሕግና ፖሊሲ ቀረጻና አፈጻጸም ሂደቶች ላይ መሳተፍ የሚችሉበት ነው። በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት በፌዴራል ደረጃ ሁለተኛው የኅዳጣን ብሔረሰቦች ውክልና የተሰጠበት መንገድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ያለው የኅዳጣን ብሔረሰቦች ውክልና ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ኅዳጣን ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ቢያንስ 20 መቀመጫዎች እንዲኖራቸው ይደነግጋል።

   እነዚህ አካሄዶች በትክክለኛ አቅጣጫ የተወሰዱ እርምጃዎች ቢሆኑም፤ በክልላቸው ውስጥ ያሉ ኅዳጣንን ተካታችነት ለማሳደግ በክልላዊም ሆነ በአገር-አቀፍ ደረጃ ያሉ ፖሊሲ አውጪዎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮቻቸውን የበለጠ ማስተናገድ አስፈላጊ ነው። በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች እና በፖሊሲ ቀረጻ ውስጥ በሕዝባዊ ተሳትፎ መልክ የሁሉንም የህብረተሰብ አባላት ፖለቲካዊ አካታችነት ማህበረሰባዊ ተሳትፎን የማሳደግ ዋና ገጽታ በመሆኑ በአገሪቱ ውስጥ በክልላቸው ውስጥ ባሉ ኅዳጣኖች ሁሉ በሁሉም ዘርፎች መፈለግ አለበት፡፡

   በሌላ በኩል፣ ከክልላቸው ውጪ የሚኖሩ ኅዳጣን ቡድኖች ጉዳይ የበለጠ የተወሳሰበ ነው፡፡ ይህም በብሔር ፌዴራሊዝሙ እና በክልላቸው ያሉ ኅዳጣን – ምንም እንኳን በርካታ ቁጥር ካላቸው ከክልላቸው ውጪ ከመጡ ኅዳጣን ጋር አብረው ቢኖሩም – ፌዴራሊዝሙ በክልላቸው ውስጥ የራሳቸውን ጉዳይ የመወሰን ተቋማዊ ቅርጽ እንዲይዝ ያደረገው በመሆኑ ነው፡፡ በርካታ ከክልላቸው ውጪ የሚኖሩ ኅዳጣን ማኅበረሰቦች በእያንዳንዱ ክልል ውስጥ የሚኖሩት በታሪካዊ ክስተቶች በተለያዩ አቅጣጫዎች በነበሩ የሕዝብ እንቅስቃሴዎች ምክንያት ነው። ሆኖም፤ አንዳንድ ክልሎች የእነዚህን ማኅበረሰቦች መኖር እውቅና ባይሰጡም፤ ሌሎች ደግሞ ያለ ውክልና እውቅና ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን፣ በማኅበረሰባቸው ውስጥ ከውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ጋር ብዙም ተሳትፎ፣ ተጽዕኖ ወይም ግንኙነት ባይኖራቸውም ከክልላቸው ውጪ ያሉ ኅዳጣን ብዙ ጊዜ በስፋት ማኅበራዊ መድረኮች የአድልዎ፣ የፍትሕ መጓደል እና የማኅበራዊ መገለል ሰለባ ናቸው።

   ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በፌዴራላዊ ስርዓታችን ውስጥ በተለያዩ በክልላቸው ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች ራስን የማስተዳደር ሚዛን እና ነፃ የጉልበትና የካፒታል እንቅስቃሴን ከክልላቸው ውጪ ላሉ ብሔር ብሔረሰቦች ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት መካከል ውጥረት ሲፈጠር ተመልክተናል። በኦሮሚያ፣ በደቡብ ክልል፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ፣ በአማራ፣ በሶማሌ እና በመሳሰሉት ከክልላቸው ውጪ ያሉ ኅዳጣን ብሔረሰቦችን ማፈናቀል እና ማግለል በዝቷል። ይህም ሀገረ መንግሥቱን አደጋ ላይ ይጥላል፡፡

   ማኅበራዊ አካታችነትን ለማስፋፋት የሁሉም በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውስጥ የመሳተፍ እድል ወሳኝ ነው። የፖለቲካ አካታችነት እያንዳንዱ ማኅበራዊ ቡድን ህይወቱን በሚነኩ ውሳኔዎች ላይ የራሱን አስተያየት መስጠትን ያካትታል፡፡ የክልል መንግስታት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አካታችነት ራዕይን በራሳቸው አሠራር ለማስተዋወቅ ብዙ ሊሰሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ተወካዮች በመንግስት ውስጥ መኖራቸው የተለያዩ እና ውክልና ያለው መንግስት ለመፍጠር አንድ መንገድ ሊሆን ይችላል። የተለያዩ የሕብረተሰብ አባላት በፖሊሲ ማውጣት ውስጥ ተደራሽነት እና ተሳትፎ የፖለቲካ ተሳትፎን ለመጨመር ሌሎች መንገዶች ሆነው ሊያካትቱ ይችላሉ።

   ለማኅበራዊ መካተት ወደፊት የሚያስኬድ መንገድ

   ሁሉንም ያካተተ ማኅበረሰብ መፍጠር በመንግስትና በሕዝቡ ርብርብ ብቻ እውን ሊሆን የሚችል ለሁሉም የሕብረተሰብ አባል በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ማለትም በሲቪክ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውስጥ እኩል እድሎችን መፍጠር የሚችል ሁለገብ ሂደት ነው።

   ለረጅም ጊዜ፣ ብዙ ጽሁፎች የኅዳጣንን ማኅበራዊ ማካተት ለማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ እርምጃዎችን ሲጠቅሱ ነበር። እኔም በጽሑፌ ውስጥ፣ ሶስት ወደፊት ሊያስኬዱ የሚችሉ መንገዶች ላይ አፅንዖት ሰጥቻለሁ፡፡ እነዚህም የኅዳጣን ቡድኖችን ሰብአዊ መብቶች ማስከበር፣ የኅዳጣን መብቶች ፖለቲካዊ ጥበቃ እና የኃይል-መጋራት እና/ወይም የክልል ያልሆነ ራስን በራስ የማስተዳደር ተጓዳኝ እርምጃዎችን ማሳደግ ናቸው፡፡

   በክልላቸው ውስጥ እና ከክልላቸው ውጪ ያሉ ኅዳጣን ብሔረሰቦችን ማኅበራዊ ማካተት ለማስፋፋት በፌዴራል ሕገ-መንግሥት፣ በክልል ሕገ-መንግሥቶች ውስጥ ኅዳጣን ብሔረሰቦችን መብቶች እና የግለሰብ ዜጎች መብቶችን ማስጠበቅ እና ጠንካራ ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ ተቋማዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ማስከበር አስፈላጊ ነው።

   ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይም በፌዴሬል ሕገ-መንግሥቱ ምዕራፍ 2 (ከአንቀጽ 8 – 12) እና ምዕራፍ ሦስት አንዳንድ የመሻሻል ምልክቶች እና በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ ያሉ እርምጃዎች አሉ፡፡ ነገር ግን፤ እነዚህ በትንሹ የተተገበሩ ሲሆኑ የሲቪል እና የፖለቲካ ነፃነቶችን ለማስከበር ያለው የፖለቲካ ፍላጎት እምብዛም ነው፡፡ ስለሆነም፤ የኅዳጣን ብሔረሰቦችን ማኅበራዊ ተካታችነት ለማበረታታት ነጻና ገለልተኛ ተቋማት እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ኅዳጣን ቡድኖችን ጨምሮ የሁሉንም ዜጎች ሰብአዊ መብቶች የሚያስጠብቅ እና የሚያስከበሩ ጠንካራ ተቋማት መኖር ወሳኝ ነው።

   ሁለተኛው እርምጃ በክልላቸውም ሆነ ከክልላቸው ውጪ ላሉ ኅዳጣን በክልሉ አብላጫ ብሔረሰብ ሊደርስባቸው የሚችለውን ጭቆና እና መድልዎ ለመከላከል የፌደራል መንግስቱ ለእነዚህ ኅዳጣን ወገኖች ጠባቂ ሆኖ እንዲያገለግል ማስቻል ነው። የፌደራሉ እና የክልል ሕገ-መንግሥቶች በክልላቸው ውስጥ እና ከክልላቸው ውጪ ያሉ ብሔረሰቦችን መብቶች ቢያረጋግጡም፤ ተግዳሮቱ የሚሆነው የፖለቲካ ተቋማቱን የሚቆጣጠረው የብሔር ብሔረሰቦች ቡድን ብዙውን ጊዜ እነዚን መብቶችን ለማስከበር ያለው የፖለቲካ ፍላጎት ያነሰ መሆኑ ነው።

   በመጨረሻም፣ ሌላኛው መውጫ መንገድ የስልጣን መጋራት እና/ወይም ከክልል ጋር ያልተያያዘ ራስን በራስ ማስተዳደር ነው። ኅዳጣንን በከፍተኛ ሁኔታ የማግለል ሁኔታዎች በሚኖሩበት ጊዜ የስልጣን መጋራት እና/ወይም ከክልል ጋር ያልተያያዘ ራስን በራስ ማስተዳደር ኅዳጣን ላይ ከሚደርስ ማግለል መውጫ መንገድ ሊሆን ይችላል። ስልጣንን እና የግዛት ቦታን አብላጫ ካላቸው (ከርዕስ ብሔረሰቦች) ጋር መጋራት እንደ አንድ የጋራ ጥቅም በማየት በስልጣን መጋራት ውስጥ የአናሳ ቡድኖችን ማኅበራዊ ተሳትፎ ማረጋገጥ ይችላል። ከክልል ጋር ያልተያያዘ የራስ አስተዳደር ሥርዓት ግን የክልሉ አብላጫ ብሔረሰብ የራስን በራስ ማስተዳደር መብት መጠቀሙን እየቀጠለ፤ ኅዳጣን ብሔረሰቦች የፖለቲካ እና የባሕል ቦታ እንዲኖራው ሊያደርግ ይችላል።

   *አብዱልፈታ መሀመድ ፋራህ በጅግጅጋ ዩንቨርሲቲ መምህር ናቸው፡፡

   የአታሚው ማስታወሻ: ይህ ጽሑፍ ካርድ የወጣቶችን ሥልጡን እና ምሁራዊ የውይይት ልማድ ለማሳደግ “በወጣቶች የምክክር መድረኩ” ከሚያስተናግዳቸው ጽሑፎች አንዱ ነው።  በዚህ ዓምድ ለመስተናገድ ወይም ለዚህ ጽሑፍ መልስ ለመስጠት ከፈለጉ በ info@cardeth.org ላይ ኢሜይል ያድርጉልን።

Viewing 0 reply threads
Reply To: አካታች ማኅበረሰብ የመፍጠር ጉዞ
Your information: