ኢትዮጵያ በቀጠናዊ ቀውስ ውስጥ

Home Forums የወጣቶች መድረክ ኢትዮጵያ በቀጠናዊ ቀውስ ውስጥ

 • This topic is empty.
Viewing 0 reply threads
 • Author
  Posts
  • #4129 Reply

   ሐጎስ /አምላክ*

   በዚህ ጽሁፍ ማሳየት የምሞክረው የኢትዮጵያ ጂኦ-ፖለቲካዊ አስፈላጊነት መዳከሙን እና ያጋጠማትን ጂኦ-ፖለቲካዊ ቀውስ ማመላከት ነው፡፡ ጂኦ-ፖለቲካ የሚለው ቃል በዚህ ጽሁፍ ውስጥ በቀጠናው ውስጥ ያለውን ዉጪያዊና ውስጣዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ማሳየትን ታሳቢ ያደርጋል፡፡ እንደሚታወቀው ውስጣዊና ውጪያዊ ተለዋዋጭነት የጂኦ-ፖለቲካዊ ችግሮችን ያባብሳል፡፡ የተፈጠረው ሐገራዊ ቀውስ ኢህአዴግ-መራሹን ስርዓት ቢገዳደርም፣ የተነሳው ተቃውሞ በተገባለት የለውጥ ቃል ሊረግብ ችሏል፡፡ ዳሩ ግን በለውጡ ኃይል የተፈጠረው የደስታ ስሜት ኢህአዴግ ለሁለት ሲሰነጠቅ ወደ ተስፋ ማጣት ተቀየሯል፡፡ በፌደራል መንግስቱ እና በህወሓት የፖለቲካ ኃይሎች መሐል የተነሳው ጦርነት ሐገሪቱን ለቀውስ ዳርጓል፡፡ እንዲሁም የሐገሪቱን ጠንካራ የውጭ ግንኙነትና ጥቅሞች በእጅጉ ጎድቷል፡፡

   በተፈጠረው የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ተመሳሳይ ችግር በሐገር ውስጥም ተስተውሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሐገሪቱ በአደገኛ ፖለቲካዊ እና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ አደጋ ውስጥ ተነክራለች፡፡ ስራ-አጥነት እጅግ ከሚወነጨፍ የዋጋ ንረት ጋር ተደምሮ የዜጎችን ህይወት አስከፊ አድርጎታል፡፡ በእዚህ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያ በአደገኛ የውጭ ምንዛሪ ድርቅ ተመታለች፡፡

   የአለም-አቀፉ የጂኦ-ፖለቲካዊ ፉክክር እና የዓለም-አቀፍ ስርዓቱ መዘበራረቅ ለኢትዮጵያ ጂኦ-ፖለቲካዊ ቀውስ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል፡፡ በፕሬዝዳንት ትራምፕ እና በባይደን አስተዳደር ለአሜሪካ ፖሊሲዎች የሚያጋድሉት ዓለም-አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ከማሳደር አንስቶ ማዕቀብ እስከ መጣል የሚደርስ እርምጃ ወስደዋል፡፡ ከዛ ባሻገር የቻይና አማላይ ብድር መቀዛቀዝ፣ በቀጠናው ላይ የተስተዋለው የኃያላን ሐገራት ፉክክር፣ የኮሮና ቫይረስ መስፋፋት እና የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚስተዋለው የዛሬው የጂኦ-ፖለቲካዊ ቀውስ የራሱ ሚና አለው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም ችግሮች ምን እንደሚመስሉ ከስር በዝርዝር ተዳሰዋል፡፡

   የአባይ ግድብ ቀውስ እና ተያያዥ የውጭ ተጽዕኖ    

   እ.ኤ.አ በ2018 ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ መንግስት አዲስ አጀንዳ ወጥኖ ነበር፡፡ አዲሱ የለውጥ አስተዳደር የሐገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሻሻል እንዲረዳው “ሐገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ” መርሀ ግብር አስተዋውቋል፡፡

   ከኢኮኖሚ ማሻሻያው በኃላ አሜሪካ እንዲሁም አይኤምኤፍ እና የአለም ባንክ የመሳሰሉ ዓለም-አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ማሻሻያውን ለመደገፍ ቃል ገብተው ነበር፡፡ አይኤምኤፍ በሶስት ዓመት የሚጠናቀቅ 2.9 ቢሊየን ዶላር ቃል ገባ፣ አለም ባንክ በበኩሉ ማሻሻያውን ለመደገፍ የሚውል 500 ሚሊየን እንደሚሰጥ አስታወቀ፡፡ እንዲሁም አሜሪካ የኢኮኖሚ ማሻሻያው እንዲሳካ ለማድረግ ከሶስት እስከ አምስት አመት ለሚደርስ ግዜ የአምስት ቢሊየን ዶላር መዋዕለ-ንዋይ ልታደርግ እንደምትችል አሳወቀች፡፡

   ዳሩ ግን ቃሉ ተፈጻሚ ሊሆን አልቻለም፡፡ እ.ኤ.አ በሰኔ ወር 2020 ኢትዮጵያ የአባይ ግድብን ውሃ የመጀመሪያ ዙር የሙሌት ስራ ስትጀምር፣ ወዲያውኑ አለም ባንክ ለኢትዮጵያ ሊሰጥ ያቀደውን 500 ሚሊየን ዶላር አገደ፡፡ የትራምፕ አስተዳደር በበኩሉ ኢትዮጵያ በግድቡ መነሻነት ከግብጽ እና ከሱዳን ጋር በገባችው እሰጥ አገባ ምክንያት ለሐገሪቱ ሊሰጡ የሚችሉ እርዳታዎችን አቋረጡ፡፡ በሐገራቱ መካከል የተነሳውንም ውዝግብ ለማርገብ እና ለማደራደር አሜሪካ እና አለም ባንክ ሙከራ አደረጉ፡፡ ዳሩ ግን በግድቡ ዙሪያ እና በማስታረቁ ውስጥ የአሜሪካ አቋም ሆኖ የተገኘው ግብጽን በሚጠቅም መልኩ ነው፡፡ የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያ ግድቡን ውሃ ከመሙላቷ በፊት ከሁለቱ ሐገራት ጋር ስምምነት ላይ መድረስ እንዳለባት ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፡፡ አለም ባንክ በበኩሉ በድርድሩ ውስጥ ጠንካራ ተጽዕኖውን አሳርፎ ኢትዮጵያ ከግብጽ እና ሱዳን ጋር ወደ ስምምነት እንድትመጣ ለማስገደድ ሙከራ አድርጓል፡፡

   ከጥቂት ሳምንታት በኃላ አለም ባንክ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሊሰጥ ቃል የገባውን 2.9 ቢሊየን ዶላር አገደ፡፡ ባንኩ በመጀመሪያው ዙር ቃል የገባው ለኢኮኖሚ ማሻሻያው የሚውል 60% ድጋፍ ለማድረግ፣ ለሶስት ዓመት የሚረዳ 10 ቢሊየን ዶላር ነው፡፡

   አይኤምኤፍ ለሐገሪቱ ድጋፍ ይውላል የተባለውን ገንዘብ በተመሳሳይ መልኩ አገደ፡፡ በአጭሩ ኢትዮጵያ ከአለም-አቀፎቹ የፋይናንስ ተቋማት ከሚገኙ እርዳታዎችና ብድሮች ተገለለች፡፡

   እንደሚታወቀው ግብጽ የአሜሪካ ጂኦ-ስትራቴጂካዊ አጋር ነች፡፡ ስለዚህም በኢትዮጵያ ላይ የአሜሪካንና የአረብ ሊግን ድጋፍ እንዲሁም በአባይ ዙሪያ የጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸውን ኃይሎች ማነሳሳት ችላለች፡፡

   አሜሪካ ፊቷን ወደ ህንድ ፓስፊክ ማዞሯ እና የአሜሪካ ውስጣዊ የፖለቲካ ለውጥ    

   ከሁለተኛው የአለም ጦርነት አንስቶ መካከለኛው ምስራቅ እና የቀይ ባህር አከባቢ አሜሪካ አይኗን የጣለችበት አስፈላጊ የጂኦ-ስትራቴጂካዊ ቀጠና ነበር፡፡ አሜሪካ ትኩረቷን ቀጠናው ላይ አድርጋ ኢትዮጵያን ዋነኛ ጂኦ-ፖለቲካዊ አጋር አድርጋት ቆይታለች፡፡

   የአጼ ኃይለ-ሥላሴዋ ኢትዮጵያ የአሜሪካ ሁነኛ አጋር እንዲሁም ዋነኛ ድጋፍ ተቀባይ፣ በቀይ ባህር አከባቢ ላይም የአሜሪካን የጂኦ-ፖለቲካዊ ጥቅም የምታስጠብቅ ወሳኝ ሐገር ነበረች፡፡

   የኢህአዴግ ኢትዮጵያ ከ9/11 የሽብርተኞች ጥቃት በኃላ በቀጠናው ላይ አሜሪካ ለምታካሂደው የሽብርተኛነት ውጊያ የአሜሪካ ሁነኛ አጋር ሆናለች፡፡ የኢህአዴግ መንግስት በምስራቅ አፍሪካ በተካሄደው የአክራሪነት እና አልሸባብን ለማዳከም በተካሄደው ውጊያ ስርዓቱ ሰፊ እገዛ አድርጓል፡፡

   ቀደም ባለው ልምድ በቅደም-ተከተል መካከለኛው ምስራቅ፣ አውሮፓ እና ምስራቅ እስያ የአሜሪካ ቀዳሚ አጋሮች ነበሩ፡፡ በአሁን ሰዓት አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ላይ ያላት የጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎት ከሌሎቹ አካባቢዎች አንጻር እጅግ አሽቆልቁሏል፡፡ በውስጣዊ የፖለቲካ ተጽዕኖ ምክንያት አሜሪካ በቀይ ባህር አከባቢ ያላት ፍላጎት ተዳክሟል፡፡

   አሜሪካ በአብዛኛው ሊባል በሚችል መልኩ ከኃይል ምንጭ ጥገኝነት ተላቃለች ስለዚህም በቀይ ባህር እና በመካከለኛው ምስራቅ አከባቢ የሚኖራት ጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎት ዝቅተኛ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ አስተዳደር ትኩረቱን ያደረገው በአሜሪካ ህብረተሰብ መካከል እየተስተዋሉ ባሉ ማህበረ-ፖለቲካዊ መከፋፈሎች ዙሪያ ላይ ነው፡፡ የባይደን አስተዳደር እንኳ ችግሩን ለመፍታት በትሪሊየን የሚቆጠር ዶላር ወጪ አድርጓል፡፡

    

   ከዚህ በኃላ አሜሪካ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እና ትኩረቷን በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የምታደርግበት በቂ ምክንያት የለም፡፡ በአሁኑ ሰዓት የአሜሪካ ግልጽ የጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎትና ፖሊሲ የሚያጠነጥነው የቻይናን መስፋፋት መግታት ላይ እና በህንድ ፓስፊክ ቀጠና አከባቢ በሚኖሩ ሐገሮች ዙሪያ ነው፡፡

   የኢትዮጵያ የጂኦ-ፖለቲካዊ አስፈላጊነት የሚመነጨው አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ላይ ከሚኖራት ጂኦ-ስትራቴጂካዊ አላማ አንጻር ነው፡፡ ነገር ግን አሁን አሜሪካ ከመካከለኛው ምስራቅ ወጥታ ትኩረቷን ቻይና ላይ አድርጋለች፡፡

   ይህ የኃይል ለውጥ ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የሚኖራትን ጂኦ-ፖለቲካዊ አስፈላጊነት ይቀንሰዋል፣ ቀንሶታልም፡፡

   የቻይና አማላይ ብድር መቀነስ      

   በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ግስጋሴ ውስጥ የቻይና ብድር ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡ ኢትዮጵያ ከ30 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ብድር ዕዳ ሲኖርባት፣ ከእዚህ ውስጥ ወደ 14 ቢሊየን የሚጠጋው ከቻይና የተገኘ የብድር ዕዳ ነው፡፡

   ከዓለም-አቀፉ ንግድ ድርጅት መስመር ውጭ እንዲሁም ካላት የተከማቸ የውጭ ምንዛሬ አንጻር ቻይና ለኢህአዴግ አስተዳደር የፋይናንስ እሴት እና የኢኮኖሚ መነቃቂያ ምንጭ መሆን ችላ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ኢትዮጵያ ከቻይና የሚመጣውን አማላይ ብድር በአግባቡ መጠቀም ስላልቻለች የተዳከመ ይመስላል፡፡

   ኢትዮጵያ እንደ በፊቱ ከቻይና ባንኮች የምታገኘው ብድር እየተገታ ይመስላል፡፡ በቅርቡ የቻይና ኤግዚም ባንክ ለ12 ግዙፍ የመሰረተ-ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ አለመቀላጠፍ ተከትሎ ሊሰጥ የነበረውን 339 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ብድር አግዷል፡፡

   ኢትዮጵያ ብድሯን በአግባቡ ልትመልስ አትችልም በሚል ምክንያት ከቻይና ልታገኝ የምትችለውን አማላይ ብድር አጥታለች፡፡ እንዲሁም ከሮድ ኤንድ ቤልት ኢኒሼቲቭ ልታገኝ ትችል የነበረው ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር ተገቷል፡፡ ይህ ሁሉ በኢትዮጵያ ጂኦ-ፖለቲካዊ ቀውስ እና ጂኦ-ኢኮኖሚካዊ መዳከም ላይ የራሱን አሉታዊ ሚና ይጫወታል፡፡

   የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና የዩክሬንሩሲያ ጦርነት      

   የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋት እና የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫና አሳድሯል፡፡ ወረርሽኙ የንግድ እና የአቅርቦት ዘርፉን በጣም ጎድቶታል፡፡ የተወሰኑ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት በወረርሽኙ ምክንያት የሐገሪቱ አገራዊ ምርት በዓመት ውስጥ በመቶኛ ከ4.3% እስከ 5.5% ድርሻ ዝቅ ብሏል፡፡ ይህ ደግሞ ለሐገሪቱ ኢኮኖሚ እንደ ነዳጅ የሚገለግለው የግንባታ ዘርፍ እንዲዳከም አድርጎታል፡፡ በእዚህም ምክንያት የዋጋ ንረቱ አስከፊ በሆነ ሁኔታ እንዲያሻቅብ ተገዷል፡፡

   በተለይም በቅርቡ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኃላ ችግሩ ተባብሷል፡፡ ጦርነቱ ወደ ሐገሪቱ የሚገባውን የምግብ አቅርቦት አዛንፎ የምግብ ቀውስ ፈጥሯል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ታክለውበት አስቀድሞ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ይንገላታ የነበረውን ኢኮኖሚ አሽመድምዶታል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በወጣው ሪፖርት እንደተሰማው ሐገሪቱ ያላት የውጭ ምንዛሬ ተቀማጭ ከአንድ ወር የማይዘል ወደ 1.6 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ብቻ ነው፡፡

   ቀጠናዊ የጂኦፖለቲካ ግጭቶች እና የኢትዮጵያ ተጋላጭነት      

   ኢትዮጵያ በምትገኝበት ቀጠና ከቅርብ ግዜያት ወዲህ ጠንካራ የጂኦ-ፖለቲካዊ ፉክክር እየተስተዋለ ይገኛል፡፡ አሜሪካ ከአካባቢው ከወጣች አንስቶ የመካከለኛው ምስራቅ ኃይሎች ማለትም ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቴስ፣ ኢራን እና ቱርክ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በቀጠናው ጂኦ-ፖለቲካ ውስጥ ሚናቸውን ለማሳደግ እየሰሩ ነው።

   ምስራቅ አፍሪካ እና የኢትዮጵያ ጂኦ-ፖለቲካ ራስ በርሱ የተሳሰረ ስለሆነ በቀጠናው የሚነሳ ችግር ወደ አረቡ ዓለም በቀላሉ የመስፋፋት ዕድል አለው።

   በቀይ ባሕር አከባቢ የሚነሱ የኃይል ፉክክሮች አሉታዊም አውንታዊም በኢትዮጵያ ላይ ማሳደራቸው አይቀሬ ነው። በእዚሕ ውስጥ ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ እና ግብፅ በአንድ ጎራ፣ ኢራንና ቱርክ በሌላ ጎራ ተሰልፈዋል።  ለእነዚህ ጎራዎች ኢትዮጵያ ምቹ የፉክክር የፍልሚያ ሜዳ ሆናለች። እነዚህ ግዙፍ የመካከለኛው ምስራቅ ኃይሎች በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ውስጥ የተለያየ የጂኦ-ፖለቲካዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የፌደራል መንግስቱን ይደግፋሉ።

   ሁሉም ኃይሎች የሚጋጭ የጥቅም ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ እጃቸውን አስገብተዋል። ይህ ጂኦ-ፖለቲካዊ ፉክክር የኢትዮጵያን ጉዳይ የማወሳሰብ እና የአካባቢውን የጂኦ-ፖለቲካዊ ቀውስ ያባብሳል።

   ለአብነት ቱርክ የግብፅ ተቀናቃኝ ስትሆን በአባይ ግድብ ጉዳይ ቱርክ ለኢትዮጵያ ድጋፍ በማድረግ ከግብፅ ተቃርና ልትቆም ትችላለች። የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የሶማሌላንድን ወደብ በሰፊ ድርሻ የራሷ አድርጋለች፣ ኢትዮጵያም ወደ ሐገር ውስጥ የምታስገባውን ምርት የጅቡቲን ወደብ ትታ በእዚሁ ወደብ በኩል እንድታስገባ ልታግባባ ትችላለች። በእዚህ የተነሳ ኤርትራ እና ጅቡቲ ሊንሳፈፉ ይችላሉ። ኢትዮጵያ ከኤርትራ የፈጠረችው ግንኙነት ከሶማሌላንድ ወደብ ጋር ሲደመር የኢትዮጵያ እና የጅቡቲን መልካም ግንኙነት ያሻክረዋል።

   እ.ኤ.አ በ2019 በሱዳን የተካሄደው የስልጣን ሽግግር እንዲሁም ግብፅን የሚደገፉ ኃይሎች ወደ ስልጣን መምጣታቸው ለኢትዮጵያ ለአከባቢው ጂኦ-ፖለቲካ መጥፎ ዕድል ነው። ከቅርብ ግዜያት ወዲህ ሱዳን እና ኢትዮጵያ በአባይ ግድብ እና በሚያዋስናቸው የድንበር አከባቢዎች ግጭት እያስተናገዱ ነው። ይህንን መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ግብፆች በአካባቢው ከኢትዮጵያ ጋር ለሚያካሂዱት የጂኦ-ፖለቲካዊ ውጊያ ጥሩ ዕድል ይፈጥራላቸዋል።

   የኃይል ግጭት እና አለመረጋጋት

   የኃይል ግጭት አንድም ውስጣዊ ተፅዕኖ አንድም ውጪያዊ ተፅዕኖ ያስተናግዳል። ውስጣዊ የኃይል ግጭት እየተባባሰ ሲሄድ የሐገሪቱ የውጭ ግንኙነትም አብሮ ይጎዳል፣ ያዳክማል።

   በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም እና ከአለም-አቀፍ ተቋማት ጋር ያላትን ግንኙነት አሻክሯል።

   እ.ኤ.አ በ2020 ማብቂያ የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ሊሰጥ ያሰበውን የበጀት ጉድለት ማሟያ ድጋፍ 1.9 ሚሊየን ዶላር እንዲቋረጥ አድርጓል።

   የትራምፕ አስተዳደር ለብቻው ጥሎት የነበረውን ማዕቀብ የባይደን አስተዳደር በትግራይ በሚታየው የኃይል ግጭት ምክንያት ማዕቀቡን አስቀጥሎታል። እንዲሁም አሜሪካ ኢትዮጵያን ከታክስ ነፃ ገበያ ወይም አጎዋ አግዳለች።

    

   ይሕ ከምዕራቡ ዓለም እና ከአለም-አቀፍ ተቋማት ጋር የተገባው ቅራኔ ይገኝ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ በማቋረጡ ምክንያት የሐገሪቱን የማሕበረ-ፖለቲካዊ ቀውሶች አባብሷል። በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የኃይል ግጭት ለቀጠናዊ እና አካባቢያዊ ጂኦ-ፖለቲካዊ ቀውስ እና ፉክክር ተጋላጭ አድርጓታል። በፌደራል መንግስቱ እና በህወሓት ኃይሎች መሐል የተቀሰቀሰው ጦርነት የሐገሪቱን የጂኦ-ፖለቲካዊ አስፈላጊነት አደጋ ውስጥ ሲከት፣ በኢትዮጵያም ቀውስ ቀስቅሷል።

   መደምደሚያ

   ስለዚህም በዓለም አቀፍ መድረክ እና በቀጠናው የሚስተዋለው የጂኦ-ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲሁም በሐገር ውስጥ ያለው የፖለቲካ ቀውስ የኢትዮጵያን የጂኦ-ፖለቲካዊ አስፈላጊነት ገሎታል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ጠንካራ የጂኦ-ፖለቲካዊ አጋርነቷ ተዳክሟል።

   ኢትዮጵያ የግብፅንና የአሜሪካን በአባይ ዙሪያ ያላቸውን የጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎት መረዳት ይገባታል። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ በግድቡ ሙሌት ዙሪያ ከሐገራቱ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ይኖርበታል። በሐገር ውስጥ የተከሰተውን የኃይል ግጭት እና አለመረጋጋት መፍትሄ ሊያበጅለት ይገባል።

   በተጨማሪም በቀጠናው ውስጥ ኃይላቸውን ይዘው የገቡት የመካከለኛው ምስራቅ ሐገራት ሊፈጥሩት የሚችሉትን ቀውስ በመረዳት፣ የሚያደርጉትን የኃይል ፉክክር በጥንቃቄ መያዝ ይገባዋል።

   ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም የምታገኘው ድጋፍ አስፈላጊ ስለሆነ የተፈጠረውን ውጥረት በማርገብ፣ ከሐገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ማሻሻል አለባት። እንዲሁም ብቁ የሆኑ የዲፕሎማቲክ ባለሙያዎችን መመደብ ተገቢ ይሆናል።

   * ሐጎስ ገ/አምላክ ለኢንፎርም አፍሪካ የሚሠራ ጋዜጠኛ ነው። 

   የአታሚው ማስታወሻ: ይህ ጽሑፍ ካርድ የወጣቶችን ሥልጡን እና ምሁራዊ የውይይት ልማድ ለማሳደግ “በወጣቶች የምክክር መድረኩ” ከሚያስተናግዳቸው ጽሑፎች አንዱ ነው።  በዚህ ዓምድ ለመስተናገድ ወይም ለዚህ ጽሑፍ መልስ ለመስጠት ከፈለጉ በ info@cardeth.org ላይ ኢሜይል ያድርጉልን።

Viewing 0 reply threads
Reply To: ኢትዮጵያ በቀጠናዊ ቀውስ ውስጥ
Your information: