ኢትዮጵያ የማን ናት?

Home Forums የወጣቶች መድረክ ኢትዮጵያ የማን ናት?

 • This topic is empty.
Viewing 0 reply threads
 • Author
  Posts
  • #3453 Reply

   በብፅዕት ዓለሙ

   የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ስንወያይ የ1960ዎቹን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄን (ኢ.ተ.ን) ማንሳት የግድ ይላል። ይህ ንቅናቄ በዛሬው ማኅበረሰብ የፖለቲካ ባህል ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ችሏል። በተለይም፡ ንቅናቄው ለረጅም ጊዜ በማህበረሰቡ ዘንድ እንደ ነውር ሲቆጠር የነበረውን የብሔር፣ የሃይማኖት እኩልነት እና የመሬት መብት ጥያቄን ሕዝባዊ ርዕሰ ጉዳይ እንዲሆን አድርጓል። በመሆኑም ኢ.ተ.ን በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ የለውጥ ምዕራፍ ተደርጎ ይወሰዳል።

   እ.ኤ.አ. በ1991 የደርግን ስርዓት ከጣለ በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1974 እስከ 1991 በነበረውን የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት በብሄር የተደራጁ ተፋላሚ ፓርቲዎችን መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ቅራኔ ለማስታረቅ የኢ.ተ.ንን ትሩፋት እንደወሰደ ይታመናል። በዚህ መሠረት ኢሕአዴግ የብሔር ፌደራሊዝምን የዘመናዊቷን ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች ስብጥር ለማስተናገድ እንደ አንድ የአስተዳደር ሥርዓት አቅርቧል። ይህ ሥርዓት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት ዋና ማዕከል ለመሆን  ይፋ ማድረግ ችሏል። አገዛዙ በብሄር ፌደራሊዝም አማካኝየብሄር ዕውቅና እና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትንነት የብሄር ብዝሃነትን ጉዳይ ለመፍታት ሞክሯል። ሆኖም፣ የነገሩ መደምደሚያ፣ ይህ የብሄር ፌደራሊዝም ጽንፍ የረገጡ የብሔረሰብ ጥያቄዎችን በመፍጠር ኢትዮጵያ  ፡ ብሄርተኝንት የፖለቲካ ግጭት ጎራዴ ወደ ተቀየረበት ሁኔታ ውስጥ እንድትዘፈቅ ካደረጓት ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ሆነ። የዚህ ችግር መፍትሄም እጅግ ውስብስብ እና በሀገረ መንግሥቱ የፖለቲካ እና ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ አወቃቀር ጋር በጥልቅ የተቆራኘ ነው።

   ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዝሃነትን ለማስተዳደር ከሁሉ የተሻለ መንገድን በተመለከተ ጽንፍ አመለካከቶች ኢትዮጵያን ከሁለት ተቃራኒ አቅጣጫዎች እየጎተቱ ይገኛሉ። በአንድ በኩል ብዝሃነትን ተቋማዊ በሆነ መልኩ የራስን ዕድል በራስ መወሰን እውቅና እንዲያገኝ የሚሟገቱ ሰዎች አሉ። በሌላ በኩል በብሄር ፖለቲካ በተፈጠሩ ክፍተቶች ምክንያት አሁን ላለው የአገሪቱ ራስ ምታት ብቸኛ መዳኛ የአንድነት ሀሳብ ነው የሚሉ አሉ። ይህ የወቅቱ ክርክር በ1960ዎቹ የኢ.ተ.ንን ሲመሩ የነበሩ ሁለት ቁልፍ ሰዎች፣ ዋለልኝ መኮንን እና ኢብሳ ጉተማ  አቋም ተጽዕኖ አድሮበታል። ሁለቱ የኢ.ተ.ን መሪዎች “ኢትዮጵያ የማን ናት?” እና “ኢትዮጵያዊ ማን ነው?” የሚሉ ጥያቄዎችን አጉልተው ለማሳየት የሞከሩ ናቸው፡፡

   ዋለልኝ መኮንን በ1969 እ.ኤ.አ የህዝቦችን እኩልነትና ፍትህ አስመልክቶ ጥልቅ ጉዳዮችን በማንሳት የብሔር ጥያቄን ወደ ፖለቲካው መድረክ ያመጣውን ጽሑፍ አሳትሟል። በጽሁፉም ውስጥ የውሸት ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት”ን ይነቅፋል ይህም “የአቢሲኒያ ባሕል” በሀገሪቱ ውስጥ የነበረውንና የፖለቲካ ምህዳሩን ከልዩ ልዩ ባሕሎች ጋር በመደባለቅ እና ሌሎች ባህሎችን በማግለል የፖለቲካውን መድረክ በማጥበብ  ያገለገለበትን ስርአት ተችቷል። እንዲሁም ዋለልኝ “አብዮቱ …… የመጨረሻ ዓላማው፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ሁኔታዎችን ተገቢው ግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያን ህዝብ ነፃ የማውጣት፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አብዮት በማድረግ እውነተኛ ህብረ ብሔራዊ ሀገርን ለመገንባት ጥሪ ያቀርባል። የሁሉም ብሔረሰቦች ባህላዊ ነፃነት  መከበር አለበት” ይላል፡፡ ይህ ከ1991 እ.ኤ.አ በኋላ ያለውን የፖለቲካ ምህዳር በበላይነት የተቆጣጠሩት የብሄረተኛ ኃይሎች መሠረት ሆነ።

   ዋለልኝ በኢትዮጵያ ውስጥ ለተለያዩ ቡድኖች እውቅና የመስጠት ጥያቄ ላይ አፅንዖት የሰጠ ሲሆን በጉዳዩ ላይም ጥብቅ አቋም ነበረው። ለራሳቸው አጀንዳ ብቻ የታገሉትን እንቅስቃሴዎች ይቃወም ነበር። ይልቁንም ዋለልኝ የሌሎችን ክልሎች ትግል ለመደገፍ እና እውነተኛ የኢትዮጵያን ብሄራዊ መንግስት በአንድነት ለማምጣት ዓለም አቀፋዊ አመለካከትን ይፈልጋል። ሆኖም፣ የእሱ ድክመት እውነተኛ ብሄራዊ ሀገርን ለመገንባት ብቸኛው አማራጭ በአመፅ እና የትጥቅ ትግል የታጀበ አብዮት ነው የሚለው ነበር። እዚህ ላይ፣ ዋለልኝ ራሱ ያነሳቸው ጉዳዮች በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ጥልቅ ስለመሆናቸው እና ሁሉንም ህዝቦች የጋራ አጀንዳ እና መርሆዎች ዙርያ ማደራጀት እንዲሁም ሌሎች በቅድሚያ መመለስ ያለባቸው ብዙ ጥያቄዎች መኖራቸውን ዘንግቷል።

   ሌላው የኢ.ተ.ን ዝነኛ አቀንቃኝ የነበረው ኢብሳ ጉተማ በፖለቲካዊ ዕውቀት በተቃኘ ግጥም በወቅቱ የነበረውን የሀገሪቱን ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ የሚፈታተን ነበር። ግጥሙ “ኢትዮጵያዊ ማን ነው?” የሚለውን ቁልፍ ጥያቄ የሚዳስስ ሲሆን በዚህም የብሔር ጥያቄ  ጽንፎችን በግጥም ያሳያል። ኢብሳ ከ “ኢትዮጵያዊነት” ይልቅ በወቅቱ የነበረውን የብሔር ማንነት እና የመደብ ባለቤትነት ዝንባሌን አጉልቶ አሳይቷል። ኢትዮጵያዊ ማንነት እና የአንድነት ትልቁን ምስል ወደ ማደብዘዝ የሚያመሩ ክፍተቶችን የፈጠረ የመደብ እና የብሔር ፖለቲካ የሚያመጣው ድምር ውጤት ያሳስበው ነበር።

   ኢብሳ መከፋፈሉ ከተባባሰ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ በተመለከተ ከመጨነቁ የተነሳ “ኢትዮጵያዊ ማን ነው?” የሚል ጥያቄን እንዲህ ሲል ጠይቋል፡ –

   “ጥበበኞች ሆይ ፣ እስኪ ንገሩኝ

   ኢትዮጵያዊ ማን ነው? ይህን እንቆቅልሽ ፍቱልኝ ”

   ሊያስተላልፈው የፈለገው መልእክት ሁላችንም በተናጥል ማንነት ላይ ተመስርተን በተለያዩ ቡድኖች ውስጥ ብንመደብ ስለእነማን ኢትዮጵያ  እያወራን ነው? ሲል ይጠይቃል፡፡ እሱ በመደብ ወይም በጎሳ መጠለያ ውስጥ የሚደበቁ ሰዎችን ዝንባሌ ይተቻል። ኢብሳ በመደብና በጎሳ ብሔርተኝነት ከሚደረግ ቅስቀሳ ሁላችንም ወደ ተወለድንበት ግዛት ኢትዮጵያ እንድናዘነብል ቅስቀሳ ሲያደርግ መታወስ ያለበት መፍትሔ ምን እንደሆነ ማወቅ ይፈልግ ነበር።

   ዋለልኝ እና ኢብሳ የህዝቡን ማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ህይወትን በጥልቀት በመመርመር ተገቢ ውይይቶችን ወደ እይታ አምጥተዋል። በተወዳዳሪ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የክርክር ምንጭ ሆነው ቆይተዋል እኚህ ጥያቄዎቻቸው አሁንም ገና አልተመለሱም። በአሁኑ ጊዜ በፖለቲካ መድረኩ ላይ ሁለት ዋና ዋና ክርክሮች እንዳሉን ግልፅ ነው፤ አንዱ ለዘመናት ሳይነካ ለነበረው ብዝሃነት እውቅና ከመስጠት ጋር ይዛመዳል፣ ስለሆነም የማንነት ዕውቅና እና ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ለማግኘት በብሔር ብሔረሰብ ላይ የተመሠረተ አደረጃጀት እና ቅስቀሳ ያስፈልጋል የሚል ነው። ሌላው ከብሔር ንቅናቄ ጋር በመጋፈጥ ከአንድነት ጋር የሚገናኝ ሲሆን “በኢትዮጵያ ብሔርተኝነት” ላይ የተመሠረተ አንድነት የሚጠይቅ እና የብሔር ብዝሃነትን ተቋማዊ ያደረገ የብሔር ፌደራሊዝም እንዲፈርስ ሐሳብ አቅርቧል። በእነዚህ ቡድኖች መካከል ያለው ፉክክር የዋለልኝ እና የኢብሳ ጥያቄዎችን እና ስጋቶችን እንደገና እንድናነሳ ያስገድደናል። ነገር ግን፡ አሁን ላይ ፍትሃዊ ለሆኑት ግን ለተዛባ አረዳድ ለተዳረጉት ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ስንፈልግ የኢሕአዴግ አገዛዝ እንዳደረገው አንሳሳትም።

   የዋለልኝ ጽሑፍ የብሄር ማንነት እውቅና፣ የፍትህ እና የእኩልነት ጉዳይን ለመፍታት ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያ የብዙ ብሄረሰቦች ሀገር መሆኗን  እና ብዝሃነታችንን መካድ ከቀጠልን አሁን ላለው ትርምስ መፍትሄ ማግኘት አንችልም። ያንን እስካልተቀበልን ድረስ፣ ወደ ፊት መራመድ አንችልም። ምክንያቱም በታሪክ የሚነገር የብሔረሰቦች ዕውቅና ማጣት ወደ ቅሬታዎች ስለሚመሩ እና ቀደም ሲል ለደረሰው ጉዳት የማካካሻ ጥያቄዎች ስለሚቀርብ ነው። በአንድነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ከሚያሳድር የእውቅና ጉዳይ ጋር የተዛመዱ ጥያቄዎችን ካልተመለከትን፣ እንዲሁ መፈረጅ  ብጥብጥን እና ግጭትን ይጨምራል። ስለሆነም ብዝሃነትን ዕውቅና በመስጠት፣ ያለፈውን ኢ-ፍትሐዊነት በመካስ እና እርስ በእርስ በመደጋገፍ ለሀገር ህልውና መሠረታዊ መፍትሄዎችን የመፈለግን አስፈላጊነት መቀበል አለብን።

   ዛሬ የብሄር ማንነት በፖለቲካ ተሞልቶ ተፎካካሪ ብሄርተኝነት ጫፍ ላይ ደርሶ እራሱን በፖለቲካ ስልጣን፣ በትጥቅ ትግል እና በአክራሪነት የተገለጥበት ደረጃ ደርሷል። የታጠቁ ቡድኖች መበራከት ከታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነት ንግርቶች/ትርክቶች ጋር በመሆን “እኛ” እና “እነሱ” በመባባል አንዱ ሌላውን “የእኛ” ክልል ነው ብለው ከሚያምኑበት ቦታ የሚያባርርበትን “የብሔረተኛ ቡድኖች” አለመቻቻል እና ግጭትን ወደ መባባስ እያመሩ ይገኛሉ። በመሆኑም፡ እዚህ ላይ መሰመር ያለበት፡ የመሬት ጥያቄ የችግሩ መሰረት ሆኗል፤ እንደ አለመታደል ሆኖ ለዚህ ጥያቄ መልስ ማግኘት አልቻልንም እንጂ።

   ዘመናዊው የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምስረታ ሂደት የተለያዩ የብሄር ብሄረሰቦች አብረው እንዲኖሩ በመደረጉ የአሁኑን የኢትዮጵያ ካርታ አስገኝቷል። ጠንካራ እና ተወዳዳሪ የሆነው አሸናፊ የሚሆንበት  የዓለም የፖለቲካ ስርአት ውስጥ አንድ ጠንካራ መንግሥት ለመመስረት ወደ አነስተኛ ብሔር ከመከፋፋል ይልቅ አንድነትን ማጉላት ለታላቅነት ይብጃል። ስለሆነም፡ ህብረ ብሄራዊነት የሚንጸባረቅባት የኢትዮጵያን አንድነት በመተው ወደ ነበረችበት ለመመለስ ከመሞከር ይልቅ የሁሉንም ማኅበራዊ ቡድኖች በሚያካትት አኳኃን ውስጣዊ በሆነ እይታ ሀገር በቀል ዕውቀትን፣ እሴቶችን እና ወጎችን እውቅና በመስጠት ኢትዮጵያን የበለጠ አካታች ማድረግ ይሻላል። ዛሬ ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ዓለምን ወደ አንድ መንደር ያመጣበት እና አብሮነትን ያሰረፀበት ጊዜ ሲሆን በሁሉም ቦታ በጉልህ የሚታየውን ብዝሃነታችንን አለማክበር እና እንደ ውድ ሀብት አለመጠቀማችን ተገቢ አይደለም።

   ከላይ እንደተብራራው፣ በእንደዚህ ዓይነት ብዝሃነት ውስጥ የተለመደው አንድነትን ለመጠበቅ፣ የብሔር ብሔረሰቦችን ይሁንታ ማግኘት የሚያስችል አውራ መርህ መኖር አለበት። ጥያቄው እንደ አስተማማኝ መጠጊያ በምንወስደው ቦታ ላይ እኛን አንድ ለማድረግ ምን ዓይነት መርሆዎች ሊያገለግሉ ይችላሉ የሚለው ነው። በእያንዳንዱ ብሄር ውስጥ አባላቱ የሚያደንቁትና እውቅና እንዲሰጣቸው የፈልጉት የዴሞክራሲ መርሆዎች አሉ። የብሄሮችን የእውቅና ፍለጋ ከተረዳን፣ ለባህላዊ እሴቶች እውቅና መስጠት ብቻ ሳይሆን ለሚመለከታቸው ባህላዊ ዴሞክራሲያዊ ልማዶች እውቅና ማግኘትን የሚያካትት መሆን ይኖርበታል። እንደ እድል ሆኖ ሁሉም ማህበረሰቦች ከሌሎች ጋር መቻቻል እና መከባበርን መሠረት ያደረገ የዴሞክራሲያዊ ባህል አላቸው።

   ታሪክን፣ ተዛማጅ ባህላዊ አሰራሮችን፣ ሀገር በቀል ዴሞክራሲያዊ መርሆዎችን እና ትውፊቶችን በማጥናት ላይ ያተኮሩ ጠንካራ አገር በቀል ተቋማትን ማቋቋም በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም፡ ሕዝባችንን እስካላወቅን ድረስ እኛ የምንወስደው መፍትሔ በግድ የጫንንባቸው ውሳኔ ይሆናል። ስለዚህ ተቋማቱ ህዝቦች በዚህ መንገድ ለመገዛት ዝግጁ የሆኑ አካታች ዴሞክራሲያዊ መርሆዎችን ለማውጣት ጠቃሚ ናቸው። ብሔራዊ ፖሊሲዎች የምንቀረጸው ልክ ዋለልኝ እንደሚለው በእኩልነት ላይ የተመሠረት መንግስት በማቋቋም ሀሳብ ሲሆን ይሄውም “እውነተኛ ብሄራዊ-መንግሥት በአገር በቀል ተቋማት አማካይነት ሁሉም ብሔረሰቦች በመንግስት ጉዳዮች እኩል የሚሳተፉበት” ተቋማት መገንባት ይቻላል።

   ሁለቱም ጽንፍ የያዙ አቋሞች ማለትም “ብሔርተኝነት” (ሌሎችን አለመቀበልን ወይም የ “እኛ” እና “እነሱን” ክፍፍል የሚያራግብ) እና “ኢትዮጵያዊነት” (ለብዝሃነት እውቅና የማይሰጥ) ጽንሰ-ሀሳቦች በጣም አፍራሾች ሲሆኑ ለአሁን ጊዜ ለሚስተዋሉ ትርምስ መሠረታዊ ተጠያቂ ናቸው። ስለሆነም ጉዳዩ በጣም ውስብስብ እና ስለ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ጥልቅ ግንዛቤ የሚፈልግ ስለሆነ በዚህ ረገድ ለምናቀረበው ሀሳብ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት አለብን። በተለያዩ ቡድኖች የሚቀርቡት አብዛኛዎቹ ጥያቄዎች የሚመነጩት የእኩልነት፣ የፍትህ፣ እና የእውቅና ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ናቸው። በተጨማሪም ከሁሉም በላይ መልስ ያልተሰጠው የመሬት ጉዳይ የጥያቄዎቹ መነሻ ሲሆን ሕልውናችን በእሱ ላይ የተመሰረተ ነው።

   ለመጪው ትውልድ ነገሮችን ግልጽ ለማድረግ ከፈለግን “ስለ የትኛዋ ኢትዮጵያ  እያወራን ነው?” እና “ኢትዮጵያ የማን ናት?” ለሚለው የኢብሳ ጥያቄ መልስ ማግኘት አለበት። በተጨማሪም፣ ሰዎች አመክንዮአዊ መርሆዎች (ማለትም የማንነት ዕውቅና እና ፍትህ) ላይ ለመኖር የሚያደርጉትን ትግል ልብ የሚሉትን የዋለልኝን ግንዛቤዎች ማስታወስ አለብን። ይሄውም፡ ትግሉ ለአንድ ለተወሰነ ክልል ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ክልሎች እውነተኛ የኢትዮጵያን ግዛት ለመገንባት ሁሉም በተስማሙበት ዴሞክራሲያዊ መርሆዎች እንዲገዙ ሁሉም በራሳቸው ፈቃድ አብረው ለመኖር የተስማሙበትን ኢትዮጵያን መገንባት ይቻላል (እኔ በስምምነት ህብረት ላይ የጸናች ኢትዮጵያ ብዬ ለመጥራት እመርጣለሁ)። መርሆዎቹም አካባቢያዊነትን፣ ክልልን እና አልፎ ተርፎም ግዛትን ስለሚሻገሩ መሆን መቻል አለባቸው። ብዝሃነታችንን ለማስተዳደር እና ለማስተናገድ ሁሉንም በእውነተኛነት በሚወክል እና አሳታፊ የሆነ ዘዴ መከተል አለብን። በዚህ መንገድ ሁላችንም የምናደንቀውን፤ የእኛነታችንን እንዲሁም የሀገር ባለቤትነታችንን የምንጠይቅበትን፤ ለጥያቄው በኩራት መልስ የምናገኝበት እና ሁሉን አቀፍ አንድነት ላይ የተመሰረተች ሀገር ከገነባን በኋላ “ኢትዮጵያ የእኛ ነች፣ ኢትዮጵያዊ እኛ ነን” በሚለው ሀሳብ ላይ መስማማት እንችላለን።

Viewing 0 reply threads
Reply To: ኢትዮጵያ የማን ናት?
Your information: