እውን “ኢትዮጵያ በቀጠናዊ ቀውስ ውስጥ” ነች?

Home Forums የወጣቶች መድረክ እውን “ኢትዮጵያ በቀጠናዊ ቀውስ ውስጥ” ነች?

 • This topic is empty.
Viewing 0 reply threads
 • Author
  Posts
  • #4215 Reply

   በቃልኪዳን ሙሉ ቢተው

   ኢትዮጵያ ላለፉት አራት ዓመታት ገዢው ፓርቲ በውስጡ ባካሄደው ማሻሻያ እንዲሁም የዶ/ር አቢይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ሐገሪቱ በ”ለውጥ” መንገድ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ለውጥ ማለት በአንዳች የግዜ ክበብ ውስጥ የሚካሄድ ፈጣን ሽግግር እና የወሣኝ ነገሮች መቀየር ነው፡፡ እኛም በእዚህ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ ለውጥ ውስጥ እያለፍን እንገኛለን፡፡

   ሐጎስ ገ/አምላክ በጽሁፉ ውስጥ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ጂኦ-ፖለቲካዊ ቀውስ፣ በዓለም-አቀፍ ንፍቀ-ክበብ ውስጥ እና በቀጠናው ያለውን የኃይል አሰላለፍ፣ እንዲሁም መረጃዎችን ከማሳያዎች ጋር በማንሳት ሐገራችን የገባችበትን የጂኦ-ፖለቲካዊ ቀውስና የጂኦ-ፖለቲካዊ ጠቀሜታዋ መዳከሙን ለማሳየት ሞክሯል፡፡ እንደ ጽሁፉ ኢትዮጵያ በውስጣዊ እና በውጫያዊ የፖለቲካ ተጽዕኖ እና ለውጥ ምክንያት የነበራት ጂኦ-ፖለቲካዊ ሚና ተዳክሟል፡፡ ጸሐፊው በጽሁፉ ውስጥ በዋናነት ያሳየው በመደምደሚያውም ለማረጋገጥ የሞከረው ኢትዮጵያ የገጠማትን ኃይልን በእጅ አስገብቶ መምራት የመቻል ክፍተትን ነው፡፡ ሌላው በጽሁፉ የተነሳው ነጥብ የአባይ ግድብ እና ከግድቡ ጋር ተያይዞ ሐገሪቱ የገጠማት ውጪያዊ ጫና፣ አሜሪካ በህንድ-ፓስፊክ ቀጠና ላይ የሚያተኩር ዲፕሎማሲዊ ለውጥ ማድረጓ እና የአሜሪካ ውስጣዊ የፖለቲካ ለውጥ ሲሆን በተጨማሪም የቻይና አማላይ ብድር መዳከም፣ የኮሮና ወረርሽኝ እና የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት፣ እንዲሁም ቀጠናዊ የኃይል ሽኩቻ እና የኢትዮጵያ ተጋላጭነት፣ በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የነፍጥ ግጭት እና አለመረጋጋት ናቸው፡፡

   ጸሐፊው የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የውጫያዊና የውስጣዊ ፖለቲካ ጉዳይ ብቻ በማድረግ ቀንብቦታል፡፡ ይህ ጽሁፍ ያነሳቸው መከራከሪያዎች ስለሀገሬ ባለኝ የፖለቲካ አመለካከት ላይ ወቅታዊዉንና ቀጣይ የሀገራችን እጣ ላይ የራሴን ምልከታ እንዳንጸባርቅ አስገድዶኛል፡፡

   ጽሁፉ መሳል የፈለገው በአዲሱ አስተዳደር ኢትዮጵያ ያለፈችባቸውን ታሪካዊ ዱካዎች፣ በተጨማሪም ይህ አስተዳደር ከአሜሪካ እና ከአለም-አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የተነፈገውን ድጋፍ ነው፡፡ በኔ አረዳድ የአባይ ግድብ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መነቃቃት ሰንደቅ እና የጀርባ አጥንት የሚሆን ትሩፋት ነው፡፡ በርግጥ ከጸሐፊው መከራከሪያ ጋር የምስማማው በአሜሪካ እና በሌሎች አበዳሪ የፋይናንስ ተቋማት ለኢትዮጵያ ቃል የተገባው ብድርና ድጋፍ የተቋረጠው ከአባይ ግድብ የውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ የአሜሪካ ሁነኛ አጋር የሆነችውን ግብጽን ለመደገፍ በማሰብ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቀጠናዊ ተጽዕኖ በግብጽ ላይ ባሳደረው ስጋት ምክንያት ኢትዮጵያ ላይ ተከታታይ ማዕቀብ እና ግፊት በከፍተኛ መልኩ ተጠናከሯል፡፡ ለአፍሪካ የሚደረገው እርዳታ፣ ብድርና ድጋፍ ምንም እንኳ ለአኅጉሩ ኢኮኖሚ መሻሻል የሚያበርክተው አስተዋጽኦ ባይኖርም፣ እነዚህ የውጭ ድጋፎች በድንገት መቋረጥ ቀድሞም በተዳከመው ኢኮኖሚ ላይ የራሱን አሉታዊ ጠባሳ አሳድሯል፡፡ አንድ ሉዓላዊ ሐገር ካጋጠማት ችግር በፍጥነት መውጣት የሚያሳየው፣ በዋናነት በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ሐገሪቱ ያላትን ነጻነት ነው፡፡ ዳሩ ግን እንደ ጸሀፊው ትንታኔ በዓለም-አቀፉ ፖለቲካው ውስብስብነትና እንዲሁም በሐገሮች መካከል ባለው ጥብቅ ትስስር የተነሳ ውስጣዊ ችግር ለጂኦ-ፖለቲካዊ ቀውስ መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡ በተጨማሪም ጽሁፉ የአባይ ግድብን ቀውስ ተከትሎ ውጪያዊ ተጽዕኖ በሀገሪቱ ላይ ተጠናክሯል፡፡ በተለይም በህወሓት እና በፌደራል መንግስቱ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ጉዳዩን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” አድርጎት፣ ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም እና ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያላትን ግንኙነት አሻክሮታል፡፡ ኢትዮጵያ ጂኦ-ፖለቲካዊ አስፈላጊነቷ ቢያበቃ ኖሮ ድርድር የሚባለውን ሐሳብ ጠረጴዛ ላይ የሚያስቀምጥ ኃይል አይኖርም ነበር፡፡ ያለው ሁኔታ ይህንን አያሳይም ስለዚህም ውስጣዊ ዝግጁነት፣ አቅም ግንባታ እንዲሁም ውስጣዊ ሰላምን ማጠናከር ቅድሚያ ተሰጥቶት በጋራ ሊሰራ ይገባል፡፡

   ብዙዎች የሚከራከሩት የቻይና ግዙፍ ብድር እና ድጋፍ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ መነቃቃት ወሳኝ መሆኑን ሲሆን እንዲሁም በረዥም ሂደት ግን የከፋ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንደሚያስከትል ነው፡፡ ምንም እንኳ ሐጎስ ባነሳቸው የጂኦ-ፖለቲካዊ ቀውስ እና የጂኦ-ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ብስማማም፣ የብድር እና የድጋፍ ጥገኛ መሆን ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ይጠቅማል ብዬ አላስብም፡፡ ከውጭ የምናገኘው የ30 ቢሊየን ዶላር ብድር ጠንካራ የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚ እና ማሻሻያ ከመገንባት ይልቅ ኢኮኖሚያዊ ጥገኝነታችንን የሚጨምር ነው፡፡ እኔ እንደማምነው የኢህአዴግ ስርዓት ያገኘውን ግዙፍ ድጋፍ እና እርዳታ ባይቀበል አሁን ከሰራው የተለየ ነገር አይሰራም ነበር፡፡ በመንገድ ሴክተር ላይ ተሳትፎ እንደነበረው አንድ ግለሰብ በእኔ እይታ ቻይና ለመንገድ ሴክተር በተለይም ለግዙፍ ግንባታዎች ዋነኛ ገንዘብ እና ባለሙያ (ኤክሰፐርት) አቅራቢ ሐገር ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ በግንባታው ዘርፍ በውጭ ድርጅቶችና እውቀት ላይ መመስረቷ የሐገር ውስጥ የዘርፉ ባለሐብቶችን ሚና አኮስሷል፡፡ ምንም እንኳ ስለሴክተሩ በሚነሱ ቅሬታዎች፣ እንዲሁም የውጭ ካምፓኒዎች በሐገር ውስጥ መንሰራፋትን ተከትሎ በሚነሱ ጉዳዮች ላይ፣ የእውቀት ሽግግር በአዎንታ ተጠቃሽ ቢሆንም፣ እውነታው ግን እንደሚባለው መሬት ለመውረዱ ጥርጣሬ አለኝ፡፡

   አዲሱ አስተዳደር ይፋ ያደረገው “ሐገር-በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ” የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንዳያሻሽል በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት እንቅፋት ገጥሞታል፡፡ አዲሱ አስተዳደር ሰፊ ትኩረት እና ዋጋ የከፈለበት የቱሪዝም ሴክተር ሲሆን፣ በወረርሽኙ ምክንያት የአለም የቱሪዝም ዘርፍ እንዲፋዘዝ ተገዷል፡፡ ጸሀፊው በጽሁፉ የወረርሽኙ መስፋፋት የሐገራችንን ኢኮኖሚ እንደጎዳ ቢያብራራም፣ እንደ እኔ እምነት በእዚህ ተጎጂ የሆነችው ሐገራችን ብቻ ሳትሆን፣ ዓለም በጠቅላላው ነው፡፡

   የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስጠነቀቀው የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት የምግብ ዋጋ እንዲጨምር እንደሚያደርግ እና በአፍሪካ ያለውን ችግር እንደሚያባብስ ነው፡፡

   ጄኔቭ፣ በሚያዚያ 26 (ሮይተርስ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ ማስተባበሪያ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊዝ እንዳሉት በምስራቅ አፍሪካ ወደ ሁለት ሚሊየን የሚጠጉ ህጻናት በአስርት ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ ምክንያት ለአስከፊ ረሀብ ተጋልጠዋል፡፡

   ከፊል ኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በ40 ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ እየተሰቃዩ ነው፡፡

   የአለም ኢኮኖሚ ፎረም እንደገለጸው የአለምን 60% የሚታረስ መሬት የያዘችው አፍሪካ የምግብ እህል በመግዛት በአለም ላይ ትልቁን ድርሻ ትይዛለች፡፡ ዩክሬን እና ሩሲያ በጋራ የአለምን 30% እህል አቅራቢ ናቸው፡፡ እንዲሁም ሩሲያ 13% የአለማችንን ማዳበሪያ አምራች ነች፡፡ ዩክሬን በበኩሏ ለአለም ግማሹን የሱፍ ዘይት አቅራቢ ሐገር ነች፡፡

   በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት ብዙ ገበሬዎችን ከቀዬያቸው እንዲፈናቀሉ ሲያደርጋቸው፣ በተጨማሪም ትኩረታቸውን ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ወደ መከላከል እንዲመልሱ አስገድዷቸዋል፡፡ በእዚህ ምክንያት የሀገር ውስጥ ምርት እንዲቀንስ ሆኗል፡፡ ይህ ከምግብ ዋስትና እጦት እና ከዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ጋር ተዳምሮ አሁን የምንገኝበትን ቀውስ አስከትሏል፡፡

   በጽሁፉ ውስጥ በግልጽ እንደተቀመጠው የማይታዩ አለም-አቀፍ ተጽዕኖዎች እንዲሁም ሐገራዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ኢትዮጵያ የነበራትን ጂኦ-ፖለቲካዊ አስፈላጊነት እንድታጣ አድርጓታል፡፡ እዚህ ጋር የማልስማማው በእዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ የምታገኛቸውን የውጭ ስምምነቶች እና ውሎች እንድትቀበል የሚመክረውን ሃሳብ ነው፡፡ ጸሐፊው ኢትዮጵያ በአባይ ግድብ ሙሌት ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረስ አለባት ብሎ ይመክራል፣ እኔ በእዚህ አልስማማም፡፡

   ከአቶ ሐጎስ ጋር በእዚህ ነጠላ ሐሳብ ላይ ልዩነት አለኝ፣ ምክንያቱም ይህ ጉዳይ ስትራቴጂያዊ በሆነ መንገድ ሊተነተን እና ሊብራራ የሚገባው ነጥብ እንጂ፣ እንዲሁ በአጭሩ መፍትሔ ላይ የሚደረስበት አይደለም፡፡ ከእዚህ ይልቅ ወደፊት ሐገራችን ልትደርስበት የምትችለውን ቦታ ግምት ውስጥ የሚከት መሆን አለበት፡፡

   ከፀሐፊው ጋር የምስማማበት የማጠቃለያ ሐሳብ ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቷን ለማመጣጠን መስራት አለባት በሚለው ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት እና በእዚህ ዘመን የትኛውም ሐገር ራሱን ከመሰሎቹ ነጥሎ መዝለቅ አይችልም፡፡ ስለዚህም በወሳኝ መልኩ የራሱን ሁኔታ በመገምገም የጂኦ-ፖለቲካዊ አስፈላጊነቱን ለማሳደግ የራሱን ስልት ነድፎ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ እንደ ሉዓላዊ ሀገር ኢትዮጵያውያን የምናደርጋቸው የውጭ ስምምነቶች ዘላቂ ጥቅማችንን እና ዕድላችንን ታሳቢ ሊያደርግ ይገባል፡፡ ከእዚህ ይልቅ ስሜታዊ የሆነ ከኃያላን ሐገራት ጋር የሚደረግ ግንኙነት ጊዜያዊ የበላይነት አማራጭ ይኖራቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ማድረግ ያለባት በቀጠናው እና በአሕጉሩ ውስጥ ጠንካራ የሚያደርጋት ስትራቴጂ መንደፍ ነው፡፡

   * ቃል ኪዳን በሙያዋ የኢንጂነሪንግ ምሩቅ ስትሆን፣ በጅምር ንግድ ሥራዎች እና ቢዝነስ ግንባታ ላይ እየሠራች ትገኛለች። 

   * የአታሚው ማስታወሻ: ይህ ጽሑፍ ካርድ የወጣቶችን ሥልጡን እና ምሁራዊ የውይይት ልማድ ለማሳደግ “በወጣቶች የምክክር መድረኩ” ከሚያስተናግዳቸው ጽሑፎች አንዱ ነው።  በዚህ ዓምድ ለመስተናገድ ወይም ለዚህ ጽሑፍ መልስ ለመስጠት ከፈለጉ በ info@cardeth.org ላይ ኢሜይል ያድርጉልን።

Viewing 0 reply threads
Reply To: እውን “ኢትዮጵያ በቀጠናዊ ቀውስ ውስጥ” ነች?
Your information: