የትውስታ ኣባዜ ወይስ የተዛባ የአገር ግንባታ?

Home Forums የወጣቶች መድረክ የትውስታ ኣባዜ ወይስ የተዛባ የአገር ግንባታ?

 • This topic is empty.
Viewing 0 reply threads
 • Author
  Posts
  • #3342 Reply

   በአስራት አብርሃም*

   በጸባኦት መላኩ የተጻፈው “Ethiopia: a state in an obsession with fait accompli” በሚል ርዕስ የቀረበ ጽሁፍ አነበብኩት። ጽሁፉ ኢትዮጵያ ካለፈው ታሪክና የፖለቲካ ሂደቶች ተሰንቅሮ የመቅረት ኣባዜ ውስጥ እንዳለች የሚያሳይ ነው። ሀሳቡ በከፊል እውነትነት ያለው  ሆኖ ይሰማኛል። ነገር ግን በደንብ ላስተዋለ ሰው አሁናዊ ችግሮቻችን “ያለፈ ነው” ከሚባለው የታሪክ ክንውኖች የሚመነጩና ገና ያለተዘጉ ጉዳዮች እንዳሉት መረዳት ያስፈልጋል። በአገራችን አልፈው ያላለፉ ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ የውጫሌን ውል መወሰድ እንችላለን። አጼ ዮሃንስ መተማ ላይ እንደተሰዉ፣ በሸዋው ንጉስ ምኒልክ እና በኢጣሊያ መንግስት ተወካይ መካከል የተደረገው ውል ኢጣሊያ በኢትዮጵያ መሬት ላይ ህጋዊ ይዞታ እንዲኖራትና ኤርትራ የምትባል አገር እንድትፈጠር ምክንያት የሆነ ነው። ይሁን እውነታ በአድዋ የተገኘውን ድል እንኳ ሊቀይረው አልቻለም። ከጦርነቱ በኋላ ከኢጣሊያ ጋር  የተደረጉት ስምምነቶች “ኢትዮጵያ ከውጭ መንግስታት ጋራ ራሷን ችላ በቀጥታ ግንኙነት ማድረግ ትችላለች” ከሚለው በስተቀር በውጫሌ ውል ላይ የተቀመጡት ሀሳቦች አልተሰረዙም። እንዲያውም ከጦርነቱ ጥቂት ሳምንታ በኋላ ፈረስማይ በተደረገ ውል ኢጣሊያ አኩለጉዛይና ሰራየን ጨምሮ መረብ ምላሽ ያለውን ቦታ እንዲሰጣት ሆኗል። የኢትዮጵያ ታሪክ ከማይነግረኝ ታሪካዊ ክንውኖች አንዱ ነው። ይሄ እንደምሳሌ አነሳሁት እንጂ ብዙዎቹ ያሉ የሚባሉት የታሪክ ክንውኖች በአሉታዊ ይሁን በአዎንታዊ ጎናቸው በዛሬው ህይወታችን ላይ የሚንጸባረቁ በመሆናቸው ነው እንደአገርም እንደ ህዝብም ባለፈው ነገር ላይ ተሰንቅረን እንድንቀር የሆነው የሚል እምነት ነው ያለኝ።

   በመሰረቱ ግን የኢትዮጵያ ዋነኛ ችግር ካለፈው ታሪክ ወይም የፖለቲካ ክንዋኔ ላይ ተሰንቅሮ የመቅረት ኣባዜ የፈጠረው ሳይሆን የተዛባ የአገር ግንባታ ሂደት በመኖሩ ነው የሚል እምነት አለኝ። እንደሚታወቅው የዘመናዊት ኢትዮጵያ የአገር ግንባታ መሰረት የያዘው በአጼ ምኒልክ ጊዜ ነው። በውጫሌ ውል ኤርትራን ለኢጣሊያ ሰጥተው፣ በደቡብ በምስራቅና በምዕራብ ያሉትን ልዩ ልዩ ህዝቦች በሃይልም በውዴታም የግዛታቸውን አካል እንዲሆኑ ካደረጉ በኋላ፣ በዙሪያቸው ከነበሩት የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ጋር የድንበር ውሎችን በማድረግ አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ በአዲስ ቅርጽ ለማንበር አስችሏቸዋል። ይህ በራሱ ይዞት የመጣ ብዙ መልካም እድሎች የነበሩት ያህል፣ ሌሎች ደግሞ በሂደት ችግር እየሆኑ የሚሄዱ ጉዳዮችንም አብሮ ይዞ መጥቷል። ከሁሉም ነገር በላይ ደግሞ የአገር ግንባታው በሸዋ የፖለቲካ የበላይነት፣ በአማርኛ ብቸኛ የመንግስት ቋንቋ መሆን፣ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ የመንግስት ሃይማኖት ላይ የተመሰረቱ አግላይና ጨፍላቂ የሆነ የአገር ምስረታ ሂደት መጀመሩ ነው። በዚህ ምክንያት ደግሞ በግዛቱ የነበሩት ህዝቦች ቅሬታ ውስጥ እንዲገቡ፣ ቂም እንዲቋጥሩ የሚያደርግ ሁኔታ ነው የተፈጠረው። አንደኛ በግዛቱ የነበሩ ህዝቦች ማንነታቸውን እየተዉ በሂደት አማርኛ ተናጋሪ ዜጎች የመፍጠር የአንድ ዓይነት አንድነት ፖሊሲ ነው፣ በዚህ ላይ ደግሞ የአገር ግንባታው አሳታፊነት ያልነበረው፣ እጅግ ሲበዛ አግላይ ነበር ብሎ ደፍሮ መናገር የሚያስችል ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን የነጋድራስ የገብረሕይውት ባይከዳኝ ፅሁፍ ነው። በቀደምቱ ዘመናት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውሣኝ ሚና የነበራቸው የትግራይና ጎንደርና ልሂቃን ሳይቀር ያገለለና እንደባዕድ እንዲታዩ የሚያደርግ እንደነበር ራሳቸው በአካል የታዘቡትን እንዲህ አስቀምጦውታል፦

   “ትልቅ የሆነ የቤተ መንግስት ሹመት ሁሉ ይልቁንም የሚኒስትርነት ስራ በሸዋዎች እጅ ብቻ ነው። የትግሬ፣ የስሜን፣ የበጌምድር፣ የላስታ፣ የጎጃም ልጅ የሆነም ሁሉ  እንደውጭ ሰው እየተቆጠረ ከትልቅ የመንግስት ምክር አይገባም። ትምህርት ስለሌለው ግን የስሜን ሰው የዚህን ነገር ውርደት ገና አያስተውልም። በዚህም ምክንያት በሌላ ነገር ስላልተዋረደ ለጥ ብሎ ተገዛ።”[1]

   ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ የሰሜኑን ሰው ውርደት ነው ተመልክተው የተቆጩት፣ የደቡቡ፣ የምስራቁ፣ የምዕራቡ በምን ሁኔታ ውስጥ እንደነበር ታሪክን ወደ ኋላ ሄደን የተመለከትን እንደሆነ መሬቱ ሁሉ ተቀምቶ፣ ጭሰኛ ሆኖ አገር በቀል በሆነ ከፊል ቅኝ ግዛት ውስጥ ነው የነበረው። በዚህ ሁኔታ የተጀመረው ሁሉንም ጨፍልቆ አንድ ዓይነት ህዝብ መፍጠር ላይ የተመሰረተ የአገር ግንባታ በአጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስትም በፈረንሳይ የአሃዳዊነት ሞዴል ታግዞ የአገር ግንባታው የቀጠለ ቢሆንም በጠንካራ ከተሜነትና በኢንዱስትሪ መስፋፋት ስላልታገዘ፣ ፊውዳል ስርዓቱንና የመሬት ስሪቱ በነበረበት በመቀጠሉ በየቦታው አማርኛ ተናጋሪ የሆኑ፣ በዙሪያቸው ካሉት ህዝቦች ጋር በቋንቋም ሆነ በባህል ትስስር የሌላቸው ከተሞች ከመፍጠር የዘለለ የተፈለገው ያህል አንድ ዓይነት ቋንቋ የሚናገር አንድ ዓይነት ህዝብ መፍጠር አልተቻለም። በዚህ ምክንያት በትግራይና በአብዛኛው የአማራ ክልሎች ውስጥ ከሚገኙ ከተሞች በስተቀር ከተሜው እና በከተሞቹ ዙሪያ ያለ ህዝብ ተመሳሳይ ቋንቋ እና ባህል ያለው አይደለምኣብዛኞቹ በወታደራዊ ሰፈርነት ወይም በንግድ መተላለፊያነት ወይም የዳኝነትና የመንግስት አስተዳደር መስጪያነት የተመሰረቱ ከተሞች በመሆናቸው በብዙ የአፍሪካ ከተሞች ላይ እንደሚታየው በቅኝ ግዛት እንተፈጠሩት ከተሞች ዓይነት ባሕሪ የሚታይባቸው ናቸው፤ ይህም በዙሪያቸው ካለው ህዝብ በቋንቋ እና ባህል የሚለዩ መሆናቸው ነው ከዚህ ተፅዕኖ ውጭ የሆኑት ትግራይ ውስጥ የሚገኙት ከተሞች ናቸው፤ የከተሞቹ ነዋሪ እርስ በእርስ የሚግባባው በትግርኛ  ቋንቋ ነው፤  በከተሞቹ እና በዙሪያቸው ባሉት የገጠር መንደሮች የሚወለዱ ህፃናት አፋቸው የሚፈቱት በተመሳሳይ ሁኔታ በትግርኛ  ቋንቋ ነው። አብዣኞቹ የአማራ ክልል ከተሞችም እንደዚሁ ተመሳሳይ ባሕሪይ ነው ያላቸው። ሌላው የሚገርመው ነገር ደግሞ፣ ባለፉት 30 ዓመታት፣ ብሄር ብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ነው፣ ቋንቋቸውና ባህላቸው እያሳደጉ ነው በተባለባቸው ግዜያት እንኳ ከሰማኒያ በላይ ብሄረሰቦች ውስጥ አንዱን እንኳ የራሱን ባህልና ቋንቋ የሚያንጸባርቅ አዲስ ከተማ መፍጠር የቻለ የለም፣ ማድረግ የተቻለው ከዚህ በፊት ከላይ በተገለጸው መንገድ በተመሰረቱ ከተሞች ውስጥ የሚኖረውን ህዝብ ከፖለቲካ ማግለልና መጨቆን ብቻ ነው።

   ሌላው ጸሀፊዋ ያነሱት ነጥብ የኢትዮጵያ ታሪክ ትምህርት ጉዳይ ነው፤ በታሪክ ትምህርቱ ይዘት ላይ መስማማት በመጥፋቱ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ማስተማሩ እንደተተወ ጽፈዋል። ምክንያቱ ለእኔ ግልጽ ነው፤ አርቲስት ጌትነት እንየው በግጥሙ፦

   “የማይቻል አንድ ነገር…

   እውነት- ቤት ስትሰራ:-

   ውሸት- ላግዝ ካለች

   ጭቃ ካራገጠች

   ምስማር ካቀበለች

   ቤቱም አልተሰራ

   እውነትም አልኖረች።”[2]

   እንዳለው እውነት ታሪክ ልትጽፍ ስትነሳ፣ ውሸት እኔም ላግዝሽ ብላ ገብታ ታሪካችን ሁሉ እውነትና ውሸት የተቀናቀለበት እንዲሆን ስለተደረገ ነው። በመሰረቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የአንድን ወገን የፖለቲካ ፖሮፖጋንዳ እንጂ ትክክለኛ የሆነ የታሪክ አስተምህሮ ኖሮ አያውቅውም። ይህን በተለያዩ ምሳሌዎች ማሳየት የሚቻል ነው። ለምሳሌ ከመቅደላው የእንግሊዝና አጼ ቴዎደሮስ ጦርነት መነሳት እንችላለን። የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሃፊዎች የጦርነቱ ምክንያት አጼ ቴዎደሮስ በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩት ፈረንጆች ሰብስበው በማሰራቸውና የጦር መሳሪያ የሚሰሩ ባለሞያዎች ካልሰጣችሁን አልፈታም ብለው በመያዛቸው እንደሆነ አይነግሩንም፤ የእንግሊዝ ሰራዊት የኢትዮጵያ መሬት ውስጥ ገብቶ እስረኞችን አስፈትቶ እንዲወስድ በወቅቱ የአጼ ቴዎድሮስ ተቀናቃኞች የነበሩት ሁሉ፣ የላስታው ዋግሹም ጎበዜ፣ የትግራዩ በዝብዝ ካሳ፣ የሸዋው ንጉስ ምኒልክ፣ የወሎዎቹ ወርቂቱና መስትዋት ስምምነት አግኝቶ እንደገባ አይነግሩንም፤ ከዚህ ይልቅ “አጼ ዮሃንስ ወደ መቅደላ መርተው አመጧቸው” የሚል ውንጀላ ነው የሚያስተምሩት። በአንጻሩ የሸዋው ንጉስ ምኒልክ እንግሊዝን ለማገዝ ወደ መቅደላ ዘምተው ሰራዊታቸው ፋሲጋን ከቤተሰብ ተለይቶ መዋሉን ስላልወደደ እንደተመለሰ፣ የአጼ ቴዎደሮስን ሞት አስመልክተው የደስታ ደብዳቤ ወደ እንግሊዟ ንግስት ቪክቶሪያ እንደላኩ አይነግሩንም። በተመሳሳይ ሁኔታ ዋግሹም ጎበዜ እንግሊዟ ንግስት ቪክቶሪያ በፃፉት ደብዳቤ ላይ “እናንተ ብትመጡ ከሰው ፊት እኔ ተቀብዬ መንገዱ መርቼ እህልም ማርም በግና ፍየል ይዘህ ከሰፈራቸው ግባ ብዬ አዋጅ የነገርሁ…”[3] ማለታቸቸውን የሚጠቀስ ነው። ራሳም የተባለው በወቅቱ መቅደላ ላይ እስረኛ የነበረው እንግሊዛዊም ይህን እውነታ በመጽሐፉ ላይ አስፍሮት ይገኛል[4]። እንደዚሁም በወቅቱ በወሎ ግዛት ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበሩት ወ/ሮ ወርቂቱና ወ/ሮ መስትዋት ሁለቱም በየተራ ከእንግሊዙ የጦር መሪ ናፒየር ጋር በአካል ተገናኝተው እንደተደራደሩና ዘመቻው ስኬታማ እንዲሆን ለማድረግ ስምምነት ማድረጋቸውን ታቦር ዋሚ[5] እነ Darrell Bates[6] እና ዻውሎስ ኞኞ[7] ጠቅሰው ጽፏል።

   ወደ አድዋ ድል ስንመጣም ተመሳሳይ ነገር ነው የምናገኘው፤ የውጫሌ ውል አንቀጽ 3 የኢትዮጵያን መሬት በግልጽ ለኢጣሊያ እንዲሰጥ የፈቀደ ውል ነው፤ የኢትዮጵያ የታሪክ ትምህርት ስለዚህ አንቀጽ ለመነጋገር አይፈቅድም ከዚህ ይልቅ ስለ አንቀጽ 17 እና በእሱ ምክንያት ስለተነሳው የአድዋ ጦርነት ነው ብዙ ነገር የሚያትተው። እንደዚሁም ነጮች ለመጀመሪያ ጊዜ በጥቁሮች የተሸነፉበት ጦርነት ነው የሚለው ትርክት በራሱ አከራካሪ ነው። ሌላው ይቅርና በእኛ አገር እንኳ ከዚያ በፊት ደጎዓሊ ላይ በራስ አሉላ የሚመራው ሰራዊት የጣሊያንን ጦር ድባቅ መትቶ አሸንፈዋል፤ በሮም ላይ ቆሞ የሚገኘው የኢጣሊያ የዶጋዓሊ ሰማዕታት ሃውልት ለዚህ ህያው ምስክር ነው። የግብጽ ዓረቦች ነጮች አይደሉም ወይም ቢያሸንፉንም የነጮች ያህል ጉዳት የላቸውም ካልተባለ በስተቀር ኢትዮጵያ ከዚያ በፊት በአጼ ዮሃንስ መሪነት በጉራዕና በጉንደት ላይ የግብጽ ዐረቦች ወረራ በአስተማማኝ መልኩ አሽንፋ መመለስ ችላለች።

   በጉራዕና በጉንደት ጦርነት የግብጽ ዓረቦች አሽንፈውን ቢሆኑ ኖሮ ልክ ግብጽን ወርረው ከያዙት በኋሏ የፖለቲካ ትርጉም እንዳይኖራቸው እንዳደረጓቸው ኮፕቲክ ክርስቲያን ግብጾች ያደርጉን እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ ሱዳን ውስጥም የሆነ ነገር ነው። ሌላው ከአድዋ ጦርነት በኋላ ስለተደረጉት የፈረስ ማይ እና የአዲስ አበባ ውሎች የኢትዮጵያ የታሪክ አይነገረንም። ከዚያ በፊት በተደረገው የውጫሌ ውል ያልተሰጡ ከፊል ሰራየ፣ ኣብዛኛው የአከለጉዛይ አውራጃ መሬት፣ እስከ በለሳ ሙናና መረብ ወንዝ ድረስ ያሉትን ቦታዎች ለኢጣሊያ የተሰጡት  በእነዚህ ውሎች ነው።

   ጸሃፊዋ የአጼ ምኒልክ ሃወልት ላይ አጋጠመ ያሉት ተቃራኒ ፍላጎትም ቢሆን ከዚህ ከአጼ ምኒልክ ሌጋሲ ጋር የሚያያዝ ነው። አጼ ምኒልክን የዘመናዊት ኢትዮጵያ መስራች አባት አድርጎ የማቅረብ ፍላጎት እንዳለው ሁሉ፣ በተቃራኒው ደግሞ ወራሪ ጨፍጫሪ፣ ቅኝ ገዥ አድርገው የሚያዩዋቸው ወገኖች ደግሞ አሉ። ስለዚህ ጀዋር መሀመድ እንዳለው ወይ ጨርሶ መተው ነው ወይም ደግሞ ሁለቱንም ሀሳቦች የሚያስታርቅ መንገድ መፈለግ ነው ያለብን።

   በነገራችን ላይ በጀግኖቻችንም ላይ እኮ ብዙ መስማማት የለም። ለምሳሌ ራስ ጎበና ዳጬ በአንድ በኩል አገር አቅኚ አድርገው ሲሳሉ በሌላ በኩል ደግሞ የምኒልክ ቅጥረኛ ባንዳ አስጠቂ ተደርገው በኦሮሞ ልሂቃን በኩል ይቀርባሉ፤ የኦሮሞ ልሂቃን እንደ ጀግና የሚያይዋቸው እንደነ ጄኔራል ታደሰ ብሩ፣ ዋቆ ጉቱ ደግሞ በሌላው ወገን በጥሩ የሚታዩ አይደሉም። ደርግ የራሱን ጭቁን ጀግኖች ለማስተዋወቅ ሞክሮ ነበር፣ ከንጉሶች አጼ ትዎድሮስ፣ ከትግራይ ራስ አሉላ፣ ከጎጃም በላይ ዘለቀ፣ ከኦሮሞ አብዲሳ አጋ፣ ከሶማሌ ደጃዝማች ዑመር ስመትር ወዘተ የታሪክ ጀግኖች አድርጎ በመጽሐፍም በድራማም በግጥምም በትርክትም ለማስረጽ ሙከራ አደርገዋል። ነገር ግን ጎጃም ላይ የአድዋው ድል አርበኛ ንጉስ ተክለሃይማኖትን በደጃዥማች በላይ ዘለቀ ማስረሳት ከማስቻሉ ውጪ ብዙ የተሳካ አይደለም።

   በአጠቃላይ ካየነው የአገራችን ነገር ታዋቂው ገጣሚ በእውቀቱ ስዩም “ኗሪ አልባ ጎጆዎች” በተሰኘው ግጥሙ እንደገለጸው ዓይነት ችግር ነው የገጠመን፦

   “አያቶች

   በባዶ መስክ ተመራምረው

   ጥበባቸውን

   ዕድሜያቸውን

   ገብረው

   የጎጆን ንድፍ ሲያበጁ

   አረጁ

   ዘመናቸውን ፈጁ።

   አባቶች

   መላ ዘመናቸውን

   ጎጆውን በመቀለስ አለፉ።

   ልጆች

   ጎጆውን መውረስ ሳይከጅሉ

   እንዲህ አሉ

   ‘ያባቶቻችን ቤት

   ያያቶቻችን ጎጆ

   ይሁን ባዶ ኦና

   በኛ ቁመት

   በኛ መጠን

   አልተቀለሰምና።”[8]

   ወደ መፍትሄ ሀሳብ ስንመጣ ምን መሆን አለበት? የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። አንደኛ የተሳሳተው የአገር ግንባታ ማረም ነው። እንዲህ ዓይነቱ መሰረታዊ የሆነ ችግር የሚፈታው ደግሞ ባለፉት 150 ዓመታት ተጨቁነናል የሚሉ ህዝቦች በፖለቲካም፣ በኢኮኖሚም፣ በባህልም በቋንቋም እኩል የማደግና የመበልጸግ እድል እንዲያገኙ ማድረግ፣ እንደዚሁም ራሳችውን በራሳቸው ማስተዳደር ለሚፈልጉ ህዝቦች ሰፊ የሆነ የራስ አስተዳደር ነጻነት የሚሰጥ ህብረ ብሄራዊ የሆነ የሃገረ መንግስት ግንባታ (State Building) መከተል ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ የብዙ ሃገር አካል ብሔሮች አገር በመሆኗ ከብሄረ መንግስት ግንባታ (Nation Building) ይልቅ በሃገረ መንግስት ግንባታ (State Building) ላይ ነው ትኩረት ማድረግ ያለባት። በዚህ መንገድ በህዝቦች ትብብርና መልካ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ የሃገረ መንግስት ግንባታ (State Building) ማካሄድ ትችላለች። ሁለተኛ የኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነት የባህልና ቋንቋ ብዙሕነት፣ ሰፊ የኢኮኖሚ ትስስር እና የህዝብ መስተጋብር የሚገለጽበት የጋራ ሃብት (Common Wealth) እንዲሆን የሚያደርግ የጋራ የሆነ የፖለቲካ አካሄድና የታሪክ አረዳድ ማጎልበት ይኖርብናል። ቋንቋ በተመለከተ በመንግስት የአገልግሎት ተቋማት፣ በሚዲያዎች በትምህርት ቤቶች የቋንቋ ብዙሕነት እንዲኖር የሚያደርግ ፖሊሲ መከተል ያስፈልጋል። ትያቲር ቤቶቻችን የፊልም ማሳያ ሲኒማዎቻችን በተለያየ የአገር ቋንቋዎች የሚቀርቡ ሰራዎች የሚታዩባቸው መድረኮች እንዲሆኑ የሚያበረታታ የመንግስት አቅጣጫ እንዲኖር ማድረግ።   የታሪክ ትምህርትና ትርክ በተመለከም እንደዚሁ ታሪካችን የሚያኮራ ነገር ካለው በጋራ እንድንኮራበት፣ የሚሳፍር ነገር ካለውም በጋራ ትምህርት ወስደን እንዳይደገም የምናደርግበት ሁኔታ የአገራችን የታሪክ ትምህርት መሰጠት መቻል አለበት። በዚህ ጉዳይ ያለ ምህረት መከራከርና በሚያስማሙን እየተስማመን፣ በማያስማሙን ነገሮች ደግሞ በመከባበር ላይ የተመሰረተ የተለየ ሀሳብና አቋም በመቀበል ነገሮችን ማርገብ፣ በሀሳብ ብዙሕነት ላይ የተመሰረተ የጋራ አገር እና ታሪክ እንዲኖረን ማድረግ ይቻላል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ።

   *አስራት አብርሃም (የከሃገር በስተጀርባ፣ የፍኖተ ቃኤል፣ የህገመንግስቱ ፈረሰኞች ወዘተ መጽሐፍት ጸሐፊ)

   [1] ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ስራዎች (2007) ገጽ 18

   [2] ጌትነት እንየው (2006 ዓ.ም) “እውቀትን ፍለጋ” ከሚለው መጽሐፉ የተወሰደ።

   [3] ተክለጻዲቅ መኩሪያ፣ አፄ ዮሃንስና የኢትዮጵያ አንድነት ገጽ 35

   [4] Rassam Hurmuzd, Narrative of the British Missin to Theodore, king of Abyssinia, vol. II P. 252

   [5] ታቦር ዋሚ፣ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፣ ገጽ 378-381

   [6] Darrell Bates, the Abyssinian Difficulty፡ the emperor Theodorus and the Magdalla Campaign 1867-1868, Oxford University Press, 1979.

   [7] ጳውሎስ ኞኞ፣ አጼ ቴዎድሮስ፣ 1985 ዓ.ም አዲስ አበባ

   [8] በእውቀቱ ስዩም ኗሪ አልባ ጎጆዎች ከተሰኘው የግጥም መድብል የተወሰደ።

Viewing 0 reply threads
Reply To: የትውስታ ኣባዜ ወይስ የተዛባ የአገር ግንባታ?
Your information: