ፖለቲካል ኢኮኖሚ በኢትዮጵያ፦ ለውጥ እና ቀጣይነት

Home Forums የወጣቶች መድረክ ፖለቲካል ኢኮኖሚ በኢትዮጵያ፦ ለውጥ እና ቀጣይነት

 • This topic is empty.
Viewing 0 reply threads
 • Author
  Posts
  • #4238 Reply

   ናታን በለጠ

   “ኢኮኖሚስቶች የሚያውቁት የኢኮኖሚ ሞዴሎችን ብቻ አይደለም፡፡ በተጨማሪነት የጋራ የሆኑ ፍላጎቶችን፣ የፖለቲካ አመለካከቶችን፣ ግጭቶችን፣ ስሜቶችን ይረዳሉ፡፡ ግዜያዊ ለውጦችን በህግ ማምጣት ይቻል ይሆናል፣ ቋሚ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ግን ትብብር እና ደጋፊዎችን ማብዛት ይገባል” (ቡስካጋሊያ፣ 2004፣ 43) ይህ ሐሳብ የሚያሳየው ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ፣ አንዱ ከሌላኛው የማይነጠል፣ አንዱን ሳያውቁ ሌላኛውን መረዳት አዳጋች መሆኑን ነው፡፡ በሌላ ቋንቋ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው፡፡ የእዚህ ጥምር ግንዛቤ ፖለቲካል ኢኮኖሚን አስገኝቷል፡፡ ፖለቲካል ኢኮኖሚ በቀላል አገላለጽ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ መካከል የሚገኝ ነጥብ ነው፡፡ በአጭሩ አንዱ በሌላው ላይ ግዙፍ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡

   ይህ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ግንኙነት በአፍሪካ በባከነ መንገድ ሲፈስ ይስተዋላል፡፡ በአፍሪካ ጥያቄ በሚያጭር መልኩ የፖለቲካ ስልጣን ለግለሰቡ እና በግለሰቡ ዙሪያ ለተሰበሰቡት ቡድኖች የሀብት ማፍሪያ መንገድ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ባህሪ በዘመድ አዝማድ የመጠቃቀም እና በኔትወርክ ለተቆራኘ የሐብት ስርጭት የተጋለጠ ነው (ፍራንሲስኮ፣ 2010)፣ ክስተቱ በኢህአዴግ ስርዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የተከሰተ አይደለም፡፡ ስርዓቱ የልማታዊ መንግስት ጽንሰ ሐሳብን ለመተግበር በሞከረበት ወቅት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ግለሰቦች ስርዓቱ የሚፈልጋቸው አካላት ብቻ ተጠቃሚ ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋታቸውን አሰምተዋል፡፡

   እ.ኤ.አ በ2018 የሪፎርም እንቅስቃሴው ሲጀመር፣ የነጻ ገበያ ሐሳቦች በስፋት ተደምጠው ነበር፡፡ በተለይም በዜጎች ዘንድ የለውጥ ተስፋ ስለነበር ጉዳዩን በመልካም ተቀብለውታል፡፡ ይሁንና ከነጻ ገበያው ጋር ተያይዞ በዜጎች ዘንድ የተስተዋሉ ስስ ፍርሐቶች ነበሩ፡፡ በኔ እምነት በተሳሳቱ ፖሊሲዎች እና በአንዳንድ የኢህአዴግ ባህሪዎች እና ልምዶች ታጅቦ አዲሱ ስርዓት ኢትዮጵያን ድህረ ልማታዊ መንግስት ግዜ ላይ ጥሏታል፡፡ በሰሜን የተቀሰቀሰው ጦርነት፣ የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት፣ የኮሮና ወረርሽኝ እና የተዘባራረቀውን የገበያ ስርዓት በነጻ ገበያ ለመተካት በተካሄደው ሙከራ ውስጥ፣ በውስጣዊ እና ውጪያዊ አለመረጋጋት ምክንያት የኢትዮጵያ ዕድገት ተገቷል፡፡ በእዚህ ሂደት ተነሳስተን ወደ ልማታዊ መንግስት እሳቤ መመለስ እና ብልጽግና ከመጣ ወዲህ የታዩ ችግሮችን መቅረፍ አለብን፡፡

   ኢህአዴግ እና ልማታዊ መንግስት

   ልማታዊ መንግስት ማለት “መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ ገብቶ፣ የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላት፣ ኢኮኖሚውን የሚመራበት ስልት ነው” (ካልደንታይ፣ 2008፣ 28) የኢህአዴግ ስርዓት በጥብቅ ይከተለው የነበረው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሓሳብ ነው፣ በተጨማሪም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የተቆጣጠረው በእዚሁ ስልት ነበር (ፋንቲኒ፣ 2013) በልማታዊ መንግስት ርዕዮት ኢትዮጵያ ፈጣን እና አስገራሚ እድገት አስመዝግባለች፣ ለአስር ዓመታት አከባቢ አመታዊ ዕድገቷ 10 ፐርሰንት ነበር፡፡ ድህነት ከ44% ወደ 30% ዝቅ ብሏል፡፡ በእነዚህ ዓመታት በከፍተኛ መጠን የስራ አጥ ቁጥር እንዲቀንስ ተደርጎ 3.5% ወደ 2.3% ዝቅ ማለት ችሏል፡፡ ይህ ልማት የመጣው በዲሞክራሲ ዋጋ ነው፡፡ መንግስትም በጉዳዩ ላይ በይፋ ከዲሞክራሲ በፊት ሆድ ይቀድማል የሚል መርህ ማራመድ ጀምሮ ነበር፡፡

   የልማታዊ መንግስትን ፖሊሲ በቅጡ ማስፈጸም የሚችሉ ብቁ ሰዎች አለመኖር፣ በቢሊየን ዶላር የሚገመት የህዝብ ሐብት እንዲባክን ምክንያት ሆኗል፡፡ ለእዚህ ማሳያ የሚሆንን ሜቴክ የአባይ ግድብ ፕሮጀክትን በሰባት ዓመት ያጠናቀቃል ተብሎ ቢጠበቅም በቀላሉ ሊሳካ አልቻለም፡፡ ግድቡም የተሰራው ዜጎች ከኪሳቸው ባወጡት ጥሬ ሐብታቸው ነው፣ ነገር ግን በሰባት ዓመታት ውስጥ ግድቡ ያስመዘገበው ውጤት ከሚጠበቅበት በታች ነበር፡፡ መንግስት ተጨማሪ ወጪ አውጥቶ ግድቡን ቢቀጥል፣ በዜጎች በኩል ከፍተኛ ቅሬታ ቀርቦበታል፡፡ ይህ ቅሬታ የተደመጠው ከተለያዩ የብሔር የፖለቲካ ኃይሎች ወገን ነበር፡፡ በተለይም በህዝቡ ዘንድ የነበረው ቅሬታ የትግራይ ተወላጅ በሆኑ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ጎልቶ ታይቷል፡፡ ይህ እና ከስራ አጥነት ጋር የተያያዙ ችግሮች በሐገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች ከ2015 እስከ 2018 የዘለቀ ተቃውሞ ቀሰቀሰ።

   ከልማታዊ መንግስት መራቅ

   ይህ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጠ/ሚ አቢይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጋቢት 2018 እንዲመጡ ረዳቸው፡፡ አጋጣሚው በብዙዎች ዘንድ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ነጻነት እንደሚሰፍን ተስፋ እንዲያደርጉ መንገድ ከፈተላቸው፡፡ ለውጡ ጋዜጠኞችን፣ ፖለቲከኞችን እንዲሁም ቴሌኮምን ለግል በማዞር ሽግግር ማድረጉን አሳየ፡፡ በመንግስት በኩል እንደ ግዙፍ ስኬት የተቆጠረ ሂደት ነበር፡፡ በተጨማሪም እንደ ሜቴክ ባሉ ግዙፍ ተቋማት መሪዎች ክንፈ ዳኛውን ጨምሮ  በኢትዮጵያ ለውጥ እየመጣ እንዳለ ተስፋ ሰጥተው ነበር፡፡

   የአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ በውስጡ ከያዛቸው ትልሞች ውስጥ በዋናነት ገበያ ላይ ያተኮረ፣ የግል ዘርፉን የሚያነቃቃ ሐሳቦችን አጽንኦት ሰጥቷል፡፡ በእዚህ ውስጥ የስኳር እና የቴሌኮም ዘርፎችን ነጻ ለማድረግ እና ወደ ግል ለማዞር ተሞክሯል፡፡ እ.ኤ.አ ከ2018 ጀምሮ በኢትዮጵያ የነበረው የኢኮኖሚ አየር ይህንን የመሰለ ነው፡፡ መንግስት የስራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ እንዲረዳው እና ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ ለማስቻል የግሉን ዘርፍ ሲያበረታታ ቆይቷል፡፡ በ2020/21 በጀት ዓመት ሀገሪቱ 3.9 ቢሊየን ዶላር ገቢ አግኝታለች፣ ከቀደመው ዓመት ትርፍ ጋር ሲነጻጻር የአንድ ቢሊየን ብልጫ አለው፡፡

   በእነዚህ ሁሉ ለውጦች ውስጥ መንግስት በኮቪድ ወረርሽኝ እና በትግራይ በተቀሰቀሰው ጦርነት ተፈትኗል፡፡ በተለይም ወረርሽኙ በከተሞች አከባቢ በተበጣጠሰ መንገድ ግን ደሞ በፍጥነት የሚያድገውን ኢኮኖሚ ክፉኛ አዳክሞታል፡፡ በወርልድ ባንክ ይፋ የሆነው ጥናት እንደሚያመለክተው በአዲስ አበባ 42% የሚሆኑ የተመዘገቡ ሱቆች ተዘግተዋል፡፡ በሐገር ደረጃ 8% የነበረው ስራ ፈትነትን ሊቀጥሩ የሚችሉ 2% ድርጅቶች ብቻ ነበሩ፡፡ በትክክል የእዚህ ችግር ቀጥተኛ ገፈት ቀማሽ የሚሆኑት ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ የሚመሩ ዜጎች ናቸው፡፡ ነገሮችን የበለጠ የከፉ ያደረጋቸው በጥቅምት መጨረሻ አከባቢ መንግስት ከህወሓት ጋር በሰሜን ኢትዮጵያ የገባበት ጦርነት ነው፡፡ ጦርነቱ በተጀመረበት ወቅት በጥቂት ሳምንታት እንደሚጠናቀቅ ታሳቢ ቢደረግም፣ አሁን ጦርነቱ አንድ ዓመት ፈጅቶ፣ ከመጠናቀቅ ያለፈ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ጦርነቱ እጅግ ሰፊ መሰረተ ልማቶችን አውድሞ፣ ወደ ሌሎች ክልሎችም ተስፋፍቷል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ኢኮኖሚው የተንኮታኮተ ሲሆን፣ በዕቃዎች ላይ የሚኖር ዋጋ እንዲያጋሽብም አድርጓል፡፡

   ለውጥ እና ቀጣይነት

   ድህረ 2018 የኢትዮጵያ ፖለቲካ በ27 ዓመታት ውስጥ ያልታሰቡ ክስተቶች የተስተዋሉበት ነው፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ መከፈት እና የኢኮኖሚው ነጻ መሆን፣ በኢትዮጵያውያን አዕምሮ ውስጥ የማይታሰብ ሁነት ነበር፡፡ በመጀመሪያዎቹ የለውጥ ዓመታት በዜጎች ልብ ውስጥ ከፍተኛ ተስፋ ይታይ ነበር፣ እንዲሁም የልማታዊ መንግስት ርዕዮት ከጠረጴዛው ገሸሽ ሲደረግ ዜጎች ጉዳዩን ያዩት በአውንታ ነበር፡፡ ኢኮኖሚው ነጻ መሆኑ የስራ ዕድል፣ ግልጽነት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ ይፈጥራል የሚል እምነት እንዲኖር አደረገ፡፡ ተጨማሪ ተስፋ ያበበው ኢህአዴግ ከስሞ የብልጽግና ፓርቲ ሲመሰረት ነው፡፡ መንግስት የ’ሸገርን ማስዋብ’ ፕሮጀክት ይፋ ሲያደርግ የስራ ዕድል ለመፍጠር፣ የአከባቢ ጥበቃን መነሻ አድርጎ፣ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን ለማጎልበት ነበር፡፡ በገጠር አከባቢዎች መንግስት ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመሆን የሴፍትኔት ፕሮግራሞችን ለማጠናከር ሞክሯል፡፡

   በእነዚህ ሁሉ ሂደት ኢህአዴግ በሐገሪቱ ላይ ያለው ቁጥጥር በመዳከም ላይ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ጉዳዩ ከሚባለው በተቃራኒ መሆኑ ይስተዋላል፡፡ አዲሱ አስተዳደር ህወሓት የሌለችበት ኢህአዴግን ቅርጽ የያዘ ነው፡፡ ከኢህአዴግ ስርዓት ጥቅም ተጋሪ የነበሩ ግለሰቦች አሁንም በአዲሱ ስርዓት ውስጥ ያላቸው ተጠቃሚነት አልቀነሰም፡፡ ስራ አጥነቱ አሁንም ችግርነቱ አልተቀረፈም፣ ብዛት ካላቸው ዩንቨርስቲዎች የሚመረቁ ተማሪዎችን መቅጠር የሚችል ኢኮኖሚ በገበያው ላይ አይስተዋልም፡፡ በከተሞች አከባቢ የሚገነቡት መናፈሻዎች የዜጎችን አኗኗር የሚቀይር አይደለም፣ ኢኮኖሚው ላይ ግን የራሱን ጠባሳ እያሳደረ ይገኛል፡፡ ይህ ጉዳይ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ በነበረበትም ወቅት ይነሳ የነበረ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ቀድሞ የነበሩ ችግሮች በድህረ 2018 ኢትዮጵያም መቀጠሉን ነው፡፡

   የዜጎች መደናገጥ

   የ2018 ሽግግር ዓመታት ያለፉት መስሏል፣ የዕድገት መንገዱም በተቃራኒ አቅጣጫ እየሄደ ነው፡፡ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ከለወጡ በፊት ከነበረችበት ውስጣዊ እና ውጪያዊ ችግር የከፋ ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡፡ በሀገር ውስጥ በትግራይ የተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ግጭት እና የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ተጨማሪ ችግሮችን ፈጥሯል፡፡ ከእዚህ ባሻገር የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሐገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይ ጥላውን አጥልቷል፡፡ እነዚህ ችግሮች ኑሮ በማስወደድ ዜጎች በአስከፊ ስጋት ውስጥ እንዲገቡ አስገድዷቸዋል፣ ብዙዎች በስራ እጦት ሲንገላቱ ቀሪዎቹ፣ ስራ አጥ እንዲሆኑ ተገደዋል፡፡ በሐገሪቱ ያለው የዋጋ ንረት መጠን 34.7% የደረሰ ሲሆን በማርች ወር የተመዘገበው 43.4% በተከታታይ በነበሩ ወራቶች የተመዘገበው የዋጋ ንረት መጠን 33% እና 44% አከባቢ ነው፡፡ በእዚህ የዋጋ ንረት ውስጥ መንግስት የማስተካከያ እርምጃዎችን እስከ አሁንም በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ የመንግስት አማራጮች ዜጎች አመጋገባቸውን አስተካክለው አትክልት እንዲመገቡ የሚመክር ነው፡፡ በዜጎች በኩል ግን ይሄን መሰል መንግስታዊ አካሄድ የከፋ ብሶት ቀስቅሷል፡፡ በተለይም በምግብ ዘይት ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ከፍተኛ ቅሬታ እንዲኖር አድርጓል፡፡

   ቀድሞ መንግስትን ሲያደንቁ የነበሩ ዜጎች አሁን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች መንግስትን ሲተቹ ይደመጣል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለአትክልት ያወሩትን ወሬ በየዕለቱ በሚዲያው ላይ የጨዋታ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በተለይም በቲክ ቶክ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክር፣ በተለያየ መንገድ ቪዲዮ እየተሰራበት መዘባበቻ ሆነዋል፡፡ ሰሞኑን በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተከበሩት የኢድ እና የፋሲካ በዓላት ላይ ዜጎች ሙዝ እያረዱ በመንግስት ሲሳለቁ ታይተዋል፡፡

   በርግጥ መንግስት በጉዳዩ ላይ የወሰደቸው እርምጃዎች ነበሩ፡፡ ገበያውያን ለማረጋጋት ምርቶችን ከውጭ ወደ ሐገር በማስገባት ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ለአብነት የምግብ ዘይት ችግሩን ለመፍታት እንዲረዳው መንግስት ከውጭ 150 ሚሊየን ሌትር ዘይት ወደ ሐገር ውስጥ አስገብቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት የስንዴ ዋጋ እንዲጋሽብ ቢያደርግም፣ መንግስት በሐገር ውስጥ እጥረቱን ለመሸፈን ሙከራ እያደረገ እንዳለ ሲያሣይ ቆይቷል፡፡ ቢሆንም ግን እያደገ ያለውን የኢትዮጵያውያንን የምርት ፍላጎት ማሟላት መቻሉ አጠያያቂ ነው፡፡

   የመፍትሔ አማራጮች

   እ.ኤ.አ ከ2018 በፊት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጥሩ የሚባል እድገት እያስመዘገበ ነበር፣ ይሁንና ከሽግግሩ አንስቶ አጠቃላይ ዓመታዊ ዕድገቷ በ2020 የተመዘገበው ከ6.1% ከፍ ያላለ ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ በአስከፊ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች፡፡ በተጨማሪም በየወሩ የሚስተዋለው የዋጋ ንረት ዜጎችን እያስጨነቀ፣ መንግስት በበኩሉ ችግሩን ለመቅረፍ የሚንደፋደፍባት ሐገር ሆናለች፡፡ ይህ ለውጡ እና ከለውጡ የቀጠለ ሒደት ነው፡፡

   ከለውጡ ጀምሮ የግሉ ሴክተር ኢኮኖሚውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል አቅም ያለው በመሆኑ ኢኮኖሚውን ሊበራላይዜሽን ማድረግ አስፈላጊ ነበር። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ግን ይህ በቂ አይደለም። ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ. በ 2012 በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ በፓናል ውይይት ላይ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በግሉ ሴክተር ሊሞላ የማይችል የገበያ ጉድለት የተሞላ ነው። እንደ ኤሌክትሪክ እና ትራንስፖርት ያሉ የሀገርን ኢኮኖሚ ለመለወጥ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ቢሆኑም እጅግ በጣም ደካማ የሆነው የግሉ ሴክተር ክፍተቱን መሙላት አይፈልግም። ለምሳሌ GERD ሲጠናቀቅ ሀገሪቱ ኤሌክትሪክን ወደ ውጭ ለመላክ ባቀደችው መሰረት የውጭ ምንዛሪ የማግኝት ዕድል ይፈጥራል። በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ኃይል ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እና ለአገር ውስጥ አገልግሎት የሚውል በመሆኑ በእዚህና በሌሎች የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች መንግሥት ኢኮኖሚውን መለወጥ ይችላል። ነገር ግን መንግሥት ከእነዚህ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ወደ ኋላ ቢያፈገፍግ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መለወጥ እጅግ አዳጋች ነው። በመሆኑም መንግስት ኢኮኖሚውን ለመለወጥ ማዕከላዊ ሚና መጫወት አለበት።

   ከእዚህ ባሻገር ብልጽግና የቀድሞውን ኢህአዴግ መዋቅር የያዘ እንደ አዲስ የተጠመቀ ፓርቲ ነው፡፡ በድርጅታዊ መርሁም ከቀደመው የተለየ አይደለም፡፡ የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊዎችም ሆኑ መሪዎች የቀደመው ኢህአዴግ ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወቱ የነበሩ ግለሰቦች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ልማት እና ዲሞክራሲ የሚያመጡ ሳይሆኑ ህዝቡ ዳግም ወደ አመጽ እንዲገባ እንዲሁም መንግስታዊ ለውጥ እንዲኖር እድል የሚያመቻቹ ናቸው፡፡  በመሆኑም መንግስት የህዝቡንና የኢኮኖሚውን መሰረታዊ ፍላጎቶች የሚዳስሱ ሰፋፊ የልማት አጀንዳዎችን በመቅረጽ የህዝቡን ሰፊ ጥቅም በማረጋገጥ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። እናም ሰፊውን ችግር ለመቅረፍ መንግስት የበጎ አድራጎት ፕሮጀክቶች ላይ እንደ ንፅህና እና መኖሪያ ቤት ለታችኛው የህብረተሰብ ክፍሎች ኢንቨስት ማድረግ ላይ ትኩረት መስጠት አለበት፡፡ በተጨማሪም እንደ መጓጓዣ ባሉ መሰረታዊ ፍላጎቶች ላይ ማተኮር ይኖርበታል፡፡ መንገዶችን መገንባት፣ የህዝብ ማመላለሻ ማጠናከር፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ግንባታ መሰረተ ልማቶች ላይ የስራ እድል የሚፈጥሩ እና የስራ አጥነትን ችግር በተወሰነ ደረጃ ሊፈቱ የሚችሉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኢንቨስትመንትን ማበረታታት ይኖርበታል።

Viewing 0 reply threads
Reply To: ፖለቲካል ኢኮኖሚ በኢትዮጵያ፦ ለውጥ እና ቀጣይነት
Your information: