ኢትዮጵያ:- ባለፈ ታሪክ የምትዋልል አገር

Home Forums የወጣቶች መድረክ ኢትዮጵያ:- ባለፈ ታሪክ የምትዋልል አገር

 • This topic is empty.
Viewing 0 reply threads
 • Author
  Posts
  • #3322 Reply

   በጸባዖት መላኩ

   ያለፈው ግዜ፣ አሁን ያለንበት እና የወደፊቱ የሶስትዮሽ ህብረት በልዪ ልዩ መንገዶች የእለት ተእለት የህይወት ተሞክሯችንን ቅርጽ ያስይዛል። ያለፈ ታሪካችን አስተሳሰባችንን በተለያየ መንገድ ለማምለጥ በማይቻል መልኩ ጫና ስለሚያሳድርብን ትናንትናችንን ጨርሶ ልናስወግደው አይቻለንም። ግለሰቦች እና ቡድኖች እራሳቸውን የሚረዱት፣ የህብረተ ፖለቲካቸውን አመክንዮ የሚያስረዱት እና የማህበራዊ ባህላቸውን ድር የሚገምዱት ተረቶችን፣ ትርክቶችን፣ እና የጥንት አፈ-ታሪኮችን በመጠቀም ነው። ይሁን እንጂ በድህረ-አምባገነናዊ ስርአት ውስጥ፣ የማህበረሰቦች ታሪካዊ ጭቆና አሁን ያሉ ማህበረሰቦች ሸክም እንዲሆን ሲደረግ አንዲሁም ሁሉም የትናንት በደሎች በማስተባበያ ትርክቶች እና በደምሳሳው ሲካዱ ዛሬ በትናንት ፖለቲካ ተውጦ መልካሙን የወደፊት እርምጃ ውጤት አልባ ያደርገዋል። በመሆኑም ይህን አይነት የታሪክ አረዳድ መፍትሔ አልባ ከመሆኑም በላይ በእንዲህ ከቀጠለ ማብቂያ ወደ ሌለው አዝቅት ውስጥ ሊከተን ይችላል።

   በታሪክ አረዳድ ላይ የሚደረጉ ንትርኮች በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መድረክ ላይ የሰርክ ኩነቶች እየሆኑ መጥተዋል። ያለፈ ታሪክ ትርጓሜ አሰጣጥ እጅጉን እየተራራቀ እና ጽንፍ እየያዘ መምጣቱ የመነጨው ከተለያዩ አከራካሪ የታሪክ ትርክቶች ሲሆን የሀገሪቱ ብሔራዊ ስነ-ልቦና ውስጥ ስር እየሰደደ መጥቷል። ታሪክ እና ትውስታ እጅጉን እየተራራቁ ከመምጣታቸው ባለፈ በልሂቃን እና በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ሚና እንዲኖራቸው ተደርጓል። እየተራራቀ የመጣውን ብሄራዊ ልዩነቶች ለማጥበብ ሲባል የኢትዮጵያ ታሪክን በወል ትምህርትነት (Common course)  ለመጀመሪያ አመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለመስጠት ያልተቻለ ሲሆን፤ ይህም ችግሩ ምን ያህል ስር የሰደደ መሆኑን ማሳያ ነው። ፖለቲካ የታሪክ አለም ውስጥ ጣልቃ እየገባ በመምጣቱ የታሪክ ተመራማሪዎች ራሳቸው የማስተማርያ አጀንዳዎች ምን መሆን እንዳለባቸው እንኳ መግባባት ላይ ሊደርሱ አልቻሉም። ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት በርካታ የትምህርት ዓይነቶች በመጀመሪያ አመት የዩኒቨርሲቲ ፕሮግራም ውስጥ የተካተቱ ቢሆኑም የኢትዮጵያ ታሪክ ግን እየተሰጠ አይደለም፤ ይህም በመሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ፍኖተ-ካርታው የተሟላ ሳይሆን ቀርቷል።

   በ1960ዎቹ የተጀመረው የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴን ተከትሎ በጥንታዊነት ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምስል በተለያዩ ንዑስ ምስሎች፣ ማንነቶች እና ታሪካዊ ሐተታዎች ተሞግቷል። የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ ገጽታ በኤርትራውያን፣ ሶማሌዎች፣ ኦሮሞዎች እና አማራዎች ዘንድ በጽኑ ልዩነቶች ውስጥ የገባ ሲሆን፤ ዳግም አንድ የማድረግ ትርክት በአንድ ወገን እንዲሁም የሃይል አገዛዝ ትርክት በሌላ በመሆን ስለአለፉት አገዛዞች የሚቃረኑ መገለጫዎች ሆነዋል። ያለፈ ታሪክ ንግርቶች መሃል ትልቅ ልዩነት ያለ ሲሆን፤ አንደኛው ወገን የታሪክ ቀጣይነት፣ አንድነት፣ እና ባህላዊ ማንነትን ሲያውጠነጥን፣ በተቃራኒው ወገን ደግሞ ወረራ፣ ግዞት እና ልዩነት ላይ ማተኮር ይታይበታል።

   በተመሳሳይ በ1990ዎቹ ጎልቶ የወጣው የጎሳ ብሔርተኝነት ተከትሎ በታሪክ አረዳድ እና ትንታኔ ላይ የሚነሱ ንትርኮች በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሀተታ ውስጥ የበላይነት አግኝተዋል። አዲስ የታሪክ ገለጻዎች የጎሳዎችን ማሀበራዊ ትውስታዎች የተንተራሱ ሲሆን፣ የጋራ ትውስታዎቹ ከምንግዜውም በላይ እንደ አዲስ እንዲዋቀሩም አድርገዋል። ከዚህ በተጨማሪም በ2010 ዓ.ም የተከፈተው ፖለቲካዊ ምሕዳር ሌላ ታሪክን መሰረት ያደረጉ ክርክሮች እና ሐተታዎች ማእበል እንዲነሳ አድርጓል።

   የኢትዮጵያውያንን የታሪክ ትውስታ በተመለከተ ፖለቲከኛ ጀዋር ሞሃመድ በአንድ ወቅት የተናገረው፣ ሐገሪቱ ለገባችበት አጣብቂኝ የተሻለ ማሳያ ይሆናል። ይህን በተመለከተ ጀዋር ቃለ-መጠይቅ ከማድረጉ በፊት የአኖሌ ሀውልትን የጎበኘ ሲሆን፤ በተመሳሳይ እለት ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ በዳግማዊ ምንሊክ ቤተ መንግስት ውስጥ የሚገኝው የአንድነት ፓርክን የምርቃት ስነ-ስርአት አካሄደው ነበር ። ጀዋር በቃለ መጠይቁ ላይ ስለ ጉብኝቱ ሲያስረዳ፣ ድረጊቱ በ ‹‹ፖለቲካ ታሪካዊ ትውስታ›› ላይ የተመሰረተ ተግባር መሆኑን ገልጾ፤ ማንኛውም ሰው ዳግማዊ ምኒልክን፣ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴን አልያም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስን ለማወደስ ቢሞክር፣ አኔ ደግሞ ‹‹ሰይጣናዊ ተግባራቸውን›› አጋልጣለሁ ብሏል ። ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ያለፈ ታሪክ ትንተና ሁለት አማራጮች ብቻ እንዳሉት የተናገረ ሲሆን፤ እነዚህም፡ የታሪክ ምእራፉን መዝጋት አልያም ሁሉም የታሪክ ትንታኔዎች በይፋ እንዲነገሩ መፍቀድ ብቻ ነው በማለት ለታረቀ የታሪክ እውነታ ምንም አማራጭ ሳይተው ቀርቷል። በመቀጠልም ‹‹የጭቁኖች፣ የደሃዎች፣ እና የተጠቂዎች ታሪክ መነገር አለበት›› ሲል አስረግጧል።

   ሌሎች ማሳያዎች እንዳሉ ሆነው፣ እስካሁን እንደቀጠለ ያለው አከራካሪው የዳግማዊ ምኒሊክ ፈረሰኛ ሃውልት ጉዳይ በሀገሪቷ ውስጥ ያለውን ያለፈ ታሪክን የተመለከተ ማህበራዊ ክፍፍል ሌላኛው ሁነኛ ማሳያ ይሆነናል። በ 1984 ዓ.ም የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ብዛት ያላቸው ሰልፈኞችን በመጥራት ዳግማዊ ምኒሊክ አደባባይ ዙሪያ ሰላማዊ ሰልፍ አድርጎ ነበር፤ ሰልፈኞቹም የምንሊክ ሃውልትን በጥቁር መጋረጃ በመሸፈን ሃውልቱ በፍጥነት እንዲወገድ ጥያቄ አቀረቡ። ከጥቂት ቀናት በኋላ ብዛት ያለው ህዝብ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ ጥቁሩ መጋረጃ በማውረድ ይልቁን ሃውልቱን ማሳደሻ ገቢ አሰባስበዋል። አሁንም ድረስ የህዝቦች አለመግባባት የቀጠለ ሲሆን፤ በ2011 ዓ.ም ሀውልቱ እንዲፈርስ በሚፈልጉ የኦሮሞ ማህበረሰብ አባላት እና ሃውልቱ እንዲጠበቅ በሚፈልጉ ሰዎች መሃል በተነሳ ግጭት ህልፈተ ህይወት እንደተከሰተ ተዘግቧል።

   እንዲህ ያሉት በታሪክ ምክንያት የሚነሱ ነውጠኛ እና ለሞት የሚዳርጉ ንትርኮች ዋነኛ መንስኤ የሃገሪቱ ብሔረተኛ ልሂቃን የሚጫወቱት አውዳሚ ሚና መሆኑ ይታመናል። የተለያየ ብሔርተኝነትን የሚያቀነቅኑ ፖለቲከኞች እና ማህበረሰብ አንቂዎች ትኩረታቸውን በብሔራዊ ሐፍረት እና ብሄራዊ ኩራት ጫፍ ዋልታዎች ላይ ብቻ በማድረግ፤ የታሪክን ምስል በመፍጠር፣ በማፍረስ እና ዳግም በማዋቀር፤ እንዲሁም ሆን ብለው ታሪክን በመዘንጋት እና በማስታወስ ለጊዜያዊ ጥቅማቸው ያውሉታል። እነዚህ ታሪክን የተመለከቱ አለመግባባቶች የሚመነጩት ከራሱ ከታሪክ ሳይሆን የፖለቲካ ልሂቃን ብሄራዊ ማንነትን ዳግመኛ ለመፍጠር በማለም ታሪክን እንዳሻቸው በመጠምዘዝ እና በማዛባት ስለሚጠቀሙበት ነው። በመሆኑም፡ ፖለቲከኞች እና የህዝብ እሳቤን የሚመሩ ሰዎች ቀዳሚ የታሪክ ተንታኞች ሆነዋል።

   በዚህም መልኩ፣ ያለፈ ታሪክን የሚያስተካክለው ሰው የነገን የተለያዩ ገጽታዎችን መቆጠጣር እንደሚችል መታመኑ የብሔረተኛ ልሂቃን፣ የመሪዎች እና የማህበረሰብ አንቂዎችን እንቅስቃሴ የሚወስን ይመስላል። አሁን እነዚህ እርስ በራሳቸው የሚጋጩ የታሪክ ምስሎች  ታሪካዊ መሰረትን፣ ያለፉ ወርቃማ ዘመናትን፣ ያለፈ ግዜ ናፍቆትን እንዲሁም የቦታ እና የጊዜ መታጣትን ስሜቶች ለግለሰቦች በማውረስ ከቡድኖች ማንነት ምስረታ እና ህልውና ጋር ተቆራኝተዋል። በመሆኑም በታሪክ ላይ የሚደረግ ትግል በማህበረሰባዊ ማንነት ላይ የሚደረግ ትግል ሆኗል።

   ያለፈው ታሪክ የሰዎችን ስሜት እንዲቀሰቅስ፣ ተግባራትን እንዲፈጽሙ እንዲያነሳሳ፣ ብሎም በራሱ አንዳች የማህበራዊ አና ባህላዊ የድርጊት መንገድ እንዲሆን በመፈቀዱ የጋራ ብሄራዊ ምልክቶችን፣ ትርክቶችን፣ እንዲሁም ከተለያዩ ጎሳዎች የወጡ ብሔራዊ ጀግኖችን መጋራት አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጓል። እንዲህ ያለው የአንጽሮተ-አለም ቀውስ ወደፊት ከዘለቀ፤ ከሐገር መፍረስ በተጨማሪ፤ ታሪክን መዘከር የማይቻልበት እና የወደፊቱ ባዶ የሚሆንበትን ጨለምተኛ የፖለቲካ ዐውድ ሊገነባ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ምድራዊ ገነትን ቃል የሚገቡ የቀደምት ዘመናትን ናፋቂ እንቅስቃሴዎች በየቦታው ሊያብቡ ይችላሉ። ነገር ግን የመፍትሔ ርምጃዎች በፖለቲካዊ እና መዋቅራዊ ደረጃዎች ብቻ ሳይሆን በቅድመ-ፖለቲካ ደረጃ ጭምር ተግባራዊ መደረግ ከቻሉ ጨለማውን መሻገር ይቻላል።

   የጋራ ምልከታ እና ቅድመ–ፖለቲካ

   ምንም እንኳን ጥቂት የሚጋጩ የታሪክ ትርክቶችን ለማስታረቅ የተደረጉ ሙከራዎች ቢኖሩም፣ አሁን የሚታየውን የታሪክ እና የጎሳ፣ የቋንቋ ተኮር ጉዳዮች ውህደትን ለመነጠል የሚደረጉ ጠንካራ ሃገራዊ ጥረቶች አልታዩም። በተቃራኒው አንድን የታሪክ ትርክት ከሌላው አስበልጦ በመምረጥ ቅቡል እንዲሆን ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች የሀገሪቷ የፖለቲካ ልሂቃን የእለት ተእለት ተግባር ሆኖ ቀጥሏል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ፤ ከፋፋይ የታሪክ ገጾችን በ”አንድነት” ንግርት ውስጥ በደምሳሳው የመዘንጋት እና ታሪካዊ ማንነቶችን የማረም ይፋዊ ፍላጎቶች አዘንብለው መስተዋል ጀምረዋል። እንዲህ ያሉ ከአለፈ ታሪክ ለመራቅ የሚደረጉ ጭፍን እምቢተኝነቶች በይፋ ለሚጠየቁ የታሪካዊ በደል ጥያቂዎች መልስ ሊሆኑ አይችሉም። ሆን ብሎ ታሪክን መዘንጋት ድሮ የተደረጉ ኢፍትሃዊ ተግባራትን እንደ መደገፍ ሊቆጠር ይችላል። አሁንም ድረስ ቀድሞ በተፈጸሙ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ተጠቂ የሆኑ የፖለቲካዊ ህብረተ-ሰብ አባሎችን ሆን ብሎ የመናቅ ተግባር ተደርጎም ሊታይ ይችላል።

   ኢትዮጵያ ልትጠቀም የምትችለው ከጋራ ምልከታ፣ ማሰላሰል እንጂ በጋራ ከማስታወስ ወይም መዘንጋት አይደለም። አሁን ካለው ውጥንቅጥ ለመውጣት የሚቻለው፣ በገንቢ እና ሃቀኛ ውይይቶች ላይ የተመረኮዘ አዲስ ማህበራዊ ስነ አመክንዮን በመጠቀም ብቻ ነው። አንዱ የሌላውን ቅቡልነት በማክበር፣ በፍላጎቶች እና አቋሞች ላይ በቀጥታ የሚደረግ ድርድር ታሪክን ከብሄር እና ቋንቋ ለመነጠል ያስችላል። የሁሉንም እውነት ህጋዊ ማድረግ እና ለህዝብ የሚደርስበትን መንገድ ማመቻቸት፤ የተለያዩ ብሔራዊ እንቅስቃሴዎች ከያዙት የብሔራዊ ኩራት እና ሃፍረት ስሜት መሃል ያለውን ሚዛን መጠበቅ አስፈላጊ ነው። በታሪክ የተደረጉ በደሎች እና ስኬቶችን ሙሉ እውቅና መስጠት እና ተቀባይት እንዲያገኙ ማድረግ አዲስ ፖለቲካዊ ማህበረሰብን ለመፍጠር የሚያስችል ትልቅ አንቀሳቃሽ መርህን ይገነባል። ይህም ያለፈው ቁስል እንዲሽር እና አሁን ያለውን የእውነታ አረዳድ ለማስተካከል እና ሰላማዊ የጋራ የወደፊት ራዕይ እንደገና እንዲታለም ያግዛል።

   የጋራ ምልከታ የሌላውን እውነት መፍቀድ ብቻ ያካተተ ሳይሆን፣ የብሔርተኛ እንቅስቃሴዎች እና መሪዎቻቸው ያለፈ ታሪክን ፖለቲካዊ ከማድረግ እንዲቆጠቡ የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶችንም ማካተት አለበት። በማህበረሰብ አንቂዎች የሚደረጉ ታሪክን ዳግም የመተንተን ሁነኛ ሚናዎች ቁጥጥር ሳይደረግባቸው መታለፍ የለባቸውም። እውነተኛ ታሪካዊ በደሎችን እለት ተእለት ከሚፈበረኩ ሃሰተኛ ታሪኮች የመነጠል ተግባር ላይ የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። የእርቅ ሂደቶች በሁሉም ደረጃዎች መደረግ ያለባቸው ሲሆን፤ ትርጉም ካለው የፖለቲካ ውሳኔዎች ተገልለው ያሉትን ሁሉንም ማህበረሰቦች ያካተተም መሆን አለበት።

   ነገር ግን በገሃድ ከሚታዩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቁስሎች በዘለለ፤ ካልተሳኩ ሃገር የመገንባት ጥረቶች እና ማንነት-ተኮር ብሄርተኝነት ባላፈ የሌላውን እውነት ለመረዳት የሚያግድ አንዳች ነገር ያለ ይመስላል። ከፖለቲካ በላይ የሆነ ነገር እንደማለት ነው። በአፈ-ታሪኮቻችን በዘላቂነት የሚንጸባረቀው ላለፈ ታሪክ ያለን ልዩ ፍቅር፣ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ዋነኛ ሃይማኖቶች የግዜ አረዳድ ጭምር በተቃርኖ የቆመ ነው። ምናልባትም የጊዜ ግንዛቤአችንን እና የባህል ሰዋሰዋችንን በቅድመ-ፖለቲካዊ ደረጃ መመርመር ይኖርብናል። አሁን ያለንበት የእውነታ አለም ተሞክሮ፣ የምንኖርበትን አለም ውቅር እንዲሁም በውስጡ የምንኖረውን ሰዎች ቅንጅት ያሳያል ። ስለ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተሞክሯችን የምናበጀው ተራማጅ እሳቤ ህልው ስርአቱን በቅድመ–ፖለቲካ ደረጃ መለወጥ የሚሻ ነው። ስለ ስነ- ምግባር፣ መልካምነት፣ ፍትህ፣ ግዜ እና የመሳሰሉት ያሉን ግንዛቤዎች አዲስ ፖለቲካዊ ተምኔት ብሎም ድርጊት እንዲኖረን ማስቻል አለባቸው።

   በመሆኑም የምንኖርበትን እውነታ ቅርጽ በህቡዕ የገነቡትን ዲበ-አካላዊ መላምቶቻችንን በመመርመር አሁን የምንገኝበት ተሞክሮ ያለፈ ታሪካችንን እንዲያንጸባርቅ የሆነበትን ምክንያት በጥልቀት እንድንረዳ እና ለምን እንደዛ እንደሆነ እንድንጠይቅ ያስችለናል። ፌደሪኮ ካምፓኛ የሚባል ምሁር እንደሚያነሳው “ለምሳሌ አሁን ያለንበት ጊዜ ልዩ የሚያደርገው ዋና መሰረት ከሌሎች ያለፉ ጊዜያት ጋር ምን ይለየዋል? እንዲህ እና እንዲያ ያሉ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ገጽታዎች እንዲፈጠሩ ምን አይነት ዲበ-አካላዊ መላ ምቶች ወሳኝ ናቸው? የማህበራዊ ተቋማትን ህቡዕ ስነ-ምግባራዊ ግቦች ለማስረገጥ የትኛው አውቀት ያስፈልጋል?” የሚሉ እና ሌሎችም ጥየቄዎችን ማንሳት ተገቢ ነው።

   አሁን ወደ ኋላ መመለስ የማንችልበት ቦታ ደርሰናል። ያለፈ ታሪክን የተመለከቱ መሰረታዊ አለመግባባቶች ወደ አላስፈላጊ ደም መቃባቶች አምርተዋል። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የእርስ በርስ ጦርነቶች ሃገሪቷን እያፈረሱ ናቸው፤ እንዲህ ያለው ሁከት እንዲከሰት ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል ያለፈ ታሪክ ፖለቲካ አንዱ ነው። ትናንትን ለማምለጥ የማንችል ከሆነ፤ ቢያንስ ጭለማ ጥላዎቹ እንዲደበዝዙ ለማድረግ መሞከር ያስፈልጋል። አዲስ ፖለቲካዊ ምናቦች፣ አዲስ ፖለቲካዊ አማራጮችን ማለምን፣ ቀድሞ ማሰብን ይሻል። ህልውናዊ ጥፋትን ለመጋፈጥ፣ የተራዘመ የግዜ ምልከታ ያሻል። ጊዜ ባዶ ነገር አይደለም፡ ወደ ፊት ሊሆን የሚችለውን አማራጭ እና የወደ ፊቱን እርምጃ በውስጡ አካቷል። “በጊዜ ውስጥ” ይላል ዕውቁ የሥነ-መለኮት ተመራማሪ ፖል ቲሊች “የወደፊት ነገራችንን እንወስናለን፣ እኛም እንወሰናለን”። ይህን አስመልክቶ፣ ስመ-ጥሩ ባለቅኔ ክቡር አቶ ከበደ ሚካኤል ‹‹ዓለም እና ጊዜ›› የተሰኘው ስራቸው፣ የህልውናን እውነታ ካለፈ ጊዜ ጋር ያለውን ግንኙነት ማሰብ መታለል እንደሆነ እንደሚከተለው አስፍረውታል፡

   አንዱ ስፍራ ሲለቅ፥ አንዱ እየተተካ፣

   ሁሉም ርስቴ ነች፥ እያለ ሲመካ፣

   ሞኝነት አድሮብን፥ ሳናስበው እኛ፣

   ዓለም ሰፈር ሆና፥ ሕዝቡ መንገደኛ፣

   ትውልድ ፈሳሽ ውሃ፥ መሬቷም ዥረት፣

   መሆኑን ዘንግቶ፥ ይህ ሁሉ ፍጥረት፣

   ስትመለከቱት፥ በሰልፍ ተጉዞ፣

   ሁሉም በየተራው፥ ያልፋል ተያይዞ። (ከበደ ሚካኤል፣ የቅኔ አዝመራ)

   በታሪካዊ ጊዜ ውስጥ በመኖራችን ምክንያት ብቻ፤ “በግዜአዊው ውድመት” ውስጥ “የዘላቂው ጊዜን መገለጫዎች”፤ እንዲሁም ከአሁኑ ግዜ ተሻግረው ያሉትን የሰዎችን (ፖለቲካዊ) አማራጮች መመልከት እንችላለን። ያለፈ ታሪካችንን ለማስታረቅ፣ ለማከም፣ እና ዳግም ለማጣመር የሚደረግ ጥረት ማህበራዊ፣ መንግስታዊ ተቋማትን ማሳተፍ እንዲሁም ማህበራዊ ባህልን፣ እውነተኛ ብዝሃ-ባህል ስርአትን፣ ዴሞክራሲያዊነትን እና የመሳሰሉትን የማዳበር ሂደት ብቻ ሳይሆን፤ በፍልስፍና፣ ሥነ-ልቦና፤ ሥነ-መለኮት፣ ስነ-ጥበብ፣ እና ሌሎች ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ነገሮችን የሚያሰላስሉ መስኮች ላይ የተሰማሩትን ባለሞያዎች የተለየ ጥረት እና ራዕይ ይጠይቃል።

   ኢትዮጵያ ካለፈ ታሪክ ትውስታ ውጥረት መላቀቅ አለባት። ብሔርተኛ ልሂቃን እንዲሁም ማህበረሰቡ በአጠቃላይ ያልተገደበ የማህበረሰብ ለውጥ እና እድገት ማምጣት የሚቻልበትን መንገድ ማሰላሰል አለባቸው። ሆን ተብሎ በሚደረጉ ማሳሳቻዎች እና በታሰበባቸው ውሸቶች ታሪክን ለማወክ የሚሞክሩ አካላት ፖለቲካዊ ሃይል ሊገረሰስ ይገባዋል። እንዲሁም ያለፈው ታሪክ ከፋፋይ ሁነቶች በመዋቅራዊ እና ቅድመ- ፖለቲካዊ ደረጃ እንዲመረመሩ ያስፈልጋል።

Viewing 0 reply threads
Reply To: ኢትዮጵያ:- ባለፈ ታሪክ የምትዋልል አገር
Your information: