የአዲስ ዓመት የሰላም ጥሪ - ከአገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች

ባሁኑ ወቅት አገራችን ኢትዮጵያ በከባድ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች። በትግራይ፣ በአማራ፣ በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ፣ በሶማሊ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በሚካሔዱ ግጭቶች ምክንያት በሺሕ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን እየሞቱ ነው። በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ከቀያቸው እየተፈናቀሉ ነው። ሚሊዮኖች የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ እየሆኑ ነው። ሕፃናት ልጆቻችን፣ በዕድሜ የገፉ ወገኖቻችን እና ሴቶቻችን በተለየ ሁኔታ ለመከራ ተጋላጭ እየሆኑ፣ ጾታዊ ጥቃትንና ግድያን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ ጥሰቶች ሰለባ በመሆን ላይ ናቸው። ኢኮኖሚያችን በከፍተኛ ደረጃ እየተጎዳ፣ መሠረተ ልማቶች እየወደሙ  ነው። ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት የምንጠቀምባቸው የሽምግልናና የዕርቅ ባሕላዊና ማኅበራዊ አቅሞቻችንን ለመጠቀም እያደረግን ያለነው ሁለገብ ጥረት እስካሁን ሰላምን ሊያረጋጋጥልን አልቻለም።  በመሆኑም ሕዝባችንን ለዘመናት ደግፈው ያቆዩ ማኅበራዊ እሴቶቻችን ሳይቀሩ አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ። በዚህ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ በመቆየት የምናገኘው ነገር ቢኖር ያሁኑ ማኅበራዊ ግንኙነታችንን የበለጠ ማሻከር ብቻ ሳይሆን፥ ለመጪው ትውልድም ቂምና ቁርሾ ማውረስን ሊሆን ይችላል። 

ይህንን የአዲስ ዓመት የሰላም ጥሪ ለማስተላለፍ የተሰባሰብነው የአገር በቀል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ላለፉት በርካታ ወራት በኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶች በአስቸኳይ መቆም አለባቸው፣ ለሰላም ዕድል ሊሰጠው ይገባል በሚል ግልጽ ጥሪ ለማቅረብ የወሰንነው፣ በሚከተሉት ምክንያቶች ነው። 

  1. ለጦርነቱ መንስዔ የሆኑት የተለያዩ የፖለቲካ ችግሮችን በጦርነት በዘላቂነት ሊፈቱ የማይችሉ በመሆናቸው፣ ይፈታሉ ተብሎ ቢታመን እንኳን መንግሥትን እና መላው የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚያስክፍለው ዋጋ የከፋ መሆኑን ከግምት በማስገባት፤
  2. ጦርነት እና ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ደኅንነት ጉዳይ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ፣ በተለይም ሕፃናት፣ ሴቶች እና አረጋውያን ለከፍተኛ አደጋ እየተጋለጡ በመሆናቸው፤
  3. ጦርነቱ በተለይም በወጣቱ የማኅበረሰብ ክፍል ላይ እያስከተለ ያለውን እልቂትና ኢኮኖሚያዊ ውድመት፣ እንዲሁም የከፋ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በመመልከት፣ ይህም ኢትዮጵያ ከገባቻቸው ዓለም ዐቀፍ ሥምምነቶች እና ራሷም ማክበር ከምትፈልጋቸው መብቶች ጋር የሚጣረስ በመሆኑ፣ የአገራችንን የልማት ጉዞ ወደኋላ የሚመልስ እና የዘላቂ የዕድገት ግቦችን ለማሳካት ከፍተኛ እንቅፋት የሚፈጥር ሆኖ በማግኘታችን፤
  4.  ግጭቶቹ እየተስፋፉ በርካታ አካባቢዎችን እያዳረሱ በመሆናቸው እና  አሁን መቆም ካልቻለ እጅግ ወደ ከፋ ቀውስ ከመግባታችን በፊት ተነጋግሮ ለመግባባት እና ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችል ሥራ መሠራት ስላለበት፤
  5. ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራዎቹ እየተባባሱ ወደ አገር ዐቀፍ እና ንዑስ አህጉራዊ ቀውስ ሊያመሩ የሚችሉ በመሆኑ፣ በተለይም ጦርነቱ በመሠረተ ልማት አገልግሎቶች ላይ እያደረሰ የመጣውን ጉዳት ከግምት በማስገባት፣ ከከፋ ድህነት ለመውጣት በመጣር ላይ የምትገኘው አገራችንን በሌሎች ዘርፎች ላይ ማዋል ያለባት መዋዕለ ነዋይ በጦርነት ላይ ማዋል መጀመርዋ ያለውን ጉዳት በመረዳት፤
  6. ጦርነቱ በማኅበራዊ ግንኙነቶች ላይ ያስከተለውን ጉዳት በመገንዘብ በተለይም በኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የሕዝብ ለሕዝብ አዳሪ ቂምና ቁርሾ እያፈሩ ሊመጡ የሚችሉ መሆናቸውን በመመልከት፤
  7. ቀውሶቹ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ዘላቂ ጥቅም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠሩ፣ ለውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ተጋላጭነታችንን እየጨመሩ በመሆኑ እና የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ኅልውናን የሚፈታተን አደጋ በመደቀኑ፣
  8. ለግጭቶቹ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት አዳጋችነቱ እያደር እያሻቀበ በመምጣቱ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎች ዘንድ የዳበሩ ከጦርነት ወጪ ግጭቶች የሚፈቱባቸው፣ ከጦርነት በኋላም ዕርቅ፣ ሰላምና ፍትሕ ማምጣት የሚችሉ፣ ረቂቅ ልምዶች ስላሉ ለነዚህ የሰላም እሴቶችና ተሞክሮዎች የፖለቲካ ልኂቃኑ ዕድል እንዲሰጡ፣ ሰላምን መገንባት የሚያስችል ቅድመ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ፤
  9. በ2020 የተጀመረውን የአፍሪካ “ነፍጥን  ዝም የማሰኘት ዘመቻ” (“silencing the guns campaign”) የሰላም ጥሪዎች እና መግባባት ሊፈጥሩ የሚችሉ ንግግሮችን ማድረግ የሚጀመር በመሆኑ፤
  10. የጦርነቱ መባባስ እና እየተስፋፋ መምጣት በተለይም የአገር ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በአግባቡ የመከታተል፣ የመመዝገብ እና የማጣራት ሥራ ላይ እየፈጠረ ያለው ችግርን በመረዳት፣ ይህም በኢትዮጵያ የተለያዩ አስተዳደር ክፍሎች ካለው የግንኙነት አገልግሎት መቋረጥ እና ነባራዊ የደኅንነት ተግዳሮቶች ጋር የተያያዘ መሆኑን በመገንዘብ፤

ስለሆነም ሥማችን ከዚህ በታች የተዘረዘረው አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እነዚህ ግጭቶች አስቸኳይ መቋጫ ያገኙ ዘንድ ይህንን የአዲስ ዓመት የሰላም ጥሪ እያስተላለፍን በአገራችን የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ግጭቶችን በሰላማዊ መንገዶች ለመፍታት ብሎም ሁለንተናዊ  የሰላም ግንባታ ሥራ እና  ሁሉን ዐቀፍ  ዕርቅ እንዲደረግ  የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ እንዲያተኩሩ በአክብሮት  ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የሰላም ጥሪያችን የተሳካ ይሆን ዘንድ በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች በግጭቶች ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከነውጠኛ ግጭቶች፣ ከግጭት አባባሽ ሁኔታዎች እና ከጦርነት ፕሮፓጋንዳዎች በመቆጠብ ለሰላማዊ ንግግሮች ራሳቸውን እንዲያስገዙ እና የብዙኃኑን ደኅንነትና አብሮነት፣ የአገራችንን ሰላምና ሉዓላዊነት ከአደጋ እንዲከላከሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
እኛም እንደ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ግጭቶችን በሰላማዊ መንገዶች ለመፍታት እና ከዚያም ሁለንተናዊ  የሰላም ግንባታ ሥራ እና  ሁሉን ዐቀፍ  ዕርቅ እንዲሰፍን  ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት ቃል እንገባለን።

የዚህ የሰላም ጥሪ አቅራቢ ድርጅቶች

  1. የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት (CEHRO)
  2. የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD)
  3. ኢስት አፍሪካን ኢንሼቲቭ ፎር ቼንጅ (I4C) 
  4. የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች
  5. ሴታዊት ንቅናቄ
  6. የኢትዮጵያ አርታኢያን ማኅበር
  7. ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ
  8. ኢኒሺዬቲቭ አፍሪካ
  9. ፋሚሊ ሰርቪስ አሶሲዬሽን
  10. ዓለምዐቀፍ የመነቃቃት አገልግሎት
  11. የብሔራዊና ቀጠናዊ ትስስር የጥናት ማዕከል
  12. የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር (EWLA)
  13. የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል
  14. ትምራን
  15. ሴንተር ፎር ጀስቲስ
  16. ሴንተር ኦፍ ኮንሰርን
  17. መልካም አስተዳደር ለአፍሪካ-ምስራቃዊ አፍሪካ
  18. የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (NEWA)
  19. ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ
  20. ጌት ፎር ኦፖርቹኒቲ
  21. ኒው ሚሌኒየም
  22. ሁሉን አቀፍ ራዕይ ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ
  23. ኢትዮጵያን ኢኒሺዬቲቭ ፎር ሂዩማን ራይትስ
  24. የኢትዮጵያ ሚዲያ ሴቶች ማኅበር

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.