ግልጽ ጥሪ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና የሐሳብን የመግለጽ ነጻነት

ሚያዚያ 25፣ 2014

አዲስ አበባ

ለ፦ ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስተር፣

የክልል ርዕሰ መስተዳደሮች፣

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር፣

የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣

የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር፣

የኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር፣

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፣  

የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር፣

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር፣

ክቡራትና ክቡራን፣

“ጋዜጠኝነት በዲጂታል ከበባ ውስጥ” በሚል መሪ ቃል ዛሬ እየተከበረ ያለውን የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን ምክንያት በማድረግ እኛ የዚህ ግልጽ ጥሪ ደብዳቤ ፈራሚ ድርጅቶች ሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪዎች እና ተዋናዮች  ከግጭት ቀስቃሽ እና ሰብዓዊነት ከጎደላቸው ንግግሮች እንዲቆጠቡ እንጠይቃለን። በተጨማሪም የተቋረጡ የመገናኛ ዘዴዎችን ወደነበሩበት በመመለስ ያልተገደበ የመረጃ ተደራሽነትን እንዲያረጋግጡ እንጠይቃለን።

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሚያስመሰግን የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች ብታደርግም ቅሉ፣ የደቦ ጥቃት፣ በይነማኅበረሰባዊ ግጭቶች እና ጦርነትን ያካተተ የፈተና ጊዜ እያሳለፈች ነው። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያለው ጦርነት ከሁሉም ግጭቶች የከፋ ሲሆን ለበርካታ ንፁኃን ዜጎች ስቃይ መንስዔ ሆኗል። በአገር ዐቀፍ ደረጃ እንደ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ካውንስል ከኢሰመኮ ጋር በመተባበር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች ያሉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች በርካታ የሰብዓዊ መብቶች ክትትሎችን እና ምርመራዎችን በማከናወን የተለያዩ መግለጫዎችን ያወጡ ሲሆን፥  አንዳንዶቹም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊነት የሕግ ማዕቀፍ የጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ተብለው የተቀመጡትን ድንጋጌዎች የሚያሟሉ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለዋል። በተጨማሪም፣ በምርመራዎቹ በሁሉም ተዋጊ አካላት ፆታዊ ጥቃትን የጦር መሣሪያ ያደረገ ድርጊት መፈፀሙን አረጋግጠዋል።

እኛ የዚህ ግልጽ ጥሪ ደብዳቤ ፈራሚዎች፣ እነዚህ ግጭቶች፣ የንፁኃን ዜጎች ጭካኔ የተመላባቸው የመብቶች ጥሰቶች፣ የዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብቶችና የሰብዓዊነት ሕጎች ጥሰቶች እና የተለያዩ ገደቦች በግጭት ቀስቃሸ መልዕክቶች፣ በጥላቻ ንግግር፣ በተሳሳተ መረጃና በጦርነት ፕሮፓጋንዳ ዐውድ ውስጥ የተከሰቱ መሆናቸውንና  ለግጭቶቹ መባባስ፣ ብሔርን መሠረት ላደረገ ጥቃት፣ ለሰብዓዊ መብቶችና ለዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊነት ሕጎች መጣስ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጋቸውን እናምናለን።

በአሁኑ ወቅት በትግራይ ጦርነት ዋና ዋናዎቹ ተዋናዮች በሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ለሰብዓዊነት የታወጀ ጊዜያዊ ዕርቀ ሰላም ሊያወርዱ ተሥማምተዋል። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥትም አገራዊ ምክክር እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል፤ ለዚህም፣ ሒደቱ አነጋጋሪ ቢሆንም ኮሚሽነሮች ተሰይመዋል። ይህንን ጅምር እያበረታታን እና አገራዊ ምክክሩ ምክክሩ ሁሉን አካታች እና ግልጽ እንዲሆን ከመጠየቅም ባሻገር በጦርነቱ ተሳራፊ ወገኖች የገቡትን ሰላም የማውረድ ቃል እንዲፈጽሙ እያሳሰብን፣ እኛ የዚህ ግልጽ ደብዳቤ ፈራሚዎች፣ እነዚህ ተዋናዮች እና ሌሎችም በመላው ኢትዮጵያ በተከሰቱ ግጭቶች ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ሁሉ ሰብዓዊነት ከጎደላቸው ንግግሮችና በግጭት ቀስቃሽ ተግባራት ከመሳተፍና ግጭቶችን ከማባባስ እንዲቆጠቡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።  

በጦርነቱ እና ከጦርነቱ በፊት ፕሮፓጋንዳ፣ በሐሰት መረጃዎች ዘመቻ እንዲሁም በመረጃ ተዳራሽነት ገደቡ ምክንያት እውነታው መስዋዕት ተደርጓል ብለን እናምናለን። ይህም በግጭቶቹ እና በጦርነቱ ብዙ ስቃይ ለደረሰባችው ተጠቂ ንፁኃን  ዜጎች  ተጨማሪ በደል ነው። ያልተገደበ የመረጃ ተደራሽነት እና የጋዜጠኞች ነጻነት የተከሰተውን ክፍተት በመሙላት እውነቱን እንድንረዳ ያግዘናል ብለን እናምናለን። ይህም የግጭት አፈታት እና ዕርቀ ሰላም ሙከራዎችን ያቀላጥፋል።   

ዛሬ፣ ሚያዝያ 25፣ 2014 የዓለም የፕሬስ ነጻነት “ጋዜጠኝነት በዲጂታል ከበባ ውስጥ” በሚል ዓለም ዐቀፍ መሪ ቃል እየተከበረ ነው። በኢትዮጵያ የበይነመረብ እና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች አገልግሎት በትግራይ እና በተወሰኑ አጎራባች የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች፣ በምዕራብ ኦሮሚያ እና በተወሰኑ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አካባቢዎች ተገድበዋል። በተጨማሪም ጋዜጠኞች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ፣ በዘፈቀደ ሲታሰሩና እና ክስ ሳይመሰረትባቸው፣ አልፎ ተርፎም ጎብኚዎች ተከልክለው በእስር እንዲቆዩ ሲደረጉ ተስተውሏል። ይህም ብዙኃኑ ላይ የፍርሐት እና የደኅንነት ስጋት ስሜት እንዲያድርባቸው እንዲሁም የሲቪክ ምኅዳሩ እንዲጣበብ አድርጓል። ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭቱን ለማስቆም ያለውን ቁርጠኝነት እንዲያረጋግጥ እና የታቀደውን አገራዊ ምክክር ለጋዜጠኞች እና ለዜጎች ያልተገደበ የሚዲያ እና የግንኙነት ዘዴዎችን በመፍቀድ እንዲያበረታታ እንዲሁም የዜጎችን ስቃይ ለማስቆም እና እውነትና ፍትሕን ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ላይ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ እናቀርባለን።

እኛ ከዚህ ግልጽ ደብዳቤ ፈራሚዎች መካከል የተወሰንነው እና ሌሎችም የኢትዮጵያ የ2014 አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ “ግልጽ የአዲስ ዓመት የሰላም ጥሪ” አቅርበን እንደ ነበር ይታወሳል። በዛሬው ግልጽ ደብዳቤያችንም ይህንኑ ጥሪያችንን በማደስ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት የጦርነት ፕሮፓጋንዳ በማርገብ፣ ያልተገደበ የመረጃ እና ሚዲያ ተደራሽነትን ለማስቻል እንዲሠሩ በመጋበዝ ጥሪያችንን በድጋሚ እናቀርባለን።

በመጨረሻም ይህ የግልጽ ጥሪ ደብዳቤ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት በተጨማሪ ሌሎች ባለድርሻ አካላትንም፣ ማለትም የመንግሥት የዴሞክራሲ ተቋማት፣ አገር ዐቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ ሌሎች የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ወይም የግል ሚዲያዎች፣ ምሁራን፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የሃይማኖትና ጎሳ መሪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በውጪ አገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ የአገር ውስጥ እና ዓለም ዐቀፍ ማኅበረሰቦች የጦርነት ፕሮፖጋንዳን እና የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል እና የሚዲያ ነጻነትን እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን ለማሻሻል አዎንታዊ እና ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ለማሳሰብ የተደረገ ጥሪ ነው።

የዚህ ግልጽ ጥሪ ፈራሚ የሲቪል ማኅበራት፡-

  1. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)
  2. የመብቶችና ዲሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)
  3. ኢትዮጵያዊ ተነሳሽነት ለሰብዓዊ መብቶች
  4. ጠበቆች ለሰብዓዊ መብቶች
  5. አሊያንስ ፎር ፒስ ኤንድ ደቨሎፕመንት
  6. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ጥምረት
  7. የኦሮሚያ ጋዜጠኞች ማሕበር
  8. የአማራ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር 
  9. የአማራ ሴት ጋዜጠኞች ማህበር
  10. የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ትምህርት ተቋማት ማህበር
  11. የኢትዮጵያ የማኅበረሰብ ሬድዮ ብሮድካስተሮች ማህበር
  12. ሚዛን የጋዜጠኝነት ሞያ ምሩቃን ማኅበር
  13. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል
  14. ሚዛን የወጣት የሕግ ባለሙያዎች ማዕከል
  15. ኮንሰርን ፎር ኢንቲግሬትድ ደቨሎፕመንት
  16. የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር
  17. ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ
  18. የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት
  19. የኢትዮጵያ አርታኢያን ማኅበር
  20. ኢምፓቲ ፎር ላይፍ ኢንተግሬትድ አሶሲዬሽን

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.