ፍርድ ቤቱ በእነ ጃዋር መሐመድን መዝገብ ሥር ያሉ ተከሳሾች ወደ ችሎት እንዳይመጡ የሚል ትዕዛዝ በመስጠቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል
ሰኔ 10፣ 2013፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የፀረ ሽብር እና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የምርጫ ቅስቀሳ እየተደረገ ያለበት ወቅት ስለሆነ ለተከሳሾች እና ለሕዝቡ ደኅንነት ሲባል በትላንትናው ዕለት በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ ሥር ያሉ ተከሳሾችን ዛሬ በፍርድ ቤት እንዳይገኙ የሚል ትዕዛዝ ለማረሚያ ቤት ባስተላለፈው መሠረት ሁሉም ተከሳሾች አልቀረቡም።
ተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው አቤቱታ ላይ ተከሳሾች መልስ እንዲሰጡበት አቤቱታውን የላክንላቸው ቢሆንም እንኳን ተከሳሾች ዛሬ ባለመቅረባቸው የተሟላ ክርክር ማድረግ አንችልም በማለት አጭር ቀጠሮ ችሎቱን ጠይቀዋል።
የተከላካይ ጠበቆች በተጨማሪም ምንም እንኳን ችሎቱ ለታዳሚያን ክፍት ወይም በግልጽ ችሎት ቢዳኝም፣ ቁምላቸው ዳኜ የተባሉት ግለሰብ ለኢምባሲዎች ጥብቅና በመቀጠር የእነ ጃዋርን የችሎት ሒደት በሚመለከት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ባሉ ታዳሚያን ላይ የራሳቸውን አመለካከት በማቅረብ የተዛባ እና ሚዛናዊ ያልሆነ ሪፖርት በሚዲያ ላይ እያቀረቡ ስለሆነ ችሎቱ እንዲያሳስቡልን ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል።
ችሎቱም የትኛውም ዓይነት ሚዲያ፣ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ከሕግ አግባብ ውጪ ከሆነ እየሠሩ ያሉት በሕግ እና ደንብ መሠረት ይጠየቃሉ፤ ነገር ግን እስካሁን ባለው ሒደት የተለየ ነገር አላየንም በማለት አቤቱታውን ውድቅ አድርጎታል። ችሎቱ ከምርጫ በኋላ ያሉት ቀናቶች የምርጫ ውጤት የሚገለጽባቸው ቀናቶች ስለሆኑ ከተከሳሾች ደኅንነት አንፃር ቀጣይ ቀጠሮ ለ ሰኔ 21፣ 2013 ሰጥቷል።
Add a review