ዐቃቤ ሕግ በእነጃዋር መሐመድ መዝገብ 146 የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለደኅንነታቸው የጦር መሣሪያ አስታጥቄ ለመቆጣጠር እቸገራለሁ አለ
ሕዳር 7፣ 2014 - ዐቃቤ ሕግ በእነጃዋር መሐመድ መዝገብ 146 የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለደኅንነታቸው የጦር መሣሪያ አስታጥቄ ለመቆጣጠር እቸገራለሁ አለ። ዐቃቤ ሕግ ይህን ያለው ከዚህ በፊት በእነ ጃዋር መሐመድ ላይ የሚሰሙ ምስክሮች በግልጽ ችሎት እዲሰሙ የተሰጠውን ብይን በመቃወም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ባቀረበበት በዛሬው ቀጠሮ ነው።
በዚህ ችሎት ዐቃቤ ሕግ የፍርድ ቤት ምስክሮች ጥበቃ አንጻር ለምስክሮች ጥበቃ እንዲደረግ እንዲሁም 136 ከመጋረጃ ጀርባ፣ እንዲሁም 10 ምስክሮች ደግሞ በዝግ ችሎት ይመስክሩ ያለው ጥያቄ ውድቅ መደረጉ የምስክሮቼን ደኅንነት ያገናዘበ አይደለም በማለት አቤቱታ አሰምቷል።
በዚህም አቤቱታ ላይ በመነሳት ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ዐቃቤ ሕግን ለምስክሮች ምን ጥበቃ አደረጋችሁ በማለት ለጠየቀው ጥያቄ ዐቃቤ ሕግ አሁን ካለው አገራዊ ሁኔታ አንጻር 146 ምስክሮቼን መሣሪያ አስታጥቄ መቆጣጠር እቸገራለሁ ሲል ገልጿል።
ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ አቤቱታቸውን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ለሕዳር 24 ቀን ሰጥቷል።
በሌላ በኩል በእነ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሀምዛ አዳነ (ቦረና) እና ደጀኔ ጣፋ ፍርድ ቤት አንቀርብም በማለታቸው በሌሉበት ምስክር እንዲሰማ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም በጠበቆቻቸው በኩል 5 ነጥብ በማንሳት የይግባኝ አቤቱታ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አስገብተዋል።
አቤቱታዎቹ
- በፍርድ ቤት የተፈቱ ባስፈፃሚ አከላት እየታሰሩ ባሉበት ጊዜ ፍርድ ቤቱ ሳይመረምር ውሳኔ መስጠቱ ተገቢነት የለውም፣
- ተከሳሾቹ አንቀርብም ቢሉም እንኳን በሕጉ መሠረት አስገድዶ መቅረብ እየተቻለ በሌሉበት መባሉ ተገቢነት የለውም፣
- በሌሉበት ጉዳያቸው ይታይ ቢባል እንኳን አስቀድሞ ለተከሳሶች በሰነድ መቅረብ ነበረበት፣
- ትዕዛዙ ለየትኛው ክርክር እንደሆነ ግልጽ አይደለም፣
- በእስር በማረሚያ ቤት እያሉ በሌሉበት መባሉ ልክ አይደለም በማለት የይግባኝ አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት አስገብተዋል።
ፍርድ ቤቱም አቤቱታቸውን መርምሮ ያስቀርባል አያስቀርብም ለማለት ለሕዳር 24 ቀን ቀጠሮ ሰጥቷል።
Add a review