እስክንድር ነጋ ፍርድ ቤት ባለመቅረባቸው የዐቃቤ ሕግ ምስክር ሳይሰማ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል

ጥቅምት 11, 2014 - ችሎቱ ከመጀመሩ በፊት በመዝገቡ ሁለተኛ ተከሳሽ የሆኑት ስንታየሁ ቸኮል "መንግሥት፣ ዐቃቤ ሕግ፣ የማረሚያ ቤት አስተዳደር፣ እያንዳንዱን ታራሚ የሚጠብቅ ደኅንነት አካሎች የሚያውቁት፣ በተቀናጀ መልኩ ችግሮችን በእኔ እና በእስክንድር ላይ ለመፍጠር፣ ከውጪ እገዛ ያለው በደኅንነት የታጀበ የሚንቀሳቀስ ሰዎች አሉ " ስለዚህ ፍርድቤቱ ይወቁልን ብለዋል። በተጨማሪም እስክንድር ነጋ ትላንት ከፍርድ ቤት መልስ ማታ 1:20 ወደ ማረሚያ ከገቡ በኋላ ከባድ ነገር ስለገጠማቸው መቅረብ እንደማይችሉ እንድነግርላቸው ልከውኛል፤ ምን እንደደረሰባቸው፣ መቅረብ በሚችሉበት ግዜ እንዲያስረዱ አጭር ቀጠሮ ጠይቀዋል ብለዋል።

3ኛ ተከሳሽ ቀለብ ስዩም በበኩላቸው፣ እስክንድር ነጋን በተመለከተ በእንባ በታጀበ ሁኔታ ሲናገሩ፣ እስከ ዛሬ መብታቸውን በሚመለከት ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቶ በማረሚያ ቤቱ ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም ብለዋል። ለምሳሌ ያክል ጫማ እንዲያደርግ ስለማይፈቀድላቸው በነጠላ ጫማ እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል። ከዚህ በፊት መሔድ አቅቷቸው ወድቀው እንደነበር፣ እርሳቸውም ደግፈው እንዳመጧቸው ከተናገሩ በኋላ፣ የጥየቃ ግዜ እና ሁኔታን በሚመለከትም በቀን አንድ ሰው ለአንድ ደቂቃ ብቻ ከሌላው እስረኛ በተለየ መልኩ እንደተገደበባቸው፣ አሁንም ቢሆን ከመሞታቸው በፊት ፍርድ ቤቱ ሴራው የግድያ ነው አይደለም የሚለውን ቀርቦ በመጠየቅ መመርመር አለበት ብለዋል። አክለውም፣ ነው ወይስ መንግሥት የፖለቲካ ተቀናቃኞቹን በዚ መልኩ ነው የሚያጠፋው? በማለት አቤቱታቸውን አቅርበዋል።

ፍርድ ቤቱ የማረሚያ ቤቱ ተወካይን እስክንድር ነጋ ያልቀረቡበትን ምክንያት ጠይቀዋቸው፣ እስክንድር ነጋ ማታ ከሰው ጋር ስለተጣሉ መውጣት እንደማይፈልጉና ወደ ሕክምናም እንውሰድህ ሲባሉ ፍቃደኛ እንዳልሆኑ ነው የማውቀው የሚል ምላሽ ለፍርድ ቤቱ ሰጥተዋል።

በተያያዘ የአድማ ብተና ሽፍት ኃላፊ ዋ/ሳጅን መስፍን ግርማ ማታ ላይ እስክንድር ነጋ ከሰው ጋር ተጣልተዋል የሚል ነገር ሰምተው ሔደው መጠየቃቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል። ዋና ሳጅኑ፣ እስክንድር ነጋ ስለመጣችሁ አመሰግናለሁ ብለውን ነገር ግን ወደ ፍርድ ቤትም ይሁን ወደ ሕክምናም መሔድ እንደማይፈልጉ አሳውቀውናል ብለዋል። ጉልበታቸው ላይ ብቻ “ትንሽ የተሞነጫጨረ ነገር” ቢመለከቱም፣ በእነርሱ ግምገማ መንቀሳቀስ የሚችሉበት ሁኔታ ላይ ነበሩ ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ እኛ የምንረዳው ምስክር እየተሰማ ስለሆነ ተከሳሹ ማስተባበል ስላልቻሉ ምክንያት እየፈለጉ እየቀሩ እንደሆነ ነው ስለዚህ እስክንድር ነጋ ተገደው እንዲቀርቡ ለማረሚያ ቤት ትዕዛዝ ይሰጥልን በማለት ቀጠሮ እንዳይሰጥ እና ሒደቱ እንዲቀጥል ችሎቱን ጠይቀዋል።

በተያያዘም ተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው እስክንድር ትላንት ያልነበራቸው መጫጫር አለ ማለት ችግር መኖሩን ያሳያል በማለት፣ በመንግሥት ጥበቃ ሥር በሆነና በዐቃቤ ሕግ ሥር የሚተዳደር ተቋም ሥር ባሉ ግለሰብ ላይ እንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ሲደርስበት፣ እንደሰብዓዊነት ይታከሙ እንጂ ተገደው ይቅረቡ ማለት ተገቢ አደለም ካሉ በኋላ፣ በሕጉ መሠረት፣ ተከሳሽ በአሳማኝ ምክንያት የቀሩ እንደሆነ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጣል ይላል። ስለዚህ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠንና ተከሳሽም ምን እንደደረሰባቸው ቀርበው ያስረዱ። ይህ መሆን ካልቻለም፣ ከተከሳሹ አንደበት ጠበቆች ሰምተን እናስረዳ ብለው ችሎቱን ጠይቀዋል።

ችሎቱን ሲታደሙ የነበሩ ታዳሚዎች እስክንድር ነጋ ላይ ደረሰ በተባለው ጉዳት በእንባ ታጅበው በስሜታዊነት ችሎቱን አቋርጠው ወጥተዋል።

ችሎቱም የስንታየው ቸኮልን የሕክምና ጥያቄ ሚመለከት፣ ማረሚያ ቤት አስተያየት ይስጥበት ብሎ የሰጠው ትዕዛዝ መልስ ባለመቅረቡ፣ ሰኞ እንዲቀርብ በተጨማሪም እስክንድርም በሰኞው ችሎት እንዲቀርቡ እና እርሳቸው በተገኙበት ምስክር የማድመጥ ሒደቱ እንዲቀጥል ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ማስታወሻ፦ የፍርድ ቤት ዘጋቢያችን ካደረሱን መረጃ በተጨማሪ እስክንድር ነጋ በሊቀ መንበርነት የሚመሩት የፖለቲካ ፓርቲ (ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ) በፌስቡክ ገጹ እስክንድር ላይ ድብደባ መፈፀሙን በፍርድ ቤት ከተነገረ በኋላ ፍርድ ቤቱ ውስጥ ታድመው የነበሩ ሰዎች ታፍሰው መታሰራቸውን ዘግቧል። የታሰሩት ሰዎች ቁጥር 42 ሲሆን፣ በማግስቱ ፍርድ ቤት ቀርበው ሁለቱ በዋስ ተለቀዋል። በተመጨማሪም፣ እስክንድር ነጋ የግራ እግር አውራ ጣታቸው መሰበሩን ፓርቲው ፖሊስ ሆስፒታል በተደረገላቸው ሕክምና መረጋገጡን ዘግቧል

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.