በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ ዐቃቤ ሕግ 12 ምስክሮች ላይ የተሰጠውን ውሳኔ በይግባኝ አሳርመን እስከምንመጣ ለግዜው ይታለፉ አለ
ሕዳር 6፣ 2014 - የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎ በእነ እስክንድር መዝገብ የቀጠረው ቀሪ ሦስት የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ለማድመጥ፣ ማንነታቸው ያልተገለጹ 12 ምስክሮች ማንነታቸው ተገልጾ እንዲቀርቡ እና የአስካል ደምሌ አቤቱታ ላይ ምላሽ ለመስጠት ነው።
ዐቃቤ ሕግ በችሎቱ እንደገለጸው 4ኛ ምስክር ከኮሮና ገና ማገገማቸው በመሆኑ በዚሁ ምክንያት የድካም ስሜት ስላለባቸው ለነገ በይደር እንዲቀርቡላቸው፤ 8ኛና እና9ኛ ምስክሮች በፍርድ ቤቱ መጥሪያ እንዲቀርቡ ለፌደራል ፖሊስ ትዕዛዝ እንዲሰጥበት ያመለከትን ቢሆንም ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትዕዛዝ ፖሊስ "አልደረሰንም" በማለቱ ምስክሮች ማቅረብ አልቻልኩም ብሏል።
ቀሪ 12 ምስክሮች በተመለከተ ይግባኝ ጠይቀን የዚህ ፍርድ ቤት ውሳኔ እስክናሳርም ድረስ ለግዜው ይታለፉ እና ቀሪ 3 ምስክሮችን እናሰማለን ብሏል ዐቃቤ ሕግ።
ተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው ታሟል የተባሉት ምስክር መታመማቸውን የሚያስረዳ ማስረጃ እንዲቀርብ ፈርድ ቤቱ ትዕዛዝ ቢሰጥም ግን በአቃቤ ሕግ በኩል የቀረበ ነገር ባለመኖሩ እንዲሁም 12ቱ ምስክሮች በሚመለከት ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ዐቃቤ ሕግ ማቅረብ ባለመቻሉ፤ ከዚህ ቀደም በቀረቡት ምስክሮች ብቻ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ የተፋጠነ ፍትሕ ይስጠን ሲሉ ችሎቱን ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱም በግራ ቀኙ የተደረጉትን ክርክሮች አድምጦ፣ በኮሮና በሽታ ሞክንያት ያልቀረቡት ምስክር ነገ ጠዋት ከነማስረጃቸው ቀርበው እንዲመሰክሩ፣ 8ኛ እና 9ኛ ምስክሮች ደሞ የፍርድ ቤት መጥሪያ በአድራሻቸው እንዲደርሳቸው እና በ09/03/2012 ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ በማለት ትዕዛዝ ሰጥተዋል። የአስካል ደምሌ እና ማንነታቸው ያልታወቁት 12 የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ላይ የቀረቡ አቤቱታዎች ላይ ችሎቱ ትዕዛዝ ለመስጠት ለነገ ቀጥሯል። ከችሎት ዘገባ ጋር በተያያዘ የምኒልክ ቴሌቭዥን በእነ እስክንድር ነጋ ክስ መዝገብ አዘጋገብ ጋር በሚመለከት በተያያዘ ዐቃቤ ሕግ በመሠረተባቸው ክስ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ይህንኑ በሚመለከት በ08/03/2014 በቀረበባቸው ክስ ላይ መልስ ይዞ እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ አዟል።
Add a review