እነስብሓት ነጋ ‘ጉዳያችን በትግራይ ክልል ፍርድ ቤት ይታይልን’ ሲሉ አቤቱታ አቀረቡ

መጋቢት 14፣ 2013 – እነስብሓት ነጋ የተጠረጠሩትን መዝገብ የሚያየው የፌደራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ሲሆን፣ በዕለቱ የተሰየመው በተከሳሾች በኩል የቀረበውን አቤቱታ ለማየት ነበር። አቤቱታው ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያችን መታየት ያለበት በትግራይ ክልል ፍርድ ቤቶች ነው ማለታቸው ነው።

በቀረበው አቤቱታ ላይ ዐቃቤ ሕግ ምላሽ ሲሰጥ፣ የተጠረጠሩበት የሽብር አዋጁን በመተላለፍ የፌደራል መንግሥትን ሥልጣን ለመጣል በሚል በመላው አገሪቱ ላይ በተፈፀመ ወንጀል መሆኑን በመጥቀስ በምሳሌነትም በባሕር ዳር እና በጎንደር የተፈፀመው የሮኬት ድብደባ በማስታወስ፥ በተጨማሪም ዶክተር አዲስዓለም ባሌማ የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ ከአዲስ አበባ በመሆን በመሳተፋቸው ድርጊቱ የተፈፀመው አንድ ቦታ አለመሆኑን ያመለክታል ብለዋል።

ዐቃቤ ሕግ ይህ የሚያሳየው ወንጀሉን በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች መፈፀማቸውን ስለሆነ በአከባቢ ሥልጣን ሳይገደቡ ጉዳያቸው መታየት ያለበት በፌዴራል ፍርድ ቤት ነው ብሏል። በተከላካይ ጠበቆች በኩል ቀዳሚ ምርመራ መደረግ የለበትም፤ ዐቃቤ ሕግ ቀዳሚ ምርመራ የጠየቁበት ሕግ ተሽሯል በማለት የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮች ሥምና ዝርዝር እዲገለጽላቸው ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩላቸው በተከላካይ ጠበቆች በኩል ለተነሱ አቤቱታዎች፣ ዐቃቤ ሕግ በቂ ምክንያት ካለው በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ስርዓት ሕግ አንቀጽ 38 ቅድመ ምርመራ ማድረግ እንደሚችል በግልጽ የተቀመጠ እንደሆነ፣ በማከልም በውንብድና ወንጀል እና የግፍ ግድያ የተፈፀመ ከሆነ ቀዳሚ ምርመራ ሊደረግ እንደሚችል እና የቀዳሚ ምርምራ ሕጉ ሙሉ በሙሉ እንዳልተቀየረ በሥራ ላይ እደሚገኝ ምላሽ ሰጥተዋል።

በተጨማሪም የምስክሮችን ሥም ዝርዝር አልተገለጸም በሚል በተጠርጣሪዎች ለተነሳው ተቃውሞ የምስክር ጥበቃ አዋጅ ተከትሎ ለምስክር ደኅንነት ሲባል የሥም ዝርዝር መስጠት እንደማይቻል ዐቃቤ ሕግ አሳውቋል። ፍርድ ቤቱ የተነሱትን አቤቱታዎች መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለመጋቢት 17 ቀን ቀጠሮ ሰጥቷል።

Center for Advancement of Rights and Democracy (CARD)

Making Democracy the Only Rule of Game!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *