ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት መንግሥት ኃላፊነቱን ይወጣ!

የዓለም የጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመጋቢት 02፣ 2012 ‘ዓለም ዐቀፍ ወረርሽኝ’ በማለት ማወጁ ይታወሳል። በአገራችንም፣ በመጋቢት 04፣ 2012 የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መገኘቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል። እስከ አሁን በኢትዮጵያ ዐሥራ ሁለት (12) በኮረና ቫይረስ ተጠቂዎች የተገኙ ሲሆን፥ በተወሰነ ደረጃም ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀላቸው ታውቋል። ቫይረሱ ፈጣን የሆነ የመተላለፍ ጠባይ ያለው በመሆኑ ይህ ቁጥር በአደገኛ ሁኔታ ሊያሻቅብና እልቂት ሊያስከትል የሚችልበት አደጋ ከፊት ተደቅኗል።

የቫይረሱ ተጠቂዎች በኢትዮጵያ ከተገኙ በኋላ በጤና ጥበቃ ሚንስቴር፣ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትት እና በጤና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች በጎ ፈቃደኞች አማካይነት በሽታውን በግለሰቦች እና ማኅበረሰብ አካላት ጥረት ለመከላከል የሚያስችል ግንዛቤ በመፍጠሩ ረገድ እየተካሄዱ ያሉ ጥረቶች አበረታች ናቸው፤ ሆኖም መንግሥት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ የተገበረው የመረጃ ዘዴዎች (ስልክ እና ኢንተርኔት) ግንኙነት ማቋረጥ ሁልጊዜም አግባብ ባይሆንም፥ በተለይም በዚህ ወሳኝ ወቅት የዜጎችን  የመረጃ የማግኘት የሚከለክል በመሆኑ ተቀባይነት የለውም። አልፎ ተርፎም ገዢው ፓርቲ ለቫይረሱ ስርጭት በር ከፋች የሆኑ በርካታ ሰዎች የሚታደሙባቸውን የፓርቲ ስብሰባዎችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በቸልተኝነት ማካሔዱ የማኅበረሰቡን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት ነው።

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) እነዚህ ድርጊቶች በመላው ዓለም በፍጥነት እየተዛመተ ያለው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት፣ በኢትዮጵያም ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊ ቀውስ እንዲያስከትሉ ሊያደርግ እንደሚችል ስጋት አለው። በመሆኑም፣ ቀውሱ ከመከሰቱ በፊት መንግሥት፦

  1. በምዕራብ ኦሮሚያ የጣለውን ሕጋዊ ያልሆነ የስልክ እና የኢንተርኔት ግንኙት በአፋጣኝ እንዲመልስና በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች መረጃ የማግኘት መብታቸው እንዲከበር
  2. የዓለም የጤና ድርጅት ከሰጣቸው ምክሮች መካከል አንዱ የሆነው ማኅበራዊ ፈቀቅታን (Social Distancing) ገዢው ፓርቲንም የሚመለከት ስለሆነ እንዲከበር፣ እንዲሁም
  3. ሁሉም ዜጎች ተከታታይ እና ወጥ የሆነ መረጃ ስለ ቫይረሱ ስርጭት እና መከላከያ ዘዴዎች እንዲያውቁ እንዲያደርግ (ይህም አካል ጉዳተኞችን፣ መስማት የተሳናቸውን፣ ዓይነ ስውራንን እና ሌሎችም ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሆን) ካርድ ጥሪውን ያቀርባል።

መጋቢት 14፣ 2012

Center for Advancement of Rights and Democracy (CARD)

Making Democracy the Only Rule of Game!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *