Photo Credit - Addis Standard

ፍርድ ቤቱ በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ ስር ያሉ ተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል መቀበል ጀመረ

  • “አሁንም ሕጋዊ መንግሥት አለ ብዬ አላምንም” – ደጀኔ ጣፋ

መጋቢት 6፣ 2013

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት ለዕለቱ ቀጥሮ የነበረው የተከሳሾችን የዕምነት ክደት ቃል ለመቀበል ቢሆንም እነ ጃዋር መሐመድ ባለመቅረባቸው በችሎቱ መጀመሪያ ላይ የተለያዩ የአካሔድ ጉዳዮች ተነስተዋል። በተለይም የተወሰኑ ተከሳሾች ያልቀረቡበትን ምክንያት የማረሚያ ቤት አመራሮች ለችሎቱ እንዲያብራሩ ተጠይቀዋል። በዚህም መሠረት ተቋሙን በመወከል ኢ/ር ድሪባ ተከሳሾቹ ሕክምና ሲከታተሉ ከነበረበት ሆስፒታል ወደ ማረሚያ ቤቱ በ05/07/2013 ማታ የተመለሱ መሆኑን፤ በ06/07/2013 ጠዋት ቀድሞ በተቀጠረው መሠረት ወደ ችሎት ለመሒድ እንዲዘጋጁ ተጠይቀው “በሐኪሞቻችን እረፍት እንደሚያስፈልገን ስለተነገረን መውጣት አንችልም” በማለታቸው በችሎቱ ማቅረብ እንዳልቻሉ መልሰዋል።

በእነ ጃዋር በችሎቱ አለመገኘት ላይ የተደረገው ክርክር እና የተሰጠው ትዕዛዝ፤

ከማረሚያ ቤት ተወካይ ማብራርያ በመቀጠል በተከሳሾች ጠበቆች እና ዐቃቤ ሕግ መካከል በጉዳዩ ብሎም የእምነት ክህደት ቃል አሰጣጥ ሒደት ላይ ክርክር ተደርጓል። ተከላካይ ጠበቆች እነ ጃዋር በተደረገላቸው የሕክምና አገልግሎት ፍርድ ቤቱን አመስግነው፣ ደንበኞቻቸው ሕክምናውን ቢጨርሱም እረፍት ማድረግ እንዳለባቸው በሐኪሞቻቸው ስለተነገራቸው አጭር ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ሌሎቹንም ተከሳሾች በሚመለከት ጉዳያቸው አንድ ዓይነት ስለሆነ እነሱም የእምነት ክህደት ቃል አንድ ላይ መስጠት ቢችሉ ሲሉ ለችሎቱ ጥያቄ አቅርበዋል። ከተከሳሾች መካከል ደጀኔ ጣፎ ለተደረገላቸው የሕክምና ትብብር ምስጋና አቅርበውበሐኪም የ5 ቀን እረፍት የተሰጣቸው መሆኑን በማውሳት ተከሳሾች የእረፍት ጊዜውን ሲጨርሱ መልስ መስጠት እንዲሚችሉ አብራርተዋል። አያይዘውም ለጠቅላይ ሚንስቴሩ እና ለመንግሥታቸው ብሎም ለጋዜጠኞች ምክር አዘል ሐሳብ ሰንዝረዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩላቸው ተከሳሾቹ የተከሰሱበት ጭብጥ አንድ ዓይነት ቢሆንም የእምነት ክህደት ቃል ግለሰባዊ እንደመሆኑ ሁሉም ተከሳሾች መገኘት እንደማይጠበቅ፣ ካልሆነ ደግሞ በወንጀል ሕግ ሥነ ስርዓት አንቀጽ 133 መሠረት ወንጀሉን እንደካዱ ተቆጥሮ ይመዝገብልኝ ሲል ችሎቱን ጠይቋል።

ችሎቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኋላ ተከሳሾች ካላቸው የቁጥር ብዛት አንፃር የተሳለጠ ፍትሕ ለመስጠት እንዲያስችል እና ዐቃቤ ሕግ እንዳነሱት የእምነት ክህደት ቃል መስጠት ግለሰባዊ አመለካከት መሆኑን በማውሳት በዕለቱ በችሎቱ ሳይገኙ ከቀሩት 3 ተከሳሾች እና አስተርጓሚ ከሚያስፈልገው ተከሳሽ ውጪ ያሉትን በዕለቱ ለማድመጥ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃል፤

የችሎቱን ትዕዛዝ ተከትሎ ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል። በዚህም መሠረት አራተኛ ተከሳሽ ሀምዛ ወንጀሉን አለመፈፀማቸውን እና የተከሰሱበት ምክንያት የፓርቲ አባል ስለሆኑ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። አያይዘውም “ከአምቦ ስልክ ተደውሎለታል” በሚል የቀረበባቸዉም ክስ ለአምቦ ብቻ ተብሎ የተሰጠ የስልክ ኮድ በሌለበት ለመከራከርም እንደሚያዳግታቸው እና ክሱም ፖለታካዊ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

አምስተኛ ተከሳሽ ደጀኔ ጣፋ በበኩላቸዉ ወንጀሉን አለመፈፀማቸውን በመግለጽ የተጠየቁበት አንቀፅ እና ክሳቸው አብሮ የማይሔድ መሆኑን ጠቅሰዋል። በተለይም “ግጭት አስነሳ” በሚል የቀረበው ክስ የሚያመለክተው “የእርስ በርስ ግጭት” ይሁን “የእርስ በርስ ጦርነት” ግልጽ እንዳልሆነ በመጥቀስ የትርጉም አሻሚነት ባለው ነገር ላይ ቃላቸውን መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል።

መስከረም 30 መንግሥት የለም ብለዋል ለተባለው “አሁንም ሕጋዊ መንግሥት አለ ብዬ አላምንም” ምክንያቱም በሕገ መንግሥቱ መሠረት የፓርላማው የሥራ ግዜ 5 ዓመት ሲሞላው እንደሚያበቃ በግልፅ የተቀመጠ ሲሆን መንግሥት የሥልጣን ቆይታውን ሕገ ወጥ በሆነ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ያራዘመ እንደመሆኑ መንግሥት የለም ማለቴ ወንጀል አይደለም በማለት ማብራሪያ አክለውበታል።

ጦር መሣሪያን በሚመለከት ለቀረበባቸው ክስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሆነ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ ያደረጉት መሆኑን አስታውሰዋል። በሀጫሉ ግድያ ሊጠየቁ እንደማይገባ፣ በሰዓቱም በቦታው እንዳልነበሩ እና የተያዙትም አርቲስቱ ከሞተ ከ6 ቀን በኋላ ቤታቸዉ ውስጥ ሳሉ ተከበው እንደሆነ በመጥቀስ ይህ የሚያሳየዉ ድርጊቱ “የኦሮሞ ሕዝብን ከምርጫ ለማስወጣት የተደረገ የሴራ ፖለቲካ” መሆኑን ነው ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የሽግግር መንግሥት ያስፈልጋል ያሉትን ሐሳብ አሁንም እንደሚያምኑበት እና ለኢትዮጵያ ምርጫ ሳይሆን የሽግግር መንግሥት እንደሚየስፈልግ “ከምላሴ ፀጉር ይነቀል ዶ/ር ዐቢይም በቅርቡ የሽግግር መንግሥት ያቋቁማሉ” በማለት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ስድስተኛ ተከሳሽ ማስተዋል ድርጊቱን አለመፈፀማቸውን እና ጥፋተኛ እንዳልሆኑ ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን “በኢትዮጵያ በውሸት መከሰስ ፋሽን ሆኗል፤ ስለዚህ ፍርድ ቤቱ በነጻ ያሰናብተን፤ እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ ያጠፋነው ነገር የለም” ሲሉ ችሎቱን ጠይቀዋል።

ሰባተኛ ተከሳሽ አረፋት እና ስምተኛ ተከሳሽ አማን ወንጀሉን አለመፈፀማቸውን እና ጥፋት እንዳልሠሩ ለችሎቱ ያስረዱ ሲሆን ዐሥረኛ ተከሳሽ ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ እና ዐሥራ አንደኛ ተከሳሽ የሚድያው ሥራ አስኪያጅ “የሠራሁት ሥራዬን እንጂ ወንጀል  አይደለም” ብለዋል።

ዐሥራ ሁለተኛ ተከሳሽ በበኩላቸዉ “በእኛ አገር ጋዜጠኛ ማሳደድ እና ድምፅ ማፈን የተለመደ ነው” ካሉ በኋላ እሳቸውም የአፈናው ሰለባ ሆኑ እንጂ ወንጀል እንዳልፈፀሙ ለችሎቱ አስረድተዋል።

ዐሥራ ሦስተኛ ተከሳሽ ቦና ጥፋተኛ እንዳልሆነ እና ምንም ዓይነት ወንጀል ውስጥ ተሳትፈው እንደማያውቁ ተናግረዋል። ዐሥራ አራተኛ ተከሳሽ ሃ/አለቃ ያለምወርቅ በበኩላቸው “ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ደሜን አፍስሼ፣ አጥንቴን ከስክሼ በክብር ጡረታ የወጣሁ ነኝ፤ በወንጀል የምሳተፍ ሰው አደለሁም” ብለዋል።

የጥበቃ ሠራተኞቹም በበኩላቸው ለዘጠኝ ወር መንግሥት ያለምንም ምክንያት በወጣትነታችው እንዳይሠሩ እንዳደረጋቸው ጠቅሰው ሙያቸው ጥበቃ እንጂ ፖለቲካ እንዳልሆነ፤ መንግሥት በመደባቸወ ቦታ እያገለገሉ እንደነበረ እና በጊዜው የጃዋር አጃቢዎች በመሆናቸው ብቻ ታስረው በወንጀለኛነት መጠየቃቸው ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

በመጨረሻም ተከሳሽ ቦጋለ የቀረቡባቸውን ክሶች አለመፈፀማቸውን እና ጥፋተኛ አለመሆናቸውን ለችሎቱ ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ችሎቱ የቀሩትን ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃል ለመስማት ለመጋቢት 13፤ 2013 ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል።

Center for Advancement of Rights and Democracy (CARD)

Making Democracy the Only Rule of Game!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *