ማረሚያ ቤቱ እነ እስክንድር ነጋን ፍርድ ቤት ያላቀረበበት ምክንያት በፍርድ ቤት ተቀባይነት አገኘ

ኅዳር 17፣ 2014 - በትላንትናው የችሎት ቀጠሮ ማረሚያ ቤቱ ታራሚዎችን አለማቅረቡን ተከትሎ የእነ እስክንድር ጠበቆች ደንበኞቻችን ተለይተው አለመቅረባቸው ተገቢነት የሌለው እና ደንበኞቻችን የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብቶቻቸውን የሚያጣብብ ነው ሲሉ መቃወሚያ አሰምተዋል።

አሁን ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ብንረዳም ግን  የፌዴራል ፖሊስ የፀጥታ ጉዳይ ላይ ስለሚሠራ ማረሚያ ቤቱ ትብብር መጠየቅ ይችላል ሲሉ ጠበቆች እንደመፍትሔ አቅርበዋል። በተጨማሪም ደንበኞቻችን በማናቸውም የጥበቃ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለመቅረብ እንደሚችሉ አሳውቀውናል ብለዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ አገራችን ካለችበት የፀጥታ ሁኔታ አንፃር ለተከሳሾች ደኅንነት አስቸጋሪ ስለሆነ እንዲሁም አንዳንድ አካላት የፖለቲካ ፍጆታ ሊጠቀሙባቸው ስለሚችል ነው እንጂ ፍትሕ ከማጓተት አንፃር አለመሆኑን በመገንዘብ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ፍ/ቤቱን ጠይቀዋል።

ለዛሬ በይደር የማረሚያ ቤት አስተዳደር ቀርቦ እስረኞቹን ያላቀረበበትን ምክንያት እንዲያስረዱ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት የታራሚዎች አስተዳደር ዳይሬክተር ኮማንደር አስቻለው መኮንን ቀርበው ተከሳሾችን ማቅረብ ያልተቻለበትን ምክንያት አብራርተዋል።

በዚህም ማብራሪያ የሸዋሮቢት ታራሚዎችን ወደ ዝዋይ ወስዶ እንደ አዲስ በማደራጀት ሒደት ላይ መሆናቸውን ተከትሎ ካለው የሥራ ጫና አንፃር የተወሰኑ ኃይሎች ወደ ዝዋይ በመሔዳቸው ምክንያት የሰው ኃይል እጥረት ማጋጠሙን ጠቅሰዋል። ልዩ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ታራሚዎች ተለይተው ለራሳቸው ደኅንነት ታሳቢ ተደርጎ መሆኑንም አመላክተዋል።

የተጠናከረ ጥበቃ ሳይኖር እስረኞችን ማቅረቡ ተገቢነት እንደሌለው  እና የፌደራል ፖሊስን እንደተጨማሪ እጀባ ብቻ እንጂ በኃላፊነት ወስዶ በስታንዳርዱ መሠረት ማጀብ በማረሚያ ቤቱ እንጂ በፌደራል ፖሊስ የሚከናወን ሥራ አለመሆኑን በሰጡት ምላሽ ገልጸዋል።

በማደራጀት ተግባር በዝዋይ ማረሚያ ያለው የጥበቃ ኃይል በቂ አይደለም ወይ ተብለው በፍርድ ቤቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ ኮማንደር አስቻለው አሁን እየተከናወነ በሚገኘው የማደራጀት ተግባር የዝዋይ ማረሚያ ቤት የጥበቃ አባላትና የታራሚዎች ቁጥር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ምክንያት እንደሆነም አክለዋል።

በችሎቱ እንደተገለጸው ቀለል ተደርጎ የሚታይ ጉዳይ አይደለም ያሉት ኮማንደሩ ግማሽ አባል ቤተሰቡን ትቶ ዝዋይ የሔደው ጥበቃውን ማጠናከር ስለሚያስፈልግ መሆኑንም በምላሻቸው አብራርተዋል። የእስረኞቹን መብት ለማጣበብ እንዳልሆነ የገለጹት ኮማንደር አስቻለው የፍርድ ቤቱንም ትዕዛዝ እንደሚያከብሩ እና ፍርድ ቤቱም ያሉበትን የሥራ ጫና እንዲረዳላቸው ጠይቀዋል።

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.