ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ እስክንድር ነጋ ላይ ሰጥቶት የነበረዉን ምስክሮችን የመስማት ቀጠሮ የተራዘመ ነው በማለት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ። የጥር 5፤ 2013 የፍርድ ቤት ውሎ

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት በእነ እስክንድር ነጋ ላይ ምስክሮችን ለመስማት ተሰጥቶ የነበረው ቀጠሮ ረጅም መሆኑን እንዲሁም የክሱን ውስብስብነት በመግለጽ ቀድሞ የተያዘውን ቀጠሮው ሰብሮ ጥር 5፤ 2013 ዓ.ም የተሰየመ ሲሆን በክስ መዝገቡ ስር የተዘረዘሩት ሁሉም ተከሳሾች ቀርበዋል፡፡

በዚህም መሰረት የመጀመሪያው ምስክር ጥር 26 እንደሚሰማ እና በጥር 27 ዐቃቤ ህግ የምስክሮቹን ጭብጥ አደራጅቶ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ አሳውቀዋል፡፡ በተጨማሪም የካቲት 1፣2፣3፣4፣5፣8፣9፣10፣11፣12፣15፣16፣17፣18፣19፣22፣24፣25 እና 26 ቀናት ለአንድ ምስክር አንድ ቀን በመስጠት ምስክሮች እንደሚሰሙ የተገለጸ ሲሆን አንድ ቀን ለአንድ ምስክር የተሰጠው በሂደቱ መስቀለኛ ጥያቄ ስለሚኖርና ይህም የሚፈጀው ሰዓት ስለማይታወቅ መሆኑን ችሎቱ አብራርተዋል፡፡

በመቀጠል አራቱም ተከሳሾች ተሰጥቶ የነበረው የቀጠሮ ጊዜ በማጠሩ ችሎቱን አመስግነው በተቻለ መጠን ግን ከመጭው አገራዊ ምርጫ አንጻር የፖለቲካ መብታችውን መጠቀም እንዲችሉ ቀጠሮው እንዲያጥሪላቸውና መንግስት ህጋዊ በማስመሰል እያደረገ ያለውን እነሱን ከምርጫው የማግለል አካሄድ ፍርድ ቤቱ እንዲገነዘብ ጠይቀዋል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ አቶ እስክንድር ነጋ የቀጠሮው ቀን አጥሮ ችሎት በመቅረባቸው አመስግነው ምስክሮችን የማሰማት ሂደት የአገራዊ ምርጫው ዕጩ ምዝገባ ሳይደርስ እስከ ጥር አጋማሽ ብቻ ቢሆን በማለት ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡ አቶ ስንታየሁ በበኩላቸው የግዜ ቀጠሮ ማጠሩ ለተከሳሾቹ ፍትህ ይሰጣል ማለት እንዳልሆነ ገልጸው፣ ክሱ እነሱን ከፖለትካው ለማግለል በመንግስት የተቀናበረ ስልሆነ ፍርድ ቤቱ ቀጣይ ቀጠሮ ጊዜውን በማሳጠር ለዕጩ ምዝገባ ለመድረስ ያላቸውን ፊላጎት በመረዳት ገለልተኛ ሆኖ ፍትህ እንዲሰጣቸው ተናግረዋል፡፡በተጨማሪም ተከሳሽ ወ/ሮ አስካል ደምሴ በጽሁፍ ያቀረቡት አቤቱታ እንዳለ ጠቅሰው በችሎቱ ፊት እንድነበብ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ምስክሮችን የሚያቀርበው ፍርድ ቤቱ አስቀድሞ በያዘው ቀጠሮ መሰረት እንዲሆን፤ ተከሳሾቹ በዕጩነት እንዲመዘገቡና እንዳይመዘገቡ የሚያደርገው ፍርድ ቤቱ ስላልሆነ ከነሱ ዕጩ ምዝገባ ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ እና ቀጠሮ ማጠሩ ምስክር የማሰማት ሂደቱን የሚያፋልስ መሆኑን በመጥቀስ ሂደቱ በተቻለ መጠን ከየካቲት አንድ ጀምሮ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ግራና ቀኝ ከመከረ በኃላ የተፋጠነ ፍትህ ለመስጠት ያለውን አቋም እንዲሁም ዳኞች በግላችውም ጥረት እንደሚያደርጉ አውስቷል፡፡ በአንድ ቀን አንድ ምስክር እንዲቀርብ ከሚለው ጋር ተያይዞ ሊፈጠር ስለሚችለው የጊዜ መራዘም በተመለከተ ለተነሳው አሰራሩ ተከሳሾች መስቀለኛ ጥያቄ የማቅረቢያ ጊዜ እንዳያጥርባቸው የታስቦ እንደሆነ፤ ግን ግዜ ከበቃ ፍትህ እንዳይጓደልና ሂደቱ የተፋጠነ እንዲሆን በአንድ ቀን እስከ አምስት ምስክር ለማየት እንደሚሞከር ችሎቱ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡

አቶ እስክንድር በበኩላቸው ዐቃቤ ህግ በቀን አንድ ምስክር ብቻ እንዳያቀርብ፤ በተቻለ መጠን እስከ አምስት እንዲያቀርብ እና ከጥር 26 እስከ የካቲት መጀመሪያ ምስክር ማቅረቡን እንዲጨርስ ትእዛዝ እንዲሰጥ በማለት ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም የተከሳሾች ጠበቆች የምስክሮች የስም ዝርዝር እንዳልደረሳቸው በመግለጽ ምስክርነቱ ከመሰማቱ በፊት እንዲሰጣቸው እንዲሁም የወ/ሮ አስካል አቤቱታ በችሎቱ ፊት እንዲነበብ ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡

ረዘም ካለ የዳኞች የቢሮ ውይይት በኃላ ችሎቱ የምስክሮችን ማንነት በሚመለከት ክርክር እንዲደረግ ለመድረኩ ፈቅደዋል፡፡ በዚህ መሰረት ዐቃቤ ህግ ተከሳሾች ከተከሰሱበት ወንጀል አኳያ ምስክሮች ዛቻና ማስፈራሪያ እንዳይደርስባቸውና ለደህንነታቸው ሲባል በአዋጁ በተደነገገው መሰረተ እንዲታይ በማለት ተከራክረዋል፡፡ የተከሳሾች ጠበቆች በበኩላቸው ዐቃቤ ህግ ከዚህ በፊት ያቀረበው አቤቱታ ያለመኖሩን፤ አካሄዱ ካሁን በፊት ከመጋረጃ ጀርባ የሚል ክርክር ውድቅ የተደረገበትን ውሳኔ የሚሽር መሆኑን፤ ክርክር የሚያደርጉት በአዋጅ 699 ሳይሆን በመደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሰረት እንደሆነ እንዲሁም የምስክሮች ማንነት ለማወቅ የቀረበው ጥያቄ በህጉ መሰረት ስለሆነ እና ዐቃቤ ህግ ባላቀረበው አቤቱታ ችሎቱ መጨነቅ የለበትም በማለት ተከራክረዋል፡፡ ችሎቱ ዐቃቤ ህግ ከሰጠው ፍሬ ሀሳብና ውስብስብነት አካያ ፤ ተከሳሾች ቀድመው ቢያውቁ ፍሬ ሃሳቡን ሊረዱ ይችላሉ በማለት እንዲሁም ህገ-መንግስታዊ መብታቸው እንዳይጋፋ ምስክሮች በዕለቱ ማንነታቸው እንዲታወቅ በማለት አቤቱታውን ውድቅ አድርጎታል፡፡

በአንድ ቀን የሚቀርቡ ምስክሮች ቁጥር በተመለከተ በቀን አራት ምስክሮች እንዲሰሙ ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል:: በተጨማሪም ወንጀለኛ ባልተባሉበት ሁኔታ ተከላከይ ብሎ ማስረጃ ማስቀረብ ነጻ የመሆን መብታቸውን የሚጋፋ መሆኑን በመግለጽ የወ/ሮ አስካልን አቤቱታ ችሎት ውድቅ ቢያደርግም ተከሳሿ "ወንጀለኛ ተብዬ በፍርድ ቤት ሳይወሰንብኝ የስድስት ወር ደሞዜ ተከፍሎኝ አያውቅም ስለዚህ ምክንያቱ እንዲያጣራልኝ እና ትእዛዝ እንዲሰጥልኝ" በማለት አቤቱታ አሰምተዋል::

በሌላ በከለ አቶ ስንታየሁ ደጋፊዎቻቸው ከሚለብሱት ልብስ ጋር በተገናኜ ያቀረቡት አቤቱታ እልባት ስላልተሰጠ እየተንገላቱባቸው መሆኑን በመግለጽ አቤቱታ አሰምተዋል፡፡ ችሎቱም የሚለበሰዉ በማንኛዉ አግባብ ተጽኖ ለመፍጠር ብሎም ተጨማሪ መልእክት ለማስተላለፍ መሆን እንደሌለበት ገልጾ ሌላ የውጭ ጫና ካለ ለሚመለከተው አካል ማሳሰብያ ከመስጠት ባሻገር በሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በኩል ክትትል እንዲደረግ የሚደረግ መሆኑን አስረድቷል፡፡  

በተጨማሪም ወንድ ተከሳሾች ከሴት ተከሳሾች ጋር በመገናኘት ስለክሱ እንወያይ በሚል ለቀረበው ጥያቄ ችሎቱ ይሄው ተፈጻሚ እንዲሆን ለማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ እንሰጣለን በማለት ወሰነዋል።

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.