ዐቃቤ ሕግ በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ ምስክሮችን ሳያስደምጥ ቀረ፤ ችሎቱ ምስክሮች እንዲቀርቡ ለነገ ቀጠሮ ሰጥቷል

ዐቃቤ ሕግ፤ የምስክሮቼን አድራሻ ለመቀየር ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ።

የተከላካይ ጠበቆች፤ ዐቃቤ ሕግ ጉዳዩን እያንጓተተ ስለሆነ ክሱ ይቋረጥልን።

ችሎት፤ የዐቃቤ ሕግ ምክንያት አሳማኝ ስላልሆነ ከነገ ጀምሮ ምስክሮች ይቅረቡ።

ሐምሌ 8፣ 2013፤ በዛሬው ችሎት እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሁሉም ተከሳሾች እና ከወትሮ በርከት ያሉ ደጋፊዎቻቸው በተገኙበት ተካሂዷል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የፀረ ሽብረ እና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎቱ የቀጠረው ተከሳሾች ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ምላሽ ለመስጠት እና የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለማድመጥ ቢሆንም፥ ዐቃቤ ሕግ ምስክሮቼን ‘በዛሬው ዕለት ማቅረብ አልችልም’ ሲል ያላቀረበበትን ምክንያት አቤቱታ በቃል አሰምቷል።

‘የምስክር ደኅንነትን በተመለከተ ለረዥም ግዜ አቤቱታ አቅርበን ፍርድ ቤቱም ውሳኔ የሰጠበት ጉዳይ ቢሆንም እንኳን፣ በምስክር ደኅንነት ጥበቃ አዋጁ አንቀፅ 4/1/ለ መሠረት ዐቃቤ ሕግ የምስክሮቹን ደኅንነት ለመጠበቅ የተሰጠው ሥልጣን ነው። ማለትም የምስክሮችን የመኖሪያ አድራሻ እና ማንነት መቀየር፣ ይሄን ለማድረግ ደግሞ ተቋሙ ለግዜው አቅም ስለሌለው ከሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ትብብር ጠይቀን ስለሆነ ማድረግ የምንችለው፣ ያለደኅንነት ጥበቃ ደግሞ ማቅረብ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚኖረው አጭር ቀጠሮ ይሰጠን’ ሲል ዐቃቤ ሕግ ለችሎቱ አቤቱታውን አቅርቧል።

ተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው ‘የምስክር ጥበቃ ዛሬ አይደለም የሚጀምረው፤ ደንበኞቻችን በቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ግዜ ጀምሮ ነው። ጥበቃው የሚጀምረው ዓመቱን ሙሉ ጥበቃ አድርጓል። በቃል ያቀረበው አቤቱታ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ስርዓት ሕጉ ላይ ቀጠሮ ከሚቀየርባቸው ምክንያት ጋር አብሮ የሚሔድ አይደለም። በተጨማሪም  አዋጁ መብት እስከሰጠው ድረስ በጀትም አብሮ እንደሚሰጥ ግልጽ ነው። በተጨማሪም ተጠባባቂ በጀት አለ። ስለዚህ በዚህ ግዜ የበጀት ጥያቄ ሊነሳ አይገባም። ባንወሻሽ ጥሩ ነው። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ግዴታውን (ሥራውን) ባልተወጣ ግዜ እየመጣ ፍትሕን የማጓተት ሥራ መሥራት የለበትም። ለፍትሕ ሲባል ችሎቱ መዝገቡ ተዘግቶ በነጻ ያሰናብተን ወይም ዐቃቤ ሕግ ምስክር ማሰማት በሚችልበት ግዜ መዝገቡን ማንቀሳቀስ እንዲችል ሆኖ ክሱ ይቋረጥልን’ ሲሉ ችሎቱን ጠይቀዋል።

አንደኛ ተከሳሽ እስክንድር ነጋ በተያያዘ ‘በሕወሓት ግዜ 10 ዓመት መታሰራቸውን በማስታወስ፣ ከአሁኑ እስር ጋር በድምሩ ለ11 ዓመታት ታስሪያለሁ። በዚህ ግዚያት ውስጥ ልጄን ማሳደግ አልቻልኩም፤ የሆነ ግዜ ስወጣ ልጄ ማነህ ነው ያለኝ። አሁንም በተመሳሳይ መልኩ በውሸት ክስ በዚህ መልኩ መቀጠል የለብንም። ፍርድ ቤቱንም ለዚህ መጠቀሚያ አታድርጉት። እኛ ትንሽ ብንሆንም ከበስተጀርባችን ብዙ ቤተሰቦች አሉን። ስለዚህ እባካቹ ፍትሕ ስጡን’ ሲሉ በአፅንዖት ጠይቀዋል።

ሁለተኛ ተከሳሽ ስንታየሁ ቸኮል በመጨመር ‘ይህ እኛን ለማቆየት የሚደረግ ሴራ ነው። ፍርድ ቤቱ ይህን ተገንዝቦ ክሱን ሊያቋርጠው ይገባል። ውሸት ሰልችቶናል፤ ለፍትሕ ሲባል አብረን እንታገል’ ካሉ በኋላ ‘ዐቃቤ ሕጎች እስከአሁን በውሸት ክስ ስላቆያችሁን አመሰግናለሁ’ ብለዋል።

ሦስተኛ ተከሳሽ ቀለብ ሥዩምም በበኩላቸው ‘13 ወር ሙሉ በእስር ስንቆይ የተሰጣቸው ግዜ ብዙ ነው። ስለዚህ ተጨማሪ ቀጠሮ መጠየቅ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትዕዛዝ እንደመጣስ ነው። ዐቃቤ ሕግ ከመንግሥት ጋር በመሆን የፖለቲካ አሻጥር እየሠራብን ነው’ ብለዋል።

በመጨረሻም አራተኛ ተከሳሽ አስካል ‘የፍትሕ በር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተዘግቷል፤ አልተዘጋም ካለ ችሎቱ የዐቃቤ ሕግ ክስን አቋርጦ ሊሸኘን ይገባል’ ብለዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ በስንታየሁ  ቸኮል በኩል የውሸት ክስ የሚል ቃል በተደጋጋሚ በመነሳቱ እና አላስፈላጊ ቃላት በመጠቀማቸው  ችሎቱ ቅጣት ይስጥልን ብሎ ጠይቋል።

ችሎቱም ‘በሁለቱም ወገን በኩል አላስፈላጊ ቃላቶችን የመወርወር ችግር ተገንዝበናል፤ ይታረም’ በማለት አልፎታል።

ባለፈው ችሎት የማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ ያልተፈፀመበትን ምክንያት ማረሚያ ቤቱ በጽሑፍ አቅርቦ በችሎት ተነቧል።

‘በማረሚያ ቤት መመሪያ ደንብ መሰረት ፖሊስ መድቤ የመከታተል ኃላፊነት አለብኝ’ ብሏል ደብዳቤው፤ ‘የስልክ አቤቱታን በሚመለከት በ15 ቀን ውስጥ ለ5 ደቂቃ ነው የማገናኘው’ ያለ ሲሆን ፀበልን በተመለከተ ለቀረበው አቤቱታ ግን ‘ከዚህ ቀደም አድርገን አናውቅም፤ ለማድረግም እንቸገራለን’ በማለት መልሷል። ቤተሰብ የመጠየቂያ ግዜ በሚመለከት ደግሞ ‘ቅዳሜ እና እሁድ በተጨማሪ የበዓላት ቀናቶች ብቻ ነው ጥየቃ የሚፈቀደው’ በማለት ምላሽ ሰጥቷል።

ችሎቱ ማረሚያ ቤቱ በላከው መልስ ላይ ትዕዛዝ ሰጥቶበታል። በአዋጅ 117242 አንቀጽ 40(2)መሠረት የምክንያታዊ ቁጥጥር ስርዓት ምሥጢራቸውን በጠበቀ መልኩ ነው ጥበቃ ማድረግ ያለበት ሲል የማረሚያ ቤቱን ምላሽ ውድቅ አድርጎታል። ፀበሉን በሚመለከት ሳይንሳዊ መድኃኒቶች እንደሚገቡት፣ ተገቢው ፍተሻ ተደርጎ እንዲገባላቸው እና መንግሥት ከሚሰጠው የስልክ አገልግሎት የእስክንድር ቤተሰቦች ከአገር ውጪ እንደመሆናቸው፣ ይሄ እና ያ ስለማይገናኝ፣ በግል ስልካቸው መገናኘት እንዲችሉ ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ አቤቱታ ቀጠሮ የሚያስቀይር ሆኖ አላገኘነውም በማለት፣ ከነገ ጀምሮ ተከታታይ አምስት ቀናት ምስክሮች እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.