የካርድ አዲስ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ትውልድ
#ካርድ ዓለም ዐቀፉን የሰብዓዊ መብቶች ቀን አስመልክቶ ባዘጋጀው የሰብዓዊ መብቶች ፌስቲቫል፣ በሰብዓዊ መብቶች መሠረታውያን ላይ አዲስ አበባን ጨምሮ በሰባት ከተሞች ሲያሠለጥናቸው የነበረውን 370 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አስመረቀ። እነዚህ ተመራቂዎች ሁለተኛ ዙር ሠልጣኞች ሲሆኑ፣ አምና 364 ተማሪዎችን በአዲስ አበባ አሠልጥኖ ማስመረቁ ይታወሳል።
በፌስቲቫሉ ላይ 7 በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ ሰባት አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሥራዎቻቸውን ለሠልጣኞቹ እና ለሌሎች እንግዶች አስተዋውቀዋል።
በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ በመክፈቻ ንግግራቸው በወጣቶች ላይ መሥራት ለወደፊቱ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
የባለፈው ዓመት ሠልጣኞች ከሆኑት መካከል አንዷ የሆነችው የአሚጎንያን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሰዐዳ መሐመድ በትምህርት ቤቷ ከሌሎች 12 ሠልጣኞች ጋር በመተባበር ስለመሠረተችው ክበብ ልምዷን ያካፈለች ሲሆን፣ የዚህ ዓመት የአዲስ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ትውልድ ሠልጣኞች ተግዳሮቶችን ተጋፍጠው ወደ አመራርነት እንዲመጡ መክራለች።
የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች የጋራ መሥራች እና ዋና ዳይሬክተር አምሃ መኮንን በበኩላቸው የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ እና ከሠልጣኞች የሚጠበቀውን ሚና አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ፍላጎትና ዋጋ መክፈል የሚጠይቅ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከሠልጣኞቹ መካከል በፈተና የተመረጡ ተማሪዎች እጅግ ልብ አንጠልጣይ በሆነ የሰብዓዊ መብቶች ጥያቄና መልስ ውድድር ተሳትፈው ሦስት አሸናፊዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ስለ ካርድ አዲስ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ትውልድ ፕሮጀክት የበለጠ ለማወቅ ይህንን ቡክሌት ያንብቡ።
Add a review