በእነእስክንድር ነጋ መዝገብ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች በተከታታይ ተደመጡ

የጥቅምት 10 እና የጥቅምት 15 ምስክርነቶችን ከሊንኮቹ ያንብቡ። ከጥቅምት 16 እስከ 18 በተከታታይ የቀረቡትን ምስክርነቶች ከታች ያንብቡ!

 

ጥቅምት 16, 2014 - የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት የተሰየመው ዐቃቤ ሕግ የችሎት ዘገባ በሚመለከት ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት እና የዐቃቤ ሕግ ምስክር ለመስማት ነው።

 

የዐቃቤ ሕግ ሦስተኛ ምስክር ዋና ሳጅን ያየህ ብርሃኑ ግዛው በአንደኛ ተከሳሽ ላይ ምስክርነት ሰጥተዋል። በ26/05/2012 ወረዳ 4 መንግሥት ፍቃድ ሳይሰጥ የቤተክርስቲያን ግንባታ በመጀመሩ ግንባታውን ለማስቆም ከሌሎች የፖሊስ አባላት ጋር በቦታው ተገኝተው እንደነበር፤ በወቅቱም ይህን ተቃውመው የአካባቢው ወጣት  የፖሊስ አባላቶች ላይ ድንጋይ በመወርወር እና አንድ የፖሊስ መኪና በማቃጠል ቤተክርስቲያኗ መገንባት አለባት፣ ይህን ለመቃወም የወጡ ልጆች ለምን ተገደሉ?  የሚል ተቃውሞ እያሰሙ እንደነበር ገልጿል። ይህን ተከትሎ እስክንድር ነጋ በ27/05/2014 ጠዋት በግምት 4:30 አካባቢ በV8 መኪና መጥተው ተረጋግቶ የነበረውን ወጣት "እኛ እያለን አዲስ አበባን ማንም አይደፍራትም" በማለት ወጣቱን ሰብስበው ይሄ ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ ነው ማለቅ ያለበት፣ ኃይል መጠቀም አያስፈልግም፤ ልጆቹን የገደለው የኦሮሚያ ፖሊስ ነው፣ ብሎ አናግረዋቸው እንደሔዱ እና ተረጋግቶ የነበረው ወጣት ከ30 ደቂቃ በኋላ እንደገና ጥያቄውን ጀምሮ እንደነበር እና ከንቲባዋ አዳነች አበቤ መጥተው “ጥያቄዎቻችሁን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ትችላላችሁ” ብለው አረጋግተው መሔዳቸውን አክለው አስረድተዋል።

 

ምስክሩ የሞቱት ሁለት ወጣቶች በኦሮሚያ ፖሊስ ተገድለው እንዳልነበር ነገር ግን በቦታው በነበሩት የአዲስ አበባ  እና የፌደራል ፖሊስ በተተኮሰ ጥይት መሆኑን እና ድጋሚ ተነስቶ የነበረውን ረብሻ እስክንድር ነጋ በመጡበት ወቅት የወጣቱን ሐሳብ ደግፈው በመሔዳቸው  እንጂ እስክንድርን አስነስተው መሔዳቸውን የሚያውቁት ነገር እንደሌለ፣ እሳቸው በነበሩበት ሰዓታትም ምንም ረብሻ እንዳልነበር፣ በመስቀለኛ ጥያቄ ወቅት ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

 

የዐቃቤ ሕግ አራተኛ ምስክር ቴዎድሮስ ለማ ተሾመ በአንደኛ ተከሳሽ እስክንድር ነጋ እና በሁለተኛ ተከሳሽ ስንታየሁ ቸኮል ላይ ምስክርነት ሰጥተዋል። ሰኔ 23፣ 2012 አያት ፀበል ኮንዶሚኒየም በሀጫሉ ሞት ተከትሎ ከነበረው ግርግር ከግቢው ኮሚቴ  አካባቢያችሁን ጠብቁ ስለተባልን ዱላ ይዘን በየብሎኮቻችን በምንጠብቅበት ወቅት፣ እስክንድር ነጋ እና ስንታየሁ ቸኮል በቪትስ መኪና መጥተው በአጥር በኩል ቄሮ ቤተ ክርስቲያናችሁን ሊያቃጥል ነው፣ ወጥታችሁ ጠብቁ ብሎ ነግረውን ሄደዋል። በዛ መሠረትም ቤተክርስቲያን ሔደን ጠብቀናል፤ ሆኖም ግን ምንም ዓይነት ችግር እንዳልነበር ቄሮም እንዳልመጣ ለችሎቱ ገልጸዋል። ምስክሩ መስቀለኛ ጥያቄ ሲቀርብላቸው እስክንድር ነጋ በቲቪ ብቻ እንደሚያቃቸው ስንታየሁን ደሞ ለፖሊስ ቃል በሚሰጡበት ወቅት በፎቶ እንደለየ፣ ሥማቸውንም ከፖሊስ እንደሰማ፣ በግርግሩ ግዜ ግን የማያቃቸው ሰዎች በሰጡት ቃል እምነት አሳድሮ ቤተክርስቲያን ለመጠበቅ የሔደው የእምነቱ ተከታይ ስለሆነ እና በወቅቱ ከነበረው ረብሻ አንፃር መሆኑን ተናግረዋል።

 

አምስተኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ደረጀ ግዛው (አቡሼ) በአንደኛ ተከሳሽ እስክንድር ነጋ ላይ ምስክር ሆነዋል። ሰኔ 24፣ 2014 ወሰን በሚካኤል በኩል ጩኸት በመስማታቸው  ከቤት እንደወጡ፣ በወጡበት ወቅት ደሞ ወጣቶች ይሄ ተረኛ መንግሥት አይገዛንም እያሉ እየጮሁ የግለሰብ ሱቆችን በድንጋይ በመሰባበር አንድ የቤት መኪና፣ አይሱዙ መኪና እና ጎማዎች በማቃጠል መንገድ ይዘጉ እንደነበር፣ ይህን ድርጊት ሲያስፈፅሙ የነበሩ ግለሰቦች ደግሞ ኢንጂነር ስዩም እና ሳጅን ብርሃኑ የሚባሉ እንደነበር ገልጸዋል።

 

ከቤቱ በድንጋጤ በሚወጣበት ወቅት ኢንጂነር ስዩም እና ሳጅን ብርሃኑን እንዳገኛቸው ምንድነው ብሎ ሲጠይቃቸው በቂ መሳሪያ እና ኃይል እንዳላቸው እና ይህ ተረኛ መንግሥት አይመራንም፣ ጠንካራ ወጣት እንፈልጋለን፣ ተዘጋጭተህ ጠብቀን እንዳሉት፤ እነዚህ ሁለቱ ግለሰቦች በዕለቱ 10:00 ሰዓት አካባቢ እስክንድር በቪትዝ መኪና መጥተው በምልክት አናግረዋቸው እንደሔዱ፣ በተጨማሪም በፖሊስ መነጋገሪያ ስልክ ከእስክንድር ጋር እየተደዋወሉ እንደነበር፣ ነገር ግን የመነጋገሪያ ስልኩን በእስክንድር እጅ ላይ አለማየታቸውን ጨምረው ገልጸዋል። በተጨማሪም እስክንድር በመጡበት ወቅት ምንም ንብረት እንዳልወደመ እና የወደሙት በሙሉ እርሳቸው ከመምጣታቸው በፊት መሆኑን በመግለጽ፣ ነገር ግን ከፖሊሶቹ ጋር በምልክት ሲያወሩ ስለነበር አንድ ላይ ናቸው የሚል ግምት እንደነበረው ለችሎቱ ምስክርነት ሰጥቷል። በተያያዘም፣ እስክንድር ነጋ ሰኔ 24 ከቀኑ 10:00 ሰዓት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ለችሎቱ አስረድቷል።

 

ከሰዓት በኋላም ቀጥሎ የነበረው ችሎት ሰዓት በመምሸቱ ቀሪ ምስክር ለመስማት በይደር እንዲያድር  እና ጌጥዬ ያለው እና የባልደራስ ፓርቲ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ የችሎቱን ሒደት በሚመለከት በለጠፉት ጽሑፍ ላይ ዐቃቤ ሕግ ላቀረባቸው አቤቱታ ጥቅምት 18 ምላሽ እንዲሰጡ አዟል።

 

ጥቅምት 17፣ 2014 - ስድስተኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ወርቁ ታደሰ ቶላ በአንደኛ እና በሁለተኛ ተከሳሽ ላይ ምስክር ቃላቸውን ሰጥተዋል። በተጨማሪም አራቱንም ተከሳሾች እንደሚያቋቸው ለችሎቱ ተናግረዋል።

 

ምስክሩ ከእስክንድር ነጋ ጋር በቃሊቲ እስር ቤት ባሉ ግዜ እንደተዋወቁ፣ ከተፈቱ በኋላ ደግሞ በ2011 ባጋጣሚ በድጋሚ እንደተገናኙ እና ስክል እንደተለዋወጡ፤ የታከለ ዑማ ሹመት በሚመለከት በግሉም ይቃወም እንደነበር፣ እነ እስክንድርም ሐሳባቸው ይኸው ስለነበር እነሱን ደግፎ አድዋ ድልድይ ባልደራስ አዳራሽ አካባቢ ተሰብስበው እስክንድርን ፕሬዝደንት አድርገው መሾማቸውን  ገልጸዋል። ከዛ በኋላ እስክንድር አሜሪካ ባለበት ወቅት ደሞ በስንታየሁ መሪነት በተለያዩ ግዜ ስብሰባ ያደርጉ እንደነበር፣ እስክንድርም ከተመለሰ በኋላ ባልደራስ ፓርቲን መሥርተው የታከለ ዑማ ሹመት ሕገ ወጥ ነው ብለው ስላመኑ፣ ማንኛውንም ኃይል ተጠቅመው፣  ረብሻና አመፅ በሐዝብ መሐል በመቀስቀስ ሥልጣን መያዝን ዓላማቸው አድርገው ባልደራስን መመሥረታቸውን አንድ ቀን ሙሉ በፈጀ ገለጻ ለችሎቱ አስረድተዋል።

 

ጥቅምት 18፣ 2014 - ከጥቅምት 17 በቀጠለው የምስክሩ ቃል ይህንን ዓላማቸውን ለማሳካት የተገኙትን አጋጣሚዎች በመጠቀም፣ በተለያዩ የፌስቡክ ገጾች ላይ ብሔርን ከብሔር የሚያጋጭ፣ የሃይማኖት ተቋማት በመንግሥት ላይ እንዲነሱ የሚያደረጉ ጽሑፎችን በመለጠፍ፣ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራን በመጠቀም፣ የምርጫ መራዘምን በመጠቀም፣ የሀጫሉን ሞት በመጠቀም እንደነበር አስረድተዋል።

 

ይህን ተከትሎ ሕዝቡ ሲቆጣ መንግሥት ላይ ይነሳል። ከዛ በቀላሉ ሥልጣን ለማግኘት እና የኦርቶዶክስ ተቋም ድጋፍ ለማግኘት ያስችለናል ብለው ማሰባቸውን ምስክሩ ገልጸዋል። ይህን ዓላማ ይዘው በተለምዶ ስልጤ አካባቢ ተብሎ በሚጠራው ቦታ የተፈናቀሉ ሰዎችን ሔደው መንግሥት እናንተን አፈናቅሎ፣ ከሶማሌ የተፈናቀሉ ኦሮሞዎችን ሊያሰፍር ስለሆነ እኛን ምረጡ፣ መሬት እንሰጣችኋለን ብለን ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ቅራኔ እንዲፈጠር አድርገናል ብሏል።

 

ምስክሩ ቀጥለውም የሀጫሉን ለቅሶ ለመድረስ የሚመጡትን ቄሮዎች ቀጥቅጦ ለመመለስ 1500 ብር ተሰጥቶኝ፣ ልጆች አደራጅቼ ለሁለት ልጆች የካርድ 500 ብር ለያንዳንዳቸው ሰጥቻለሁ ብለዋል። ይህንን ተከትሎም አንድ ሀይገር፣ ሁለት ኮሮላ እና አንድ ባጃጅ ተቃጥሏል። ሁለት ሰዎች መሞታቸውንም ሰምቻለሁ ብሏል። በአደጋ ግዜ እንዲሁም አገር ስትወረር የሚደወለውን የቤተክርስቲያን ደውል አስደውለናል። ይሄን ሁሉ ትዕዛዝ የሚሰጡንም እስክንድር ነበሩ በማለት አክሏል።

 

ፍርድ ቤቱ ጠዋትና ከሰዓት በዋለው ችሎት የምስክር ቃል ባለማለቁ በይደር እንዲያድር ትዕዛዝ ሰጥቷል። በተጨማሪም የሁለተኛ ተከሳሽ ስንታየሁ ቸኮል የሕክምና ጥያቄ በግላቸው በላንድማርክ ሆስፒታል እንዲታከሙ ትዕዛዝ ተሰጥቶበታል።

 

ጥቅምት 19፣ 2014 - ምስክሩ በዚህ ዕለት ዋና ጥያቄ ላይ ያብራሩትን ሐሳብ በመስቀለኛ ጥያቄ በድጋሚ በሰፊው አብራርተዋል።  ከእስክንድር ነጋ በተሰጣቸው ትዕዛዝ የፌስቡክ ወሬ ያመጣው ነገር ለፓርቲው ግብዓት ከመሆን ውጪ በተግባር ምንም ጥቅም  እንዳላገኙ፣ እንዲሁም የፕሮቴስታንት አማኝ ሆነው የቤተክርስቲያን ደውል መደወል አገር ስትወረር መሆኑን ያወቁት በጓደኛቸው አማካኝነት መሆኑን፣ በመስቀለኛ ጥያቄ ምላሽ ሰተዋል።

 

መስቀለኛው ጥያቄ ባለማለቁ በዚሁ ምስክር ለአራተኛ ቀን ጥቅምት 23 ቀጠሮ ተሰቷል።

 

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ አቤቱታ ላይ ተመሥርቶ ጌጥዬ ያለው ችሎት ሒደቱ ላይ በጻፉት ጽሑፋቸው ምክንያት ችሎት በመድፈር ጥፋተኛ ናቸው ብሎ ለፍርድ እስከ ጥቅምት 22 በእስር ቤት እንዲቆዩ ሲል ወስኗል።

 

የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው የቅጣት ማቅለያ ለችሎቱ አቅርበዋል። ተከሳሹ የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናቸው እና የሚዲያ አዋጅ ሕጉ ዘገባ ወቅት በሚፈጠር ስህተት ቅጣቱ በገንዘብ ብቻ እንዲሆን የሚደነግግ በመሆኑ፣ እንዲሁም የችሎት አዘጋገብን በሚመለከት የወጣ ሕግ ባለመኖሩ፣ ችሎቱ ከዚህ አኳያ እንዲመለከተው ጠይቀዋል። በተጨመሪም የተከሳሽ ዘገባ የከፋ ጉዳት የማያደርስ በመሆኑ እና የተለየ ጥቅም ለማግኘት የተደረገ ባለመሆኑ ይህም ከግምት እንዲገባ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል። በቀረበው የቅጣት ማቅለያ መሰረት ብይን ለመስጠት ፍርድ ቤቱ የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 22 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

 

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.