ካርድ ዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ቀንን በደማቅ ክብረ በዓል በማስታወስ ዋለ
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ - እሁድ፣ ሕዳር 30፣ 2016 የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ደማቅ የሰብዓዊ መብቶች ክብረ በዓል በአዲስ አበባ ካፒታል ሆቴል አከናውኗል። ከሽቲፍቱንግ ሜንሽንረሽተ፣ ከጀርመን ኤምባሲ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ህብረት (ኢሰመድህ) ጋር በተዘጋጀው በዚህ የሰብዓዊ መብቶች ክብረ በዓል ላይ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች እና መጪዎቹየሰብዓዊ መብቶችተሟጋቾች ትውልድ መካከል የትስስር መድረክ ተፈጥሯል።
በኢትዮጵያ የጀርመን ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሽቴፋን ኧር በቁልፍ መልዕክታቸው የሰብዓዊ መብቶችን ሁኔታ ማሻሻል አገራዊ መረጋጋትን እና ብልፅግናን ለማምጣት ወሳኝ ቅድመ ሁኔታዎች መሆናቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም አምባሳደሩ በክብረ በዓሉ ላይ ለሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾቹ እንደተናገሩት “ጀርመን ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጎን በፅናት ትቆማለች”። የካርድ ዋና ዳይሬክተር በፍቃዱ ኃይሉም ባደረጉት የአቀባበል ንግግር መጪዎቹ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ትውልድ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታ አሁን ካሉት እና የቀደሙት ትውልዶች ከሞከሩት በተሻለ ሁኔታ እንደሚያንቀሳቅሱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ከሽቲፍቱንግ ሜንሽንረሽተ (የሰብዓዊ መብቶች ፋውንዴሽን) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በካርድ አማካይነት መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሥልጠና የወሰዱ 191 የአዲስ አበባ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች “አዲስ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ትውልድ” ተብለው ተሰይመዋል። እነዚህ ወጣት መሪዎች በማኅበረሰባቸው ውስጥ የሰብዓዊ መብቶችን እሴቶችን በማስተዋወቅ እና ለሰብዓዊ መብቶች እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሕዝባዊ መሠረት በመሆን ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።በሥልጠናው የተሳተፈችው የፋውንቴን ኦፍ ኖውሌጅ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪዋ ዮስቲና ሰለሞን ከሥልጠናው በኋላ በትምህርት ቤቷ የስርዓተ ፆታ እኩልነት እና የሰብአዊ መብቶች ክበብ በመምህራኖቿ ድጋፍ አቋቁማለች። ክለቡ አሁን ከ30 በላይ አባላትን ማፍራቱን ለታዳሚዎቹ ተናግራለች።
በዘጠኝ ዙር በተደረገው ሥልጠና ድኅረ ምዘና ወቅት ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ዘጠኝ ተማሪዎች ደማቅ የሰብዓዊ መብቶችጥያቄና መልስ ውድድር ላይ በመሳተፍ ዕውቀታቸውን እና ለሰብዓዊ መብቶች ያላቸውንፍቅር አሳይተዋል።በሦስት ዙር በተካሔደው የሰብዓዊ መብቶች ጥያቄና መልስ ውድድር ባምላክ ማተቤ ከሬኔሳንስ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት የ12ተኛ ክፍል ተማሪ፣ ሳሮን ተዘራ ከካቴድራል ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ፣ እና ሊዲያ ጌታሁን የኢትዮ ዌልስ ግሎባል አካዳሚ የ9ኛ ክፍል ተማሪ፣ ከአንድ እስከ ሦስተኛ በመውጣት የላፕቶፕ፣ ታብሌት እና ስልክ ተሸላሚ ሆነዋል።
ከዚህ ትይዩ በተካሔደው የመድረክ ውይይት፣ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች በወቅታዊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ሥራ ላይ ያሉ ተግዳሮቶች እና መውጫ መንገዶች ላይ ሐሳባቸውን አቅርበዋል። ተወያዮቹ ያሬድ ኃይለማርያም (የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር)፣ ስኂን ተፈራ (የሴታዊት ፌሚኒስት ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር)፣ ሜሮን ተስፋዬ (የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች ተወካይ) ናቸው። በውይይት መድረኩ ላይ አቶ ያሬድ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ከሚገጥሟቸው ፈተናዎች መካከል የዘፈቀደ እስራት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። እ.ኤ.አ. በ2023 ብቻ ከ50 በላይ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች በኢትዮጵያ ውስጥ ታስረው እንደነበርም አክለው ገልጸዋል። በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት እና የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች አባላት በጉዳዩ ላይ ጥያቄዎችን በማንሳት እና አስተያየቶችን በመስጠት ንቁ ተሳትፎ አድርገዋል።
ከውይይቶቹ ባሻገር ስምንት የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች፣ ማለትም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ )፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር፣ ሴታዌት ንቅናቄ፣ ስብስብ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች፣ CEHRO እና ካርድ፣ ከክብረ በዓሉ ጎን ለጎን በተሰናዳው ዐውደ ርዕይ ላይ በመሳተፍ ሥራዎቻቸውን ለማሳየት እና ከክብረ በዓሉ ተሳታፊዎች ጋር ለመገናኘት ችለዋል። ዐውደ ርዕዩ የእርስ በርስ ትብብርን ከማጎልበቱም ባሻገር በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶችተሟጋቾችን ትስስር ያጠናክራል። ከኤግዚቢሽኑ ተሳታፊዎች መካከል የተሟጋቾች ማዕከሉ በ12 ዩኒቨርሲቲዎች እንዲቋቋም የረዳቸውን የሰብዓዊ መብቶች ክለቦች አስተዋውቋል፤ ይህም የሥልጠናው ተጠቃሚ የሆኑት ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ መጀመሪያ የሚስተናገዱበትን ከመደበኛ ትምህርት ተጓዳኝ ያለ ክበብ ያሳውቃቸዋል።
የሰብዓዊ መብቶች ክብረ በዓሉ ስኬቶችን ለማክበር፣ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እና የወደፊቷን የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾችን በኢትዮጵያ ለማብቃት እንደ ሁነኛመድረክ ሆኖ አገልግሏል። ክብረ በዓሉ ካርድ ለሁሉም ፍትሐዊ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ባሕል እና ስርዓት ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነትም አሳይቷል።
በክብረ በዓሉ መዝጊያ ላይ የካርድ ፕሮግራም ዳይሬክተር አጥናፉ ብርሃኔ፣ አዲስ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ትውልድ አባላቱ "ለሰብዓዊ መብቶች በጋራ እንቆማለን" የሚለውን ቃለ መሐላቸውን ተቀብለዋቸዋል።
የዘንድሮው የሰብዓዊ መብቶች ክብረ በዓል በተከታታይ ከተደረጉት ክብረ በዓሎች ሦስተኛው ሲሆን፥ ካርድ እስካሁን ተመሳሳይ ሥልጠና የሰጣቸው እና አዲስ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ትውልድ ብሎ የሰየማቸው ተማሪዎች ቁጥር በአጠቃላይ 925 አድርሶታል። ክብረ በዓሉን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ፣ አርትስ ቴሌቪዥን እና አዲስ አበባ ሚዲያ ኔትወርክን ጨምሮ በርካታ ሚዲያዎች ለክብረ በዓሉ የሚዲያ ሽፋን ሰጥተውታል።
Comments (0)
Add new comment