Skip to main content

የካርድ የመጀመሪያ አውራምባ ጠቋሚ 2015 ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፣ ታኅሣሥ 17፣ 2016 – የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) በዓይነቱ የመጀመሪያው የሆነውን አውራምባ ጠቋሚ 2015 ይፋ አደረገ። ይህ የኢትዮጵያ የፌዴሬሽን አባላትን የዴሞክራሲያዊነት ሒደት የሚመዘንበት አውራምባ ጠቋሚ የተባለ ሪፖርት ኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብቶች እሴቶች ላይ ያበበ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን በእውቀት እንድታደርግ ያግዛል ተብሎ በማዕከሉ ተስፋ ተጥሎበታል። 

አውራምባ ጠቋሚ ሥያሜውን ያገኘው በ1970ዎቹ በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ ከተመሰረተው እና ከ400 በላይ ነዋሪዎች ካፈራው የአውራምባ ማኅበረሰብ ነው። አውራምባ አመራሩ በፈቃዳቸው በተሰባሰቡ ሰዎች ፍላጎት ሆነ ተብሎ የተቀረፀ በመሆኑ ጠቋሚው ለሚያራምደው ዴሞክራሲያዊነትን በብዙኃን ይሁንታ የመገንባት ሒደት ምሣሌ ይሆናል ተብሎ ታምኗል። አውራምባ ጠቋሚ በ2015 የዴሞክራሲያዊነት ሒደቱ አዎንታዊ  ማሻሻያ ማሳየት አለማሳየቱን መመዘን ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የአምስት ክልላዊ መስተዳድሮችን እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማን ዓመታዊ የዴሞክራሲያዊነት ሒደት ገምግሟል። ምዘናው አስቀድሞ የተወሰነ ጥናታዊ ሥነ ዘዴን በመጠቀም የፖለቲካ ብዝኃነት፣ የኅዳጣን ጥበቃ፣ የዜጎች ነጻነት እና የመሳሰሉትን የዴሞክራሲያዊነት ባሕሪዎች መሠረት አድርጎ መስተዳድሮቹን በ25 መገለጫዎች መዝኗቸዋል። 

"አውራምባ ጠቋሚ በኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማምጣት ወሳኝ ሚና ይጫወታል" ይላሉ የካርድ ዋና ዳይሬክተር በፍቃዱ ኃይሉ። "ተጨባጭ እና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ክትትል፣ ስነዳ እና እወጃ በማድረግ የፌዴሬሽኑ አባላት ከራሳቸውም ሆነ ከሌሎች የፌዴሬሽኑ አባላት ጋር በዴሞክራሲያዊነት ሒደት እንዲወዳደሩ እንደሚረዳቸው ተስፋ እናደርጋለን።"

የአውራምባ ጠቋሚ በወሳኝ ወቅት የተጀመረ ነው። ለዓመታት የዘለቀው የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ሕጋዊ ማሻሻያዎች ኢትዮጵያ አሁን ወደ ተሻለ አሳታፊ እና ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ትሸጋገር ዘንድ መረጃ ላይ የተደገፈ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ። አውራምባ ጠቋሚ ለፖሊሲ አውጪዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና መላው ሕዝቦች የዴሞክራሲያዊነት ሒደትን ለመከታተል፣ ተግዳሮቶችን ለመለየት እና ለተሻለ ሽግግር በጋራ ለመሥራት ጠቃሚ ግብዓት ይሰጣል።

የአውራምባ ጠቋሚ 2015 ታኅሣሥ 17 ቀን 2016፣ በይፋ ይታወጃል። ጠቋሚው በሶፍት ኮፒ እና በኅትመት ለሚመለከታቸው አካላት ይደርሳል። በተጨማሪም የጠቋሚው ግኝቶችን መሠረት ያደረገ የምክክር መድረክ ይሰናዳል። 

Share this post

Comments (0)

Add new comment

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.