Skip to main content

የኢፌዴሪ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በድርጅታችን የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ላይ በድጋሚ የጣለውን እግድ አስመልክቶ የተሰጠ አጭር መግለጫ

ታኅሣስ 16 ቀን 2017

ድርጅታችን የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን፣ በመዝገብ ቁጥር 4307 ሐምሌ 17፣ 2011 የምዝገባ ሰርተፊኬት ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ፣ ቦርድ መር የአገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል።

የኢፌዴሪ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ታኅሣስ 07 ቀን 2017 በጻፈው ደብዳቤ ድርጅታችን የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) በድጋሚ መታገዱን ገልጾልናል።  እንደሚታወቀው ደርጅታችን ቀድሞ ተጥሎበት የነበረው እግድ እንዲነሳ  በርካታ ጥረቶችን ያደረገና ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጋርም  የተወያየ ሲሆን ይህም ውጤት አስገኝቶ ታኅሣስ 02 ቀን 2017 እግዱ መነሣቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ተጽፎልን ነበር። በወቅቱም የእግዱን መነሳት መቀበላችንን ገልፀን የተሰጡንን ማስጠንቀቂያዎች በተመለከተ ግን ከባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ጋር በመነጋገር ለመፍታት እንደምንጥር በመጥቀስ መግለጫ ማውጣታችን ይታወሳል።

ይሁን እንጂ የመጀመሪያው እግድ በተነሣ በሦስት (3) የሥራ ቀናት ውስጥ የድጋሚ እግድ መጣሉን የሚገልጽ ደብዳቤ ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ደርሶናል። ባለሥልጣኑ በደብዳቤው “ድርጅታችን ማስጠንቀቂያው ከደረሰው በኋላ አሠራሩን ባለማስተካከሉ እና ለባለሥልጣኑ ሕግ እና ውሳኔ ተገዥ ባለመሆኑ”  ዳግም እንደታገደ ገልጿል።  ይህ ዳግም እገዳ ካርድ በመጀመሪያው እግድ ሳቢያ ያቋረጠውን ሥራ እንዳችም ሳይጀመር የመጣ ከመሆኑ አንጻር ያልጠበቅነውና መጀመሪያ የተፈጠሩትን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታትም በድርጅታችን እና በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የወደፊት የሥራ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠርም ሆነ ችግርም ካለ እርምት ለማድረግ ጊዜ እና ዕድል ያልሰጠ በመሆኑ ድርጅታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል። ድርጅታችን ሕገ መንግሥቱን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅን እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ሕጎች እና መመሪያዎችን ተከትሎ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ቢሆንም ያለምንም ተጨባጭ ጥፋት ለተደጋጋሚ ጫና እየተዳረገ መሆኑ እጅጉን ያሳስበናል።

በሌላ በኩል እግዱን አስከትሎ ድርጅታችን ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በጽሑፍ ማብራሪያ እንዲሰጠን ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን በሕጉ መሠረት ለባለሥልጣኑ ቦርድ ይግባኝ ለማቅረብ ዝግጅቱን አጠናቋል። በመሆኑም ድርጅታችን የድጋሚ ዕግዱን ለማስነሣት የሚያደርጋቸውን ሕጋዊ ጥረቶች አጠናክሮ የሚቀጥልና የሚደርስበትንም ውጤት በየጊዜው ይፋ የሚያደርግ መሆኑን ለማሳወቅ ይወዳል።

 

የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)

 

Share this post

Comments (0)

Add new comment

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.