ከየመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማእከል (ካርድ) የተሰጠ አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ
ከየመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማእከል (ካርድ) የተሰጠ አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ
ታኅሣስ 1 ቀን 2017
የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የሥራ ዕግድ እንደደረሰው ካሳወቀበት ከኅዳር 13 ቀን 2017 ወዲህ ስላሉ አጠቃላይ ሁኔታዎችን እና ችግሩን ለመፍታት ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጋር ያደረጋቸው ጥረቶችን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃን ለመስጠት ይህ መግለጫ ተዘጋጅቷል።
ስለ እገዳው
ዕለተ ሐሙስ ኅዳር 5 ቀን 2017 የካርድን ከማናቸውም ሥራ መታገዱን የሚገልጽ ደብዳቤ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ደረሰው። የደብዳቤው ይዘትም ድርጅታችን “ከፖለቲካ ገለልተኛ አለመሆኑን” እና “የሀገርን ጥቅም በሚጎዱ ተግባራት ላይ መሠማራቱን” የሚገልጽ ውንጀላ ያለበት ነው። ካርድ እነዚህን ውንጀላዎች መሠረተ ቢስ እና ፈጽሞ የማይቀበላቸው መሆኑን በድጋሚ ለማረጋገጥ ይወዳል። ይልቁንም ድርጅታችን በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እና ሌሎች ሕጎች የተቀመጡትን ሕጋዊ የመደራጀት እና ሐሳብን በነጻነት የማራመድ፣ የሰብዓዊ መብቶችን መከበር እና መጠበቅ የሚያሳልጡ እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርአት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያበረክቱ ፕሮግራሞች እና ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ እንዲሁም እንደ ሀገራዊ ምክክር ያሉ ተግባራት እና ተነሳሽነቶች የተሻለ ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖራቸው ለማድረግ አመርቂ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱ ይታወቃል።
ከዚህ በፊት ለመግለጽ እንደሞከርነው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የካርድን ዕገዳ የወሰነበት አግባብ ሕጋዊነት እና ግልጽነት የጎደለው ነው ብለን በጽኑ እናምናለን። ለማሳያነትም በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ እና የባለሠልጣኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ክትትል፣ ድጋፍ እና ግምገማ መመሪያ በግልጽ ያስቀመጧቸውን አሠራሮች ማለትም ስለተፈጠረው ችግር አስቀድሞ ማሳወቅና ማብራሪያ መጠየቅን፣ ማስጠንቀቂያ መስጠትን፣ በአዋጁና በመመሪያው በተደገገው መሠረት ድርጅቱ ላይ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ማሳወቅ እና የምርመራው አካል ማድረግ እንዲሁም ከዕገዳ በፊት ምርመራ ማካሄድን ወደጎን በመተው ድርጅቱን በዘፈቀደ አግዷል። በተጨማሪም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከላይ የተጠቀሱት አዋጅ እና መመሪያ በግልጽ ያስቀምጧቸውን የምርመራ ሂደት ጥንቃቄዎችን ማለትም የድርጅቱን ሕልውና አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ መካሄድ እንደሚኖርበት፣ የሠራተኛ ደሞዝን ጨምሮ የድርጅቱን ሕልውና ለመጠበቅ የሚረዱ አስተዳደተራዊ ወጪዎችን መፍቀድን ችላ በማለት ያለምንም የሕግ ጥሰት ማረጋገጫ እና ምክንያታዊ ጥርጣሬ ባንክ አካውንቱን በመዝጋት ድርጅታችንን ላልተፈለገ ጫና አጋልጦታል። የውሳኔው ሕጋዊነት እና ግልጽነት ጉድለት እና ከውሳኔው በኋላ በምርመራ ወቅት የድርጅቱ ሕልውና አደጋ ላይ እንዳይወድቅ በሕግ የተደነገጉ አሠራሮች ወደጎን መባላቸው እንዲሁም ለክፍተኛ ጫና መዳረጉን በጽሑፍ ጭምር ብናሳውቅም በሚመለከተው አካል ችላ መባላቸው ድርጅቱን የማገድ ውሳኔም ሆነ ተከትለው የመጡ ጫናዎች ካርድን እና ሥራውን የፖለቲካ ጥቃት ዕላማ ለማድረግ ታስበው የተሠሩ ሥራዎች ናቸው ብለን እንድናምን ያስገድዱናል።
ችግሩን በውይይት ለመፍታት ያደረግናቸውን ተደጋጋሚ ጥረቶች ተከትሎ የባለሥልጣኑ የክትትልና ምርመራ ቡድን አባላት ኅዳር 12 እና 18 ቀን 2017 ወደካርድ ቢሮ በመምጣት ለምርመራ ዓላማ መምጣታቸውን በቃል ካስረዱን በኋላ አሁን በመተግበር ላይ ያሉ ፕሮጀክቶንን፣ የፈንድ ምንጮቻችንና አጠቃላይ የአሠራር ሒደቶቻችንን በመጠየቅ ገምግመዋል። ከሁለቱም ቡድኖች ጋር ሰፊ ውይይት ካደረግን በኋላ በኛ በኩል የተሰነዘረብንን ውንጀላ የሚያረጋግጥ ምንም ነገር እንዳላገኙ የሚያመለክቱ ሁኔታዎች መኖራቸውን ለመረዳት ችለናል።
ችግሩን ለመፍታት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጋርእያደረግናቸው ስላሉ ጥረቶች
ከእገዳው ደብዳቤ በኋላ ኅዳር 16 ቀን 2017 የካርድ የሥራ ኃላፊዎች ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተገናኝተው ውይይት አከናውነዋል። በዚህ ጊዜም ካርድ ተወካዮች ድርጅቱ ውንጀላውን ፍጽሞ እንደማይቀበለው፣ ውሳኔው ሕጋዊነት እና ግልጽነት የጎደለው መሆኑን እንዲሁም የዘፈቀደ ዕገዳው በአፋጣኝ እንዲነሣ ጥያቄ አቅርበዋል፣ ጥያቄያቸውንም በደብዳቤ አስገብተዋል። በወቅቱም የውሳኔው አንዳንድ አሠራሮች ክፍቶትች እንዳሉባቸው የባለሥልጣኑ ከፍተኛ አመራሮች አምነው የነበረ ሲሆን ለዐብነትም የድርጅቱን የባንክ አካውንት በምርመራ ጊዜ በሕግ ለተፈቀዱ ውጪዎች ክፍት እንደሚደረግ እናይህም ውሳኔ በሦስት ቀናት ውስጥ እንደሚተገበር ተነግሮን ነበር። ነገር ግን ከሦስት ሳምንታት በኋላ ይኼ ውሳኔ አልተፈጸመም። ይኼም በካርድ እና በሲቪል ማኅበረሰብ ምህዳሩ ላይ የተቃጣ የፓለቲካ ውሳኔ ነው የሚለው እምነታችንን የሚያጠናክር ሆኖ አግኝተዋል።
የወደፊት አቅጣጫ
ካርድ ከታገደ አንድ ወር ሊሞላው ሲሆን ችግሩን በዉይይት እና በንግግር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋችን ላይ ፈጽመን ተስፋ ባንቆርጥም የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ውሳኔ አሰጣጥ፣ የምርመራ ውጤት መዘግየት፣ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ለመስጠት መዘግየት የተነሣ ማከናወን የሚገቡንን መሠረታዊ ክፍያዎች ለመፈጸም ባለመቻላችን የድርጅታችን ሕልውና ከፍተኛ አደጋ ላይ መሆኑ እጅግ ያሳስበናል።
ስለዚህም ችግሩን በውይይት ለመፍታት ያለሰለሰ ጥረት ከማድረግ ጎን ለጎን ይህን የዘፈቀደ ዕገዳ ለማስነሣት ሁሉንም ሕጋዊ አማራጮችን የምንከተል መሆኑን ለመግለጽ እንፈልጋለ። በሕጉ በተቀመጠው መሠረት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ቦርድ ይህን የዘፈቀደ ዕገዳ ውሳኔ በጥልቀት እንዲመረምር እናውሳኔ እንዲሰጥበት ዛሬታኅሳስ 1 ቀን 2017 ይግባኝ አስገብተናል። ቦርዱ ችግሩን በጥልቀት ከመረመረ እና ገለልተኛ ግምገማ ካደረገ ይኼንን ችግር ሕጋዊነት እና ፍትሐዊነት በጠበቀ መልኩ እልባት ይሰጥበታል ብለን እናምናለን።
በተጨማሪም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት የሚከተለውን ጥሪ ለማስተላለፍ እንወዳለን
- ለኢፊዴሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን
- ችግሩን ለመፍታት የተጀመሩ ሥራዎችን በማፋጠን የድርጅታችን የዘፈቀደ ዕገዳ እንዲነሣ ስልን እንጠይቃለን።
- ሌሎች ተጨማሪ የምርመራ ሒደቶች መከናወን ያስፈልጋቸዋል ቢባል እንኳን በሕጉ በተቀመጠው እና በውይይቶቻችን በተስማማንበት መሠረት በምርመራው ጊዜ የድርጅቱን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ክልከላዎ ች አንዲነሡ እና ውል የገባንባቸው አስተዳደራዊ ወጪዎችን ለመክፈል እንድንችል እንዲደረግልን ጥሪእናስተላልፋለን።
- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) - ሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም እንደመሆኑ ችግሩን ለመፍታት እና የሲቪክ ምኅዳሩን ለመጠበቅ እና የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች በሕግ በተቀመጠው መሠረት በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ጥረት በማድረግ የአጋርነት ሚናውን እንዲጫወት እንጠይቃለን።
- የኢፌዴሪ መንግሥት በተለይም የፍትሕ ሚኒስቴር የሲቪክ ምኅዳርን ለመጠበቅ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ፣ የተጠሪ ተቋማት አሠራሮች ሕጋዊነት እና ግልጽነት በተላበሰ መልኩ እንዲሠሩ ማስቻል እና በኢትዮጵያ የሲቪክ ማኅበራትን አስፈላጊ ሚና ለማስቀጠል የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ እንጠይቃለን።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ አጋርነት ላሳያችሁን የዘወትር ወዳጅ እና አጋሮቻችን ምስጋና እያቀረብን ጥረታችሁን እንድትቀጥሉ በታላቅ የአጋርነት መንፈስ እንጠይቃለን።
የመብቶች እና የዲሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)
Add a review