Skip to main content

ካርድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ማሳያ ሪፖርት ይፋ ማድረጊያ መርሐ ግብር ላይ የሰላምና ተጠያቂነት ጥሪውን አቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ኢትዮጵያ - ሰኔ 8፣ 2014 - 36 ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ማሳያ ታሪኮችን ያጠናቀረ ሪፖርት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፣ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) በኢትዮጵያ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ሥምምነት እንዲደረስና ፍትሕና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ይፋዊ ጥሪ አቅርቧል። ካርድ ይፋ ያደረገው ሪፖርት በኦሮሚያ ክልል ጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች የተፈፀሙ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚያሳዩ ታሪኮች የተካተቱበት ነው። 

ለዓመታት በኦሮሚያ ክልል የጉጂ ዞኖች ውስጥ ታጣቂዎች እና የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ነውጥ አዘለግ ግጭት ውስጥ ከርመዋል። “የጉጂ ሰቆቃ፤ በኦሮሚያ ጉጂ ዞኖች ውስጥ የሚፈፀሙ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች” በሚል ርዕስ ያቀረበው የካርድ ሪፖርት፣ ነውጥ አዘል ግጭቶች በሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ላይ ያሳደሩትን ተፅዕኖ አሳዛኝ ምስል ያሳያል። በሪፖርቱ የተቀመጡት ጉዳዮች ከሕግ አግባብ ውጪ የተፈፀመ ግድያ፣ የዘፈቀደ እና የጅምላ እስራት፣ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ የንብረት መውደም፣ አስገድዶ መሰወር እና እገታ፣ ማሰቃየት፣ ኢሰብአዊ አያያዝ እና ማፈናቀልን ይጨምራሉ።

የካርድ ዳይሬክተር በፍቃዱ ኃይሉ "እነዚህ ማሳያ ታሪኮች የግጭቱን አስከፊ ጦስ ያጋልጣሉ" ብለዋል። ንፁኃን ዜጎች በነውጥ አጣብቂኝ ውስጥ ወድቀዋል ብለዋል።

ሪፖርቱን ይፋ በማድረጊያው ዝግጅት ላይ የተነበበው የሰላም እና የተጠያቂነት ጥሪ በጉጂ ዞኖች የሚኖሩ ነዋሪዎች ሰላምና መረጋጋት  ያለበት ሕይወት እንደሚገ'ባቸው ያወሳል። በግጭት ዐውድ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ከደረሰባቸው አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ለማገገም ሰላም፣ ፍትሕ እና ተጠያቂነት መስፈን እንዳለበት ሪፖርቱ ይናገራል። 

የካርድ የሰላምና ተጠያቂነት ጥሪ በጉጂ ዞኖች ብቻ አይወሰንም፤ ካርድ በኢትዮጵያ ነውጥ አዘል ግጭቶች መስፋፋታቸውን አስታውሶ፣ የትግራይን ሁኔታ ከተኩስ ማቆም በኋላም ቢሆን በአስተማማኝ ሰላም ውስጥ አለመሆኑን ጨምሮ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በአማራ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እየደረሰ ያለውን ጉዳት በመጥቀስ፥ እነዚህ ግጭቶች ቆመው፣ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰላም፣ ፍትሕ እና ተጠያቂነት ለማረጋገጥ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ዘላቂ መፍትሄዎችን ማፈላለግ አጣዳፊ ጉዳይ ነው ብሏል። 

ሪፖርቱ ነውጥ አዘል ግጭቶች የንፁኃንን ሕይወት ምን ያህል እንደሚያናጉ ጥሩ ማሳያ ምሳሌ ነው። ሁሉም ባለድርሻ አካላት፣ የታጠቁ ኃይሎች እና የመንግሥት አካላት አፋጣኝ የተኩስ ማቆም ሥምምነት ላይ እንዲደርሱ እና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ሐቀኛ፣ ሁሉንም ያሳተፈ ድርድር እንዲያደርጉ ካርድ በጥሪው ያሳስባል። ኢትዮጵያ ወደ ብሩህ ተስፋ ልትሸጋገር የምትችለው ለሰላምና ተጠያቂነት የጋራ ቁርጠኝነት ሲኖር ብቻ ነው።

Share this post

Comments (0)

Add new comment

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.