#በኢትዮጵያ_ሰማይ_ሥር፤ በአከራካሪ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጁ ዘጋቢ ፊልሞች ለዕይታ ይበቃሉ
የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) በተለያዩ አከራካሪ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሰናዳቸው ሰባት ዘጋቢ ፊልሞች ከዛሬ ሐሙስ፣ ግንቦት 3 ቀን 2015 ጀምሮ በአርትስ ቴሌቪዥን በየሳምንቱ ሐሙስ ከምሽቱ 1፡30 መታየት ይጀምራሉ።
ካርድ “ከኢትዮጵያ ሰማይ ሥር” በሚል መሪየ ርዕስ አከራካሪ ጉዳዮች በውይይት ለማጥራት በማሰብ፣ ርዕሰ ጉዳዮቹን በይፋዊ የበይነመረብ ዜጎች ተሳትፎ በማስመረጥ፣ በባለሙያዎች ጥናት እና ተሳትፎ፣ እንዲሁም ከአገሪቱ ክልሎች በተውጣጡ በወጣቶች አስተያየት ሰጪነት ሰባት የ30 ደቂቃ ዘጋቢ ፊልሞችን አዘጋጅቶ ከዛሬ ጀምሮ በአርትስ ቴሌቪዥን ያስተላልፋል።
ዘጋቢ ፊልሞቹ የሚተላለፉበት ጊዜ የሚከተለው ነው።
ግንቦት 3 - “መጥፎ ሰላም”፣ “ጥሩ ጦርነት”
ግንቦት 10 - ታሪክ እና ትርክት
ግንቦት 17 - አዲስ አበባ፤ በዕድገት እና ውዝግብ መሐል
ግንቦት 24 - “አረሱት”፤ የአስተዳደር ወሰን ውዝግቦች
ሰኔ 1 - የፌዴራሊዝሙ አወቃቀር፤ እየሰጡ መንሳት?
ሰኔ 8 - ልዩ ኃይሎች፤ በተፎካካሪ የብሔር ፖለቲካ ውስጥ
ሰኔ 15 - የበይነመንግሥታት ግንኙነት
የዘጋቢ ፊልሞቹ ዝግጅት፣ ካርድ ዴሞክራሲያዊ ባሕል ያበበባት ኢትዮጵያን ለማየት ራዕዩ አከራካሪ ጉዳዮች ላይ ዜጎች የሚወያዩበት እና መፍትሔ የሚፈልጉበት መድረክ መፍጠርን አንዱ ዓላማው ካደረገው የዜጎች ተሳትፎ መርሐ ግብሩ ሥር የተዘጋጀ ነው። የውይይት መድረኩ እና በውይይቱ ላይ የተነሱት ምክረ ሐሳቦች ኢትዮጵያ ለምታሰናዳው የአገራዊ ምክክር ጥሩ ግብዓት ይሆናል ብሎ ማዕከላችን ያምናል።
“በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር፤ አከራካሪ ጉዳዮች በውይይት ማጥራት” የተሰኘው ፕሮጀክት በአሜሪካ ልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤይድ) የገንዘብ ድጋፍ የተዘጋጀ ነው።
Comments (0)
Add new comment